አዴፓ አብንና አምስቱ የአማራ ድርጅቶች አብረው ለመሥራት ተስማሙ
የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት አዴፓ፣ አብን እና የአምስቱ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥምረት የያዘው የአማራ ድርጅት፤ በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ተባለ፡፡
በአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ አዘጋጅነት፣ በአማራ ክልል እና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚቀሳቀሱት አዴፓ፣ አብን እና የአምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት “የአማራ ድርጅት” ከፍተኛ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
ፓርቲዎቹ ከውይይታቸው በኋላ የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ጥቅሞች ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ዛሬ ተሰምቷል:: በአማራ ክልል ብሎም በሀገሪቱ ሠላም፣ አንድነት እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበርም ለመሥራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት የአማራ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የሚደርስባቸውን በደል ለማስቆም እና መብትና ጥቅማቸዉ ለማስከበር ፓርቲዎቹ በጋራ ይሰራሉ ነው የተባለው::
ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ እና ሐረሪ ክልሎች፣ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰዉ የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ዉድመት የተሰማቸዉን ጥልቅ ሐዘን ፓርቲዎቹ ገልጸው ለተጎጅ ቤተሰቦችም መጽናናትን ከመመኘታቸው ባሻገር ለችግሩ ምንጭ የሆኑና በጥቃቱ የተሳተፉ በሙሉ በሕግ እንዲጠየቁ አሳስበዋል::
በአዲስ አበባ የሚገነቡት ከ20 ሺኅ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዛሬ ተጀመረ
ምክትል ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ መሀል የሚገነቡ ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዛሬ ጥቅምት 22 ቀን በይፋ ተጀምሯል።
ምክትል ከንቲባውን ጨምሮ፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ አካባቢዎች በተገኙበት የለገሃር አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደተጀመረም ታዝበናል።
ኢንጅነር ታከለ ኡማ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ፤ ቀደም ሲል በቤቶች ግንባታ የነበሩ ክፍተቶች እንዳማይኖሩ እና መንግሥት በቤቶች ግንባታ ከመቆጣጠርና ማስተዳደር ውጭ ሓላፊነት እንደማይኖረው ከመናገራቸው ባሻገር፤የከተማ አስተዳደሩ ከ150 ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገነባ ፣በግሉ ዘርፍ ደገሞ በርካታ ቤቶች ለማስገነባት መንግስት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
በቀጣይ በከተማ ነዋሪ የሚነሱ የቤት፣ የትራንስፖርት እና የስራ እድል ፈጠራ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባው ጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ከተማን ለመለወጥ እየተሰራ ያለውን ስራ የመዲናዋ ነዋሪዎች በጋራ በመቆም ሊደግፉ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
የለገሃር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በ4 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን 10 ብሎኮች እና 1 ሺህ 680 መኖሪያ ቤቶች ይኖሩታል:: ግንባታው በ10 ተቋራጮች የሚከናወን ሲሆን፥ ለ3 ሺህ ሰዎች ስራ እድል ይፈጥራል:: ከሂልተን ጀርባ በልማት ምክንያት የሚነሱ ዜጎች በለገሃሩ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚመደቡም ከንቲባው ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለሟሟላት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ሳይቶች ተጀምረው በግንባታ ላይ የሚገኙትን ቤቶች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እና በተያዘው በጀት ዓመትም 500 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የግንባታ አማራጮች ለማስገንባት እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በመልሶ ማልማት እና በአዳዲስ ፕሮጀክቶች በዘጠኙም ክፍለ ከተሞች በ69 ነጥብ 2 ሄክታርመሬት ከ20 ሺህ 504 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ የማስጀመሪያ ስነ ስዓት እየተካሄደ ነው። የቤቶቹ ግንባታ ወጪም በከተማ አስተዳደሩ እና በባንክ ብድር የሚሸፈን ይሆናል።በእቅድ ከተያዙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ስራ በ1 ሺህ 740 በጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ለ52 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል፡፡
ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በስተቀር በሌሎቹ ዘጠኙ ክፍለ ከተሞች በመልሶ ማልማት እና በአዳዲስ ፕሮጀክት የመሬት ዝግጅት ከወዲሁ የተደረገ ሲሆን፥ እነዚህ ቤቶች ሲጠናቀቁ ከ102 ሺህ 520 በላይ ነዋሪዎችን ያስተናግዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በሸገር የውሃ ስርጭት ተቋርጧል
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በአሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የውሃ ስርጭት መቋረጡ እየተነገረ ይገኛል፡
በአንዳንድ ምክንያቶች በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ባለው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በውሃ ምርት ፣ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እየፈጠረ መሆኑን የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣንም አረጋግጧል፡፡
ትላንት ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በተፈጠረ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት በአቃቂ ከርሰ ምድር የተወሰነ ክፍል ውሃ ማምረት እንዳልተቻለ ነው የተገለጸው፡፡
በዚሁ ምክንያት በአቃቂ ፣በቃሊቲ፣ በሳሪስ አቦ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ጎተራ፣ ቦሌ፣ ኦሎምፒያ፣ ስታዲየም፣ ለገሀር፣ ሜክሲኮ፣ ልደታ፣ ጦር ሀይሎች፣ መርካቶ (በከፊል)፣ ቀራኒዮ፣ ቤቴል፣ ዓለም ባንክ፣ አየር ጤና ፣በዘነበ ወርቅ፣ መካኒሳ፣ ካራ ቆሬ፣ በጀሞ፣ ለቡ፣ ሀና ማሪያም፣ ጎፋ እና ቄራ አካባቢዎች የውሃ ስርጭት ተቋረጧል፡፡
በድንገት የተከሰተውን ከፍተኛ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጥረት እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ያስታወቀ ሲሆን፤ በተጠቀሱት አከባቢዎች የሚኖሩ የኀብረተሰብ ክፍሎች በትዕግስት እንዲጠብቁትም መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በአ/አ ከስድስት ወር በላይ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች ሊወረሱ ነው
በአዲስ አበባ ከተማ ከስድስት ወር በላይ መሬት አጥረው የሚያስቀምጡ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት መሬት እንደሚወረስ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስታወቁ::
በአዲስ አበባ በዘጠኝ ክፍለ ከተማዎች የሚገነቡ ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ምክትል ከንቲባው ባስጀመሩበት ወቅት ነው ይህንን አዲስ አሠራር ይፋ ያደረጉት።
በዚህ ፕሮግራም ላይ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ሲናገሩ ባደረጉት ንግግር ከስድስት ወር በላይ በከተማዋ ያለምንም ግንባታ መሬት አጥሮ የሚያስቀምጥ ማንኛውም አካል መሬቱ እንደሚወረስበት ማረጋገጥ እፈልጋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል::
“ሀብት ዝም ብሎ የሚባክንበት ወቅት አልፏል” ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በእያንዳንዱ ቦታ በመንግሥት እና በባለሃብቶች ንብረትነት ፣ ግንባታ ሳይካሄድባቸው ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች በጥናት ተለይተው የተቀመጡ በመሆናቸው በቅርቡ ዕርምጃ መውሰድ እንደማጀመር ይፋ አድርገዋል።
ዛሬ ከንቲባው በአደባባይ ባረጋገጡት አዲስ መመሪያ መሠረት ግንባታ ሳይካሄድባቸው የተቀመጡት እነዚህ መሬቶች በአጭር ጊዜ ወደ መሬት ባንክ ይመለሳሉ።