በሰሞኑ ግጭት ከሞቱት አማሮች ኦሮሞዎች በዕጥፍ እንደሚበልጡ ዶ/ር ዐቢይ ተናገሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ አንድ ወደፊት ስንሄድ ሁለት ወደኋላ የሚመልሱንን ኃይሎች ማስቆም ይገባናል ብለዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በተከሰተው ግጭት የ86 ሰዎች ህይወት እንዳለፈና ከሟቾች መካከል 82 ወንድ፣ 4 ሴቶች መሆናቸውምን አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ በብሔር ሲለካ 50 ኦሮሞ፣ 20 አማራ፣ 8 ጋሞ፣ 2 ስልጤ፣ 1 ጉራጌ፣ 2 ሀዲያ እና አንድ አርጎባ ሲሆኑ፥ የአንዱ ሟች ብሄር እስካሁን አልታወቀም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በሃይማኖት በኩል ከሟቾቹ መካከልም 40 ክርስቲያን ሲሆኑ፥ 34 ሙስሊም እና 12 የሌላ እምነት ተከታዮች መሆናቸውንም አብራርተዋል::ከሟቾቹ መካከል 76 ሰዎች በእርስ በእርስ ግጭት፤ 10 ሰዎች ደግሞ በፀጥታ ሀይሎች ህይወታቸው ማለፉንም ገልፀዋል።
ይህ ክፉ ክስተት በኢትዮጵያ የግጭት እሳት ሲነሳ አንዱን ክፍል አቃጥሎ ሌላውን አሙቆ የሚያልፍ እንