ግልጽ ደብዳቤ ይድረስ: ለአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ
ኢትዮጵያን የመምራት ሃላፊነት እጅዎ ላይ በወደቀበት በእዚህ ታሪካዊ ወቅት አገሪቱን የህወሃት የበላይነት ከነበረበት የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ የስርአት ለውጥ ለማሻገር ሁለት የተሻሉ አማራጮች ከፊትዎ ተደቅነው ነበር።
አንደኛው አማራጭ በኢህአዴግ በውስጡ የተገኘውን የስልጣን ሽግሽግ በመጠቀምና ግንባሩን ራሱን መሳሪያ በማድረግ፣ በተነጻጻሪ ሰላማዊ ሊሆን በሚችል ሁኔታ፣ ደረጃ በደረጃ በሚካሄዱ ለውጦች አማካይነት ሽግግሩን ማጠናቀቅ ነው። ይህ አማራጭ የሚፈልጋቸው ቅድመ~ሁኔታዎች ግን ነበሩ፤ እነሱም እርስዎ ራስዎን የሽግግር ወቅት ጠ/ሚ ብቻ አድርገው ማየት፤ ስላም፣ ጸጥታ፣ ህግና ስርአት ማስከበር እንዲሁም ተጠያቂዎችን ለፍትህ ማቅረብ፤ ድርጅቶች ወደ አገር የሚገቡበት ለህዝብ ግልጽ የሆነ የሰላማዊ መንገድ መፎካከሪያ መስፈርቶችን በማውጣት ሁሉም ሀይሎች የሚሳተፉበት የዳያሎግ መድረኮች ተዘጋጅተው ሁሉም ጥያቄዎች (ህገ~መንግስቱና የፌዴራል መዋቅሩን ጨምሮ) ያለገደብ ለድርጅቶችም ለህዝቡም ለውይይት፣ ለክርክርና ለድርድር እንዲቀርቡ ማድረግ፤ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፤ ለነዚህ ቅድመ~ሁኔታዎች የሚያመቹ ህጋዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ፤ እስከዚያው ድረስ መንግስታዊ መዋቅሩ ሳይቀያየር በነበረበት ቆይቶ ወደ ነጻና ተአማኒ ምርጫ መሄድ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ የራስዎን ፓርቲ (ኢህአዴግም ሆነ ሌላ) ለምርጫ ማዘጋጀት መብትዎ ይሆናል። ሁለተኛው አማራጭ ስልጣን እንደያዙ ወዲያውኑ ሁሉንም ሀይሎች ኢህአዴግንም ጨምሮ የሚያሳትፍ የሽግግር ወይም የባለአደራ (ወይም ሌላ ተመሳሳይ ስም ሊሰጠው የሚችል) አስተዳደር በማቋቋም ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ~ሁኔታዎች ባሟላ ሂደት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚያስኬደውን ጉዞ መያያዝ ነበር።
እርስዎ ሁለቱንም አማራጮች ወደ ጎን አድርገው የራስዎን ሌላ መንገድ ተከተሉ። ወይ ኢህአዴግን በአንድነት ጠብቀው የሚያሻግር ድርጅት አድርገው ሊጠቀሙበት አልቻሉም ወይም ደግሞ የሽግግር አስተዳደር አቁመው ሊያሻግሩ አልቻሉም። የመረጡት መንገድ ራስዎን ብቸኛ አሻጋሪ አድርገው ማስቀመጥ ሆነ። “አሻግራችኋለሁ” የሚለውን ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢገቡም በተግባርዎ ሊመሰክሩም ሆነ ሊያስመሰክሩ ግን ከቶ አልቻሉም። እንዲያውም የስልጣን እርካብዎን ተወጣጥተው መንበርዎ ላይ በተቀመጡ ጊዜ ባሰሙት አስገራሚ ኢትዮጵያዊ ንግግርዎ የተነሳ አግኝተውት የነበረውን በኢትዮጵያ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቀውን ድጋፍ ቢያገኙም አመት ባልሞላ ጊዜ ድጋፍዎ ሁሉ እየበነነ፣ እነሆ ዛሬ የኖቤል ሽልማትዎ እንኳ ሊያክመው ባልቻለበት ደረጃ ተከስክሶ ይገኛል። ይህ የሆነው ህዝቡ በእርስዎ ላይ የተለየ ግላዊ ጥላቻ ስላለው ሳይሆን በእርስዎ በራስዎ ተግባር የተነሳ፣ ከአሸብራቂ ንግግሮችዎ በስተቀር ፍሬውን ያልቀመሰበት ብቻ ሳይሆን ከቀድሞው ይበልጥ መራራ ፍሬ እየመገቡትና እያስመገቡት በመሆንዎ ነው። ህዝቡማ እየፈጸሙ ያሉትን ጥፋትና ስህተት ብቻ ሳይሆን ሊፈጽሙት እየተገባዎ ያልፈጸሙትን ሃላፊነትዎንም ጭምር እየታገሰ፣ እድል እንስጣቸው እያለ ከልክ ያለፈ ትእግስቱን ቸረዎታል፤ አንዳንዴ ሌሎች አላሰራ ብለዋቸው እንጂ እሳቸውማ አላማቸው ቅዱስ ነው እያለዎ፣ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ጽንፈኞች ተጠልፈው ነው እያለዎ፣ የሰበብ ዝርዝር እየደረደረልዎ ትእግስቱን ሰጠዎት።
