ታዬ ደንደዓ ቤቲን ቢጠይቃት… || ቴዲ አትላንታ

ታዬ ደንደዓ ቤቲን ቢጠይቃት… || ቴዲ አትላንታ

“በተደጋጋሚ ሳይሽ ቃለመጠይቅ ስታደርጊ ቀይ ሊፒስቲክ ትቀቢያለሽ፣ አንቺ የዚህ ቴሌቪዥን ተቀጣሪ ሰራተኛ ነሽ፣ ይህን ማድረግሽ ቴሌቪዥን ጣቢያው ቀይ ቀለም ይወዳል የሚል ግንዛቤ ሊያሰጥ አይችልም ወይ?” ሊል ይችል ነበር …

የቤተልሄም ታፈሰ እና የታዬ ደንደዓ ቃለመጠይቅን በተጣበበ ጊዜ አየሁት። በየሰከንዱ የሚታይ፣ በየሰከንዱ የሚነበብ ወሬ እንደጉድ በሚፈቅልበት ጊዜ ሁሉን ማየትና ማዳመጥ አይቻልም።

ለማንኛውም የቤቴ የመጀመሪያ ጥያቄ ከላይ የጠቀስኩት ተገልብጦ ዓይነት ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት እስከዛሬ ድረስ “በድርጅት አቋም” “በርዮተዓለም” “በመመሪያና ትዛዝ” ብቻ ሲንቀሳቀስ ለኖረ አገር፣ እንኳን የሚናገረውን የሚለብሰውን ሁሉ ተመርጦለት “ሰማያዊ ካኪ” ይገደግድ የነበረ ሰውን ያየ ፣ ሰው የብቻው የቆመ አቋም እንዳለው ባያውቅ አይፈረድበትም። “እንዴት የድርጅት መሪ ሆነህ የግል አቋም ኖረህ” ዓይነት ጥያቄ የመጣው ቤቲ በደርግና ከለውጡ በፊት በነበረው ኢህአዴግ ያደገች በመሆኗ ይመስለኛል።አይፈረድባትም፣ ግን መቀየር አለባት።

ሰው የድርጅት አቋም ሊኖረው ይችላል፣ የማህበር አቋም ሊኖረው ይችላል፣ የግል አቋም ሊኖረው ይችላል። ዲሞክራሲ ሲጎለብት ይህ ይመጣል። አሜሪካን አገር ዛሬ ይህን ነገር ስሞነጭር ሁለት ጀግኖች ዲሞክራቶች ብቅ ብለው ነበር። ዲሞክራቶች ሰሞኑን ትልቁ አጀንዳቸው አድርገው የያዙት ፕሬዚዳንቱን ተጠያቂ ማድረግ /ኢምፒች ማድረግ/ ነበር። ዛሬ ድምጽ ሰጡ፣ ሁሉም የምክር ቤት አባላት የሆኑ ዲሞክራቶች ሃሳቡን ሲደግፉት ሁለት ዲሞክራቶች ግን ተቃውመውታል። እኔ በግሌ መቃወማቸውን ባልደግፍም፣ በመቃወማቸው ግን አድንቄያቸዋለሁ። ከፓርቲ አቋም በላይ የግለሰብ ነጻነታቸውን አስከብረዋል። ታዬ ደንደዓም እንደዚያ ነው ያደረገው። ከጀማው ተለይቶ የግል አቋምን በድፍረት ማንጸባረቅ ጀግንነት ነው። እኛ አገር ይህ ቢለመድ ይህ ሁሉ መቶ ምናምን ድርጅት አይፈጠርም ነበር።

ቤቴ ያልገባት ነገር ይህ ይመስለኛል። የድርጅት አባልና አመራር የሆነ ሰው ከድርጅቱ አቋም ለየት ያለ አንድ ነገር እንኳን ማራመድ አይችልም ብላ ማመኗ የሷ ችግር እንጂ የታዬ ግን አይደለም።

አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሚናገሩትና የሚጽፉት ነገር በሙሉ በሚመሩት ድርጅት በኢሰመጉ እየተሳበበ “ኢሰመጉ እንዲህ አለ” እየተባለ የድሮዎቹ ኢቲቪና አዲስ ዘመን ሲያጥላሉት፣ እሳቸው አንድ ቀን ተነሱና “ለመሆኑ መስፍን ወልደማርያም ዶሮ ወጥ እወዳለሁ ቢል ኢሰመጉ ድሮ ወጥ ይወዳል ልትሉ ነው?” ሲሉ ተቿቸው። በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጭንቅላት ውስጥ ዲሞክራሲ አድጎና በልጽጎ ነበር።

ቤቲ እንደ ጋዜጠኛ እንዲያውም ከፓርቲና ማህበር የወል አቋም ለየት ያለ ሃሳብ የሚሰነዝሩትን ማሞገስ፣ ጎበዝ ማለት ነው ያለባት እንጂ፣ የድርጅትዎ አቋም ሳይሆን ለምን ይህን አሉ፣ የርስዎን ጽሁፍ ሁሉ የድርጅቱ አቋም አድርጌ ነው የማየው ማለት አልነበረባትም።

የታዬ ደንደዓ መረጋጋትና በግፊቱ ከመስመር ሳይወጣ፣ እሷ ጠያቂዋ ስትጮህ እሱ በረጋ ድምጽ መመለሱ፣ እሱ እየጠየቀ እሷ የምትመልስ ነበር ያስመሰለው።

አንዱ ችግር ያየሁት፣ ቤቲ ስትጠይቅ መልሱን አብራ ጨምራ ነው፣ “ወጣቱን ለምን አፈናቀላችሁት፣ አያሳዝንም?” ስትል አፈናቅላችኋል ብላ ደምድማ ነው። “የኦሮሞ ድርጅቶች አንድ ሆናችሁ አገር መምራት ሲኖርባችሁ እንዴት ትከፋፈላላችሁ” ስትል ኦነግ አገር መምራት አለበት ብላ ደምድማ ይመስላል። እንግዲህ ፖሊቲካ እንዴት እንደሚሰራ፣ እንዴት እንደሚሄድ ካለማወቅ የመጣ ነው። አንድ ድርጅት በሂደት ታግሎና መስዋትነት ከፍሎ መንግስት ሲሆን፣ አንዱ ከተኛበት ተነስቶ መጥቶ፣ ምን ፖሊሲ እንዳለው፣ ምን አቋም እንዳለው፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በሶሻል ፖሊሲ፣ በአገር አመራር፣ በሥራ ፈጠራ፣ በህክምና ፖሊሲ ምን ሊሰራ እንዳሰበ እንኳን ለሌላው ሊያሳውቅ፣ ለራሱም የማያውቅ ድርጅት “በስመ የኦሮሞ ድርጅት” ብቻ አገር መምራት ውስጥ ለምን አልገባም ስትል ትልቅ የሳተችው እና ያልገባት ነገር ያለ ያስመስላል። ታዬን አፋጥጣለሁ ብላ የራሷን አለማወቅ ነው ያሳወቀችው። አንድ ጎሳ ስለሆኑ ብቻ አንድ የፖሊቲካ አቋም እንዴት ሊኖር ይችላል? ያን ስታዋለች።

መንገድ ተዘግቶ እርጉዞች ማለፍ እንዳቃታቸው፣ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መግባት አለመቻላቸው ትክክል አለመሆኑን፣ በአጠቃላይ፣ ማንም ድርጅት መሰርቶ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ በምርጫ መወደዳደር ይችላል በተባለበት ዘመን በመንጋ አስተሳሰብ አገር ማመስን፣ መንገድ መዝጋትን፣ ሰው መግደልን በጥቂቱም ቢሆን ሳትተች ፣ ጭራሽ በአዘኔታ መንገድ የሚዘጋው እኮ ወዶ አይደለም አይነት ስሜት ማንጸባረቋ ሌላው የገረመኝ ነገር ነው። ጥያቄ መጠየቅ እኮ ይቻላል። ጥያቄ ግን ህገወጥነት በመደገፍ መልክ መቅረብ የለበትም።

የጃዋር ጥበቃ መነሳትም ያን ያህል የሚያስቆጣት አልነበረም፣ ይልቁኑ ጃዋር ሁለት ዓመት ሙሉ ወታደር መድቦ ለጠበቀው መንግስት ከወገቡ ጎንበስ ብሎ ምስጋና ማቅረብ ነበረበት። ለምን በሌሊት ጠባቂዎቹ እንዲነሱ ተደረገ (ቀን ሊሆን አይችልም ወይ) ብሎ መጠየቅ ትክክል ቢሆንም፣ አጠያየቁ ግን “ሰውየው ለምን ተነካ” በሚል ቁጭት መመስል የለበትም።

ከዚሁ ጉዳይ ሳንርቅም፣ ጃዋርን አስመልክቶ አቶ ታዬ ለጻፈው ሃሳብ “የመጨረሻ ጥያቄዬ” ነው ብላ በጠየቀችው ሰዓትም፣ እሱ በስሜት እያብራራ እያለ፣ እሷ ሌላ ጥያቄ እንደሌላት በተረጋገጠበት ሁኔታ፣ ማስታወሻዋን እየገለጠች፣ እያገላበጠች ታዬን የማትሰማ መምሰል አልነበረባትም። ቢያንስ በቅርብ ለሷ ነው እየተናገረ ያለው – እሷው ጠይቃ እሷው ካልሰማች እንዴት ይሆናል? እሱ እሷን እያየ ያወራል፣ እሷ ምንም ለማትፈልግ ነገር ፣ ወረቀቷን ታገላብጣለች። ሌላ ጊዜ ብታርመው ጥሩ ነው።

ከዚያ በተረፈ ግን ድርጅቶች ፤በተለይ የገዢው ፓርቲ አካላት የሆኑት፣ በአደባባይ መዘላለፋቸው ቢቀር የሚል ሃሳብ ማቅረቧ ትክክል ነው። እነሱ በአደባባይ በተሰዳደቡ ቁጥር ተከታዮቻቸው ጎራ ለይተው በቦክስ ይቃመሳሉ። እዚያው ተወቃቅሰው አንድ ሃሳብ እንደ አቋም ይዘው ቢመጡ በርግጥም ይሻላል።

ጋዜጠኛ ቤተልሄም አዲስ ዓይነት የአጠያየቅ ባህል ይዛ በመምጣቷ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት አድናቂዋ ነኝ፣ አሁን አሁን እሷን ተከትሎ በፋናም በሌሎችም በተመሳሳይ ዓይነት መንገድ ጠያቂዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። ለዚያ ፋና ወጊ በመሆኗ ከነስህተቷ ልትደገፍ ይገባል፣ እሷ ያበላሸችውን ሌላው እያስተካከለ፣ እሷም ራሷን እያስተካከለች ትሄዳለች ብዬ አምናለሁ። ትንሽ የተሳሳተ የመሰለንን ሁሉ ኮርኩመን የምናባርር ከሆነ ሰው አናፈራም። ላሪ ኪንግ ቁጥር አንድ ጎበዝ ጠያቂ የሆነው 32 ዓመት በሥራው ላይ ቆይቶ ነው። የመጀመሪያውን አምስት ዓመት እንዴት ነበር የሰራው? እግዜር ይወቅ።

ሃሃሃ … የቤቲና ታዬን ቃለመጠይቅ አይቼ ይቺን እየጻፍኩ እያለ፣ ዩ ቲዩብ ራሱን ቀይሮ መረጃ ቲቪ የሚል ብቅ አለ … ስንት ደረቅ አለ ግን ባካችሁ …፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚዲያ ሥራ ለመሳተፍ የሆነ መስፈርትማ ያስፈልጋል።

LEAVE A REPLY