ለሰሞኑ ግጭት ሚና አላቸው የተባሉ 407 ሰዎች መያዛቸውን መንግሥት ገለጸ
ባለፈዉ ሳምንት ከጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ከተፈጠረው ክስተት ጋር ተያይዞ ግጭት በመቀስቀስ የተጠረጠሩ ናቸው የተባሉ 407 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በሰሞነኛው አሳዛኝ ግጭት የ78 ዜጎችን ሕይወት ማለፉን የገለፀው መግለጫ ግጭቱን ብሔር እና ሃይማኖት ተኮር ለማድረግ የተንቀሳቀሱ የመንግስት ሃላፊዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከሰዓት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው ላይ በወቅቱ በግጭቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የፀጥታ መዋቅሩ በሙሉ አቅሙ መሥራቱንም ነው የጠቆሙት።
ችግሩን ለማርገብ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት አስተዋፅዖ መንግሥት ምስጋና አቅርበዋል።
በሃገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ተመሳሳይ ግጭቶች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 3 ሺህ 221 ግለሰቦች መካከል ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት ለሕግ መቅረባቸውንም አብራርተዋል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መግለጫ ይሰጣል መባሉን ተከትሎ በርካታ የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉዳዮ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ያቀርባሉ በሚል ዘግበው የነበረ ቢሆንም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት ግን አቶ ንጉሱ ጥላሁን ሆነው ተገኝተዋል::
ዶ/ር ዐቢይ አምቦ ከተማ ሲደርሱ ከበርካታ ወጣቶች ተቃውሞ ገጠማቸው
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአምቦ ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ቢወያዮም ውይይቱን መታደም ካልቻለው ነዋሪ ከባድ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ትናንት በጅማ ሐረር እና አዳማ ከተሞች እንደተደረገው ሁሉ የኦዴፓ ካድሬዎችና የከተማው መስተዳደር አካላት ታማኝ ሰዎቻቸውን በስብሰባው እንዲታደሙ በማድረግ ግልጽ የሆነ ሸፍጥ ሠርተዋል::
በአምቦ ነዋሪ እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ስም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ታማኝ የኦህዴድ ካድሬዎች ብቻ የታጨቁበት አዳራሽ መዘጋጀቱ በእጅጉ ያስቆጣቸው የአምቦ ወጣቶች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል:: ዕድሉ ተሰጥቷቸው ወደ ውይይቱ እንዲገቡም ጥያቄያቸውን በይፋ አሰምተዋል::
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምቦ ከተማ ላይ አነጋገሯቸው የተባሉት ሰዎች የተመረጡ ካድሬዎችና አንዳንዶቹም ከግጭቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው የሚሉት በስልክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች መሪዎች ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ የሚያደርጉ እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች ፈጽሞ ችግሩን ሊፈታ እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል::
በውይይቱ ላይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተገኝተዋል።
በተያያዘ ዜና አምቦ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይየአምቦ ከተማ፣ የምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የቡራዩ፣ የሆለታ እና የወሊሶ ከተማ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች መገኘታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል::
በተመሳሳይ የአራቱ የወለጋ ዞኖች ማለትም የምስራቅ፣ ምእራብ፣ ሆሮ ጉዱሩ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች እንዲሁም የነቀምቴ ከተማ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የሰላም ኮንፍረንስ በነቀምቴ ከተማ ተካሂዷል። የኢህአዴግ እና የኦዲፒ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ በኮንፍረንሱ ላይ በመገኘት ተሳታፊዎችን አወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ በዳሳ ጂንፌሳ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኦሮሞ ህዝብ ባለው እሴት አንድ ሆኖ የባርነት ቀንበርን እንደሰበረ ሁሉ ችግሮቹንም በአንድነት በመሆን በውይይት መፍታት አለበት ካሉ በኋላ፤ አንድ መሆን ከቻልን ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንችላለን ሲሉም ተደምጠዋል::
ኢትዮጵያና ግብፅ አሜሪካ የሚገናኙት ለድርድር ሳይሆን ለውይይት ነው ተባለ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት ግብፅ አሜሪካ ታደራድረን በሚል ያቀረበችውን ሃሳብ ኢትዮጵያ አልቀበልም ብላለች ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከቀናት በፊት በሩሲያ፣ ሶቺ መገናኘታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሦስተኛ ወገን ቢገባ ምንም ችግር እንደሌለው ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ዛሬ ኢትዮጵያና ግብፅ በመጭው ህዳር ወር ማብቂያ ላይ ዋሽንግተን ላይ ድርድር አዘል ውይይት እንደሚያደርጉ የግብፅን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጥቀስ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ውለዋል።
አሜሪካም፣ ሩሲያም የማደራደር ፍላጎት እንዳላቸውና እርግጥም ለኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ባቀረበላቸው ግብዣ መሰረት የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ህዳር ወር ላይ አሜሪካ ላይ ለመገናኘት መስማማታቸውን፤ ነገር ግን ለድርድር ሳይሆን ለውይይት ብቻ እንደሚቀመጡ ቢቢሲ ታማኝ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ረፋዱ ላይ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል:: የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ሦስቱ አገራት ለውይይት ዋሽንግተን እንደሚገናኙ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች የቴክኒካል ስብሰባው እንዲቀጥል ተስማምተዋል። ምንጮቹ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አቋም አሁንም “የድርድር ነገር ገና ነው” የሚል እንደሆነና “ሁለቱ መሪዎች የቴክኒካል ቲሙ ሥራውን ይቀጥል ልዩነት ካለ እኛ እየተገናኘን እንፈታለን ነው ያሉት” ሲሉ መስማማታቸውን ይናገራሉ።
ወደ ድርድር ለመሄድ፤ መጀመሪያ አገራቱ አደራዳሪ ያስፈልገናል ወይ? ድርድሩ በምን ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩረው? በሚሉ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው የሚሉት ምንጮች፤ ቀጥሎም የአደራዳሪው ሓላፊነት ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ወስነው አደራዳሪውን በጋራ መምረጥ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ድርድር ሊኬድ እንደማይቻል ብሎም ወደ ድርድር መሄድ ራሱ ቀላል እንዳልሆነና የራሱ አካሄድ እንዳለውም ጭምር ያስረዳሉ።ከዲፕሎማሲ አንፃር የአሜሪካን ላወያያችሁ ጥያቄ አለመቀበል ከባድ ስለሚሆን ኢትዮጵያ ከዚህ የተነሳ ነገሮችን እንደምታስኬድ ምንጮቹ አስታውሰዋል።
በጎንደርና ባህር ዳር ለሚገነቡ አዳሪ ት/ቤቶች የሚውል የጎዳና ሩጫ በአሜሪካ ሊካሄድ ነው
በጎንደር እና ባሕር ዳር ከተማ ሊገነቡ ለታቀዱት ሁለት አዳሪ ትምህር ቤቶች የሚውል የገቢ ማስገኛ የጎዳና ላይ ሩጫ የፊታችን ቅዳሜ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ሊካሄድ መሆኑ ተነገረ፡:
በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚካሄደውን የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ “ወንፈል” በተሰኘ የተራድኦ ድርጅት እንደተዘጋጀም ሰምተናል::
ድርጅቱ በአማራ ክልል ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች ለሚያስገነባቸው የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህር ቤቶች ገቢ ለማሰባሰብ ታስቦ የተዘጋጀ ሩጫ መሆኑን የድርጅቱ አመራር አባል ዶክተር ይንገሥ ይግዛው ይፋ አድርገዋል፡፡
በገቢ ማስገኛ መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የጎዳና ላይ ሩጫው ከዋሽንግተን ዲሲ በተጨማሪ በሳን ሆዜ፣ በችካጎ፣ በአትላንታ፣ በሲያትል፣ በሎስንጀለስ፣ በሳክራሜንቶ እና በሌሎችም ከተሞች በተመሳሳይ ቀን እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል::
ወደፊትም በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች ሩጫውን በማድረግ ገቢ የማሰባሰብ መርሀ ግብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ በተለያዩ ከተሞች በሚደረገው የጎና ላይ ሩጫም 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ተገምቷል። ትምህርት ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 100 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ነው እየተነገረ ያለው::
ዕስር ላይ የሰነበቱት የአማራ ክልል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር በዋስትና እንዲለቀቁ ተወሰነ
ከባህር ዳሩና ከአ/አ ከፍተኛ አመራሮችና ጀነራሎቹ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩት ረዳት ኮሚሽነሩ በዋስትና እንዲለቀቁ ተወሰነ:: ጉዳዮን የያዘው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ማሳለፉን ባለቤታቸው ወ/ሮ ሰሚራ አህመድ ም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ይህ ውሳኔ የተሰጠው ዛሬ ሀሙስ ጠዋት ሲሆን ግለሰቡከሰዓት በኋላ ከዕስር ተፈትተው ቤተሰባቸውን ይቀላቀላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ለሳምንታት በክልሉ ሥራ አመራር ተቋም ውስጥ ስልጠናና ግምገማ ካካሄዱ በኋላ ረዳት ኮሚሽነሩ መታሰራቸውን በሰዓቱ ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል። ረዳት ኮሚሽነሩ ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ባህርዳር ውስጥ ከተከሰተው የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው መታሠራቸው አይዘነጋም።