በአንድ በኩል ስለ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት ዘወትር እየተናገሩ በሌላ በኩል በተለይ የኦሮሞ ብሄረተኛ ቡድኖችና የትህነግ ቡድን እንዲሁም ሌሎች እኩያን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ የጣሉ እርምጃዎችን ሲወስዱ፣ የእነ ጃዋር አይነት ዲያቢሎሳዊ ሀይሎች ከሁለት አመት በፊት በለንደን ያወጁትን የብተና አዋጅ በኢንትራሃምዌ ፋና እየተመሩ አገሪቱን ለመበታተን ተግባራዊ ሲያደርጉ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ ሲሆኑ የሚሰብኩትን የኢትዮጵያዊነት ስብከት ሲኖሩበት አልታዩምና ህዝቡ እምነት ቢያጣብዎት ፍርዱ ነው። ራስዎ የሚመሩት ድርጅት ኦዴፓ መሪዎችን ጨምሮ አገሪቱን አደጋ ላይ የጣሉ ብሄረተኞች እንዳሻቸው ሲሆኑ በህዝብ ገንዘብ አሉ በሚባሉት ሆቴሎች እየተምነሸነሹ፣ በመንግስት ወታደሮች ሲያስጠብቋቸው ህዝቡ ሲያይ እኚህ ሰው እውነት ለኢትዮጵያ የቆሙ ናቸው ወይስ ከትግራይ ልሂቃን የበላይነት ወደ ኦሮሞ ልሂቃን የበላይነት፣ ለሌላ ተረኝነት የተነሱ መሪ ናቸው ብሎ ቢጠረጥር ፍርዱ ነው።
አዲስ አበባ ላይ “ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ብለው ሲያውጁ፣ አማራ ክልል ላይ ወታደራዊ ልብስ ያስለበሰዎትን ቀልጣፋ እርምጃ ሲወስዱ፣ ያለ ማስረጃ ማሰር አብቅቷል ባሉ ማግስት ወጣቶች ሲታፈሱ፣ ያለመረጃ መታሰራቸውን ታስረው የተፈቱ ሲመሰክሩ፣ ስለ ሶሻል ሚዲያ አገር አፍራሽነት በይፋ ሲወቅሱ፣ የተቃወሙዎትን የዳያስፖራ ሰዎች “እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” ብለው ለፈጣሪ ቅጣት አሳልፈው ሲሰጡ … ወዘተ. በሌላ በኩል ግን አገር ለማፍረስ የሚደክሙትን፣ በአንድ የሶሽል ሚዲያ መልእክት ዜጎች እንዲሞቱ ምክንያት የሆነን ወንጀለኛ ግለሰብና ቡድኑን፣ አንዳሻቸው
ህዝቡ ላይ ሲፈነጩ የሚውሉትን ስርአተ አልበኞች እየተመለከቱ ምንም እንዳልሆነ ዝምታን ሲመርጡ፣ ከወንጀለኛ ጋር ድርድር ውስጥ ሲገቡ ህዝቡ ቢታዘብ ለምን ብሎ ቢጠይቅና ፊቱን ቢያዞርብዎት አሁንም ፍርዱ ነው።
ተገንዝበውትም ይሁን በውል ሳይገነዘቡት አገሪቱ ያለችበት አደጋ ከዚህ ቀደም ገብታበት የማታውቀው አይነት ነው። የአደጋው ትእይንተ~መቅድም እነሆ በአሰቃቂና በአሳፋሪ ሁኔታ ዜጎች በሜንጫ እየተጨፈጨፉ በመታየት ላይ ይገኛል። አሻጋሪ መሆንዎት ይቅርና ህዝቡንና አገርን መጠበቅ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ መሪ ሆነዋል። ህዝብንና አገርን የመጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነት ቢኖርዎትም፣ እንዲሁም ደግሞ ይህን ህላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ራስዎ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑበት መከላከያ ሰራዊት፤ በቀጥታ ለእርስዎ ተጠያቂ የሆነ የደህንነት ተቋም፤ አገር የማፍረሱ ፕሮጀክት ተካፋይ የሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያሉበት እርስዎ የሚመሩት የኦዴፓና የካቢኔት ተቋሞች ይዘው በሚገኙበት ስልጣንዎ ህዝብንና አገርን ሊታደጉ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ግልጽ ሆኗል። የሰሞኑ የጃዋር ቡድን ዲያቢሎሳዊ ተልእኮና እርስዎን ጨምሮ ከኦዴፓ፣ ከመከላከያና ከፖሊስ ባለስልጣናት የወሰዳችሁት አቋም፣ ከሞስኮ ከተመለሱ በኋላ ከቤተመንግስት አስከ ሃረርና አምቦ ያደረጉዋቸው ውይይቶች የነገሩ ሁሉ መደምደሚያ ሆኗል። እርስዎና ቡድንዎ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከኢትዮጵያ ይልቅ አገር አፍራሽ የኦሮሞ ብሄረተኞችን፣ የዲያቢሎስ መልእክተኛውን ጃዋርንና መሰል ቡድኑን፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ኤምፓየር ህልም እንጂ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ህልመኛ አለመሆንዎ ለደጋፊዎችዎም ሳይቀር፣ ከርስዎ የሚያገኙት ፍርፋሪ የሚያሳሳቸው ካልሆኑ በስተቀር፣ ግልጽ ሆኗል።
በነገራችን ላይ ምናልባት የሚደነግጡ ከሆነ የሚያስደነግጥዎትን ጉዳይ ላንሳልዎ። እርስዎና ቡድንዎ እናምነዋለን፣ እንከተለዋለን የምትሉትን እግዚአብሄርን~ኢየሱስ ክርስቶስን በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ክዳችሁታል። እሬቻ የተባለውን የቃልቻ፣ የአቴቴና የዊች~ክራፍት መንፈስ፣ የወንዝና የቄጤማ አምላክ የፍቅርና የአንድነት ባህል ብሎ የዳቦ ስም ሰጥቶ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝብ እንዲሰግድለት ባወጀው ጉባኤ ግምባር ቀደም ተካፋይ ሆናችኋል፤ በፊርማችሁ አጽድቃችኋል፤ በፊታውራሪዎችዎ አማካይነት የእግዚአብሄር አምላክነት ተክዶ የእሬቻ አምላክ እንዲወደስ፣ ምልአተ~ህዝቡ በጭፈራ እንዲያመልከው አስደርገዋል። ህዝብ ያሻውን የማምለክ መብት ቢኖረውና ቢያደርግ ከእግዚአብሄር ጋር እንዲፋረድ ይተዋል። እርስዎን ግን አመልከዋለሁ የሚሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም በላይ ተጠያቂ እንደሚያደርግዎት ልብ ብለዋል? ወይስ እሬቻን የተክለሰውነትዎ መገንቢያ የስልጣንዎ መለኪያ ማድረግ ከኢየሱስ በልጦብዎት ህሊናዎን ሸፈነብዎት!! ለእሬቻ አምላክ ሰግደዋልና። የእግዚአብሄርን ክብር በእሬቻ ለውጠዋልና። የእርሱን አምላክነት ክደው የእሬቻን ጣኦት አምልከው አስመልከዋልና። እግዚአብሄር በክብሩ እንደማይደራደር ጠፋዎትን? እርስዎም በሚያውቁት የእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ካሉት ክጉዳዩ ጋር ከተያያዙት አንዱን ብቻ ባስታውስዎት፦
“እግዚአብሄር አምላክህ እኔ ነኝ፤ ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ለራስህ ጣኦትን አታብጅ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤” (ዘጸአት 20፡2~5) ይላል።
እንግዲህ ይህን በተመለከተ የቀረዎት ስራ እንባዎን እያነቡ ወደ እግዚአብሄር በንስሃ መውደቅ ነው፤ እርሱ ይቅር ባይ አምላክ ነውና ይቅር ይልዎታል።