ከሰኔ 15ቱ ግድያ ጋር ተያይዞ በጥርጥሬ ተይዘው የነበሩት የአማራ ክልል የደህንነትና ፀጥታ ሓላፊዎች ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞና ኮሎኔል አለበል አማረ ከጥቂት ቀናት በፊት በዋስ ተፈትተዋል።
በተያያዘም ከሰኔ 15ቱ ግድያ ጋር በሽብር ተጠርጥረው ለአራት ወራት እስር ላይ የነበሩት የባልደራስ አባላት እንዲሁም የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ባለቤት ከትናንት በስቲያ በዋስ መለቀቃቸውም ይታወቃል። በዕለቱ የአብንና የባላደራው አባላት መፈታታቸውን በተመለከተ በሠራነው ዘገባ ላይ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ክርስቲያን ታደለ ከዕስር መፈታታቸውን ገልጸን ነበር:: ሆኖም ማክሰኞ ዕለት ምሽት አካባቢ በርካታ ዕስረኞች ሲለቀቁ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት ክርስቲያን ታደለ በዕስር እንዲቆይ ተደርጓል::
በሞጆ ከተማ 60 ንግድ ቤቶች ዛሬ በእሳት መጋየታቸው ተረጋገጠ
በሞጆ ከተማ በልዮ ስሙ ” ገበያ ” ተብሎ በሚጠራዉ ስፍራ ዛሬ ለሊት 10፡00 ላይ ከፍተኛ የሆነ የእሳት አደጋ እንደደረሰ ታወቀ::
ባጋጠመው የእሳት አደጋ እስከ ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ በተመዘገበ መረጃ 60 የሚሆኑ ሱቆች መውደማቸው ተረጋግጧል:: ዘግየት ብሎ በጉዳዮ ላይ መግለጫ የሰጠው የከተማው የመንግሥት ኩሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም የተባለውን ግምት ያመላከተ መግለጫ አውጥቷል።
የእሳት አደጋው ወደሌሎች አካባቢ እንዳይዛመት በኅብረተሰቡና በእሳት አደጋ ሠራተኞች ትብብር በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ተብሏል፡፡ አደጋውን ለመከላከልም የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ከአዳማ፣ ከቢሾፍቱ እና ከግል ድርጅቶች ወደ ስፍራው መምጣታቸውም ተገልጿል፡፡
በአደጋው የወደመው የንብረት መጠን ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ሞጆ የሞጆ ከተማ ፖሊስ መመሪያ ሓላፊ ኮማንደር ሙሃመድ አህመድ አስታውቀዋል።
ንጹህ ዉሃ ላይ የሚያተኩረው የዋን ወሽ ምዕራፍ 2 መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ
የዋን ወሽ የምዕራፍ ሁለት መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ መጀመሩ ተገለጸ:: መርሃ ግብሩ 309 የገጠር ወረዳዎች እና 69 አነስተኛ እና መካከለኛ ከተሞችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
ፕሮግራሙ በንጹህ ውሃ አቅርቦት እና በመጸዳጃ ግንባታ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚተገበር እንደሆነም ሰምተናል:: መርሃ ግብሩ በገጠራማ የሃገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የጤና እና ማህበራዊ ችግሮችን የሚያቃልል ነው ተብሎ በመንግሥት ታምኖበታል።
ዛሬ የምዕራፍ ሁለት ፕሮግራሙ በይፋ ሲከፈት በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና፣ የትምህርት እና የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሮች እንዳስታወቁት፣ ፕሮግራሙ የኀብረተሰቡን የንጹህ መጠን ውሃ ፍላጎት እና ከውሃ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ።
ለዚህ ፕሮግራም ማስፈጸሚያም 569 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበና ከአራት ሚሊዮን በላይ ዜጎችተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከደረሰን መረጃ መረዳት ችለናል።
ቻይና በኢትዮጵያ ተጨማሪ ኩባንያዎችን የማሠማራት ዕቅድ አላት ተባለ
ቻይና በሀገሪቱ የሚገኙ ተጨማሪ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደምታበረታታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።
በቻይና ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ልዩ መልዕክተኛ እና የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በቤጂንግ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፥ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካው ዘፍር ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት መሥራት እንደሚጠበቅ እና የሀገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ለመደጋገፍ እንደሚሠራ ፤በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መጠነ ሰፊ ትብብር የበለጠ ለማጠናከርም ቻይና በርካታ ኩባንያዎቿ በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ድጋፍ እና ትበብር እንደምትሰጥም ገልጸዋል።
በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም የሁለቱን ሀገራት እንዲሁም የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በጋራ የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው የተባለው::