እርካብዎን ተውጣጥተው መንበርዎን በያዙ ማግስት ካንድ የሬድዮ ጣብያ ጋር ባደረግሁት ቃለመጠይቅ በእርስዎ መሪነት ከፍተኛ ተስፋ ማሳደሬን በበርካታ ምክንያቶች ገልጬ ነገር ግን አንድ ዋነኛ ፈተና እንደሚጠብቅዎት አስምሬ ነበር፤ እሱም በኦሮሞ ብሄረተኝነትና በኢትዮጵያዊ አገራዊነት መካከል ቆመው የሚፈተኑበት ፈተና ነበር። ስልጣን በያዙ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጀምሮ፣ ብዙዎች አንዴ መልአክ አንዴ ሙሴ እያሉ በጠሩዎት ጊዜ፣ ለውጥ የተባለው ነገር ሂደቱ እንደተደናቀፈ፣ ከበአለ~ሲመትዎ ንግግር ጀምሮ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያዊነት ትርክት ጨለማ ውስጥ እንደገባ፣ እርስዎም ተስፋ እንዳደረግሁብዎት እንዳልሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማገኛቸው ሰዎች ሃሳቤን በእርግጠኝነት ግን በሃዘን መንፈስ ገልጬላቸው እንደነበር የሚያውቁት ሰዎች ያስታውሳሉ። በየጊዜውም በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው አደጋ ምን እንደሆነ ምንም ብዥታ አልነበረኝም፤ አሁንም ምን ጊዜም ኢትዮጵያን በሚመለከት እምነቴ በእግዚአብሄር ላይ ብቻ ቢሆንም አገራችን ያገኘችውን እድል እንደገና እያጣች ከእስከዛሬው በባሰ ችግር ውስጥ እየገባች በመሆንዋ ግን ያሳዝነኛል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፈተናዎን መውደቅዎ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ያዩት እውነታ ሆኗል። ሆኖም ግን በፈተና የወደቀ እንደወደቀ እንደማይቀር ከሌላ ሳይሆን እኔ ራሴ ከፈተና ወድቄ ያልቀረሁበት፣ እንዲያውም በበለጠ ትምህርት የተነሳሁበት ምስክርነት ስላለኝ ወድቀው ይቀራሉ ብዬ ለመበየን የምዳዳበት የሞራል እሴት የለኝም። እንዲያውም ከእኔ ወድቆ~መነሳት እድል ይልቅ እጅጉን የሚበልጥ ምቹ ሁኔታ አለልዎትና ይበርቱ፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ የወንድምነቴን ምክር ልምከርዎት፦
1) ከሁሉም በፊት የሚያስፈልግዎት ጉዳይ ፈረንጆቹ Shift of Mind ወይም ከግሪኩ በተወረሰው ቃል Metanoia የሚባለው ታላቁ መጽሀፍ ደግሞ “የአእምሮ መታደስ” የሚለው ነው። የራስዎን ተክለ~ሰውነትና ተክለ~ስልጣን ከሚያስቡበት እይታ (Mind Set) ወጥተው የራሴ ጉዳይ የፈለገው ሊሆን ይችላል፣ ለህዝቡና ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን ላድርግ ወደሚለው እይታ ራስዎን ያሽጋግሩ። ይህን ማድረግ 180 ዲግሪ መዞርን ስለሚያስከትል ደፋር ውሳኔ ይጠይቃል፤ ግን ፈቃደኝነት ካለዎት ይቻላል።
2) ወደዚህ ውሳኔ እንዲደርሱ ሊረዳዎት የሚችለውን የብዙዎቹ ችግሮችዎ ምክንያት የሆነ አንድ ህመም ስላለ ከዚያ ይፈወሱ ዘንድ እጠይቅዎታለሁ፦ እሱም ራስዎን መካድ አለመቻልዎ ነው። አሁንም በኢየሱስ ክርስቶስ ቋንቋ ብነግርዎት ይበልጥ ይገባዎት ይመስለኛል፦
“ሊከተለኝ የሚፈልግ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየእለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው አለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ጥቅሙ ምንድነው?” (ሉቃስ 9፡23~25)።
ለግል ተክለሰውነትዎና የስልጣንዎ አለም ለሚያተርፍልዎ ትርፍ ከቶ አይጨነቁ፤ በቅድሚያ ለእግዚአብሄር ቀጥሎ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ትክክል ለሆነው ነገር ብቻ እስቲ ለመኖር ይጀምሩ፤ እግዚአብሄር እጅዎ ላይ ያስቀመጠው የእለት~ተእለት መስቀልዎ አሁን ይኸው ብቻ ነው። ከተክለሰውነትዎና ከስልጣን አለምዎ ይልቅ ነፍስዎን ቢያተርፉ አይሻልዎትምን?
3) ከኦሮሞ ብሄረተኝነት ጥላ ይውጡና የማንም ብሄረተኛነትም ቢሆን ሳይጎትትዎት ለኢትዮጵያ አገራዊነት ብቻ ይቁሙ። ይህን ቢያደርጉ የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር እንደሚጋጩ ግልጽ ነው፤ ግን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋጭተው የኢትዮጵያ አፍራሾችን ከሚያተርፉ ከኢትዮጵያ አፍራሾች ጋር ተጋጭተው ኢትዮጵያን ቢያተርፉ ለራስዎም ይሻልዎታል፣ ለህዝቡም የሚጠቅመው ይኸው ነው። መጀመሪያ አግኝተውት የነበረውን ድጋፍ ሊመልሱት የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ደግሞስ የዘውገኛ አጀንዳ መሳሪያ ከመሆን በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያን ብለው የሚመጣውን ቢጋፈጡ አይሻለዎትም? አንዳንድ ምርጫዎች የሚያሳምሙ ቢሆኑም ውጤታቸው ከእውነት ጋር ስለሚያስቆም ይመረጣሉ። ለዚህ ምርጫ የሚሆን ድፍረት የሚያስፈልግዎት ጊዜ አሁን ነው። የመጽሀፍ ቅዱሷን የአስቴርን ታሪክ ያስታውሱታል? መርዶክዮስ ለአስቴር የላከላት የመጨራሻ መልእክት እኮ የሚከተለውን ነው፦
“አንቺ በንጉስ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ህዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይመስልሽ፤ በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትይ፣ ለአይሁድ እርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግስት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?” (መጽሃፈ አስቴር 4፡13~14)።
እንደሚያውቁት አስቴር በዚህ የመርዶክዮስ ምክር ሰልፏን አስተካክላ አይሁድንም ራሷንም ከጥፋት ለማትረፍ ወሰነች፤ እግዚአብሄር ተጠቀመባት። እርስዎ ቤተመንግስት የገቡት ለዚህ ጊዜ እንዲጠቅሙ መሆኑን ማን ያውቃል? እርስዎ ከኢትዮጵያ አፍራሾች ጋር ቢተባበሩና ዝም ቢሉ እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ እርዳታና ትድግና ሌላ ሰው ለማስነሳት እንደማይገደው ይጠራጠራሉ? በዚያን ጊዜ ግን እርስዎና ቤትዎ ከጥፋት እንደማይድኑ እርግጠኛ ነዎት? እንዲሆኑ የተፈለገብዎትን ሳይሆኑ እየቀሩ ነውና ሌላው መርዶክዮስ ሆኜልዎት እንደሆነስ ማን ያውቃል??
4) ይመስልዎት ይሆናል እንጂ እርስዎ በራስዎ ብቻ ሁሉን ነገር አዋቂ አይደሉም፣ ማንም ቢሆን ሁሉ~አዋቂ ከቶ ሊሆን አይቻለውም። ስለዚህ ለሌሎች ሰዎችን ምክርና ተግሳጽ ጆሮዎትን ያዘንብሉ። እርስዎን ከመጥላት ወይም ለእርስዎ ክፉ ከመመኘት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ከመሳሳት፣ ተልእኮዎ እንዲሳካ ከመመኘት የሚሰነዘርን ምክርና ተግሳጽ ከልብዎ ያድምጡት፣ ይፈልጉትም። ይህን መሳዩን ምክርና ተግሳጽ ሊለግሱዎት እየሞከሩ በጆሮ ዳባነት፣ በንቀትና በለበጣ የመለሱዋቸው በርካታ ሰዎች፣ ወዳጆችዎ የነበሩ ሳይቀር አዝነው እንደተዎት ያውቃሉ? በአካባቢዎ ሳይጠሩዋቸው አቤት ሳይልኩዋቸው ወዴት የሚሉዎትን አሸርጋጆች ብቻ ሳይሆን ካልጠቀመ አይጠቅምም የሚሉዎትን፣ ሲሳሳቱ ተሳስተዋል የሚሉዎትን ይሰብስቡ። መልካም ምክር የሚያገኙት ከእነዚህኞቹ ነውና።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ! ጸሀይቱ ከመግባቷ በፊት በነዚህ ምክሮች ረዘም ያለ የጽሞና ጊዜ ይወስዱ ዘንድ በታላቅ አክብሮትና ትህትና እለምንዎታለሁ፤ ባለቤቴና አኔ እንደወትሮው ሁሉ በእንባ ጭምር እንጸልይልዎታለን።
እግዚአብሄር እርስዎንና ቤተሰብዎን ይባርክ!
ጥቅምት 2012 አ.ም. አዲስ አበባ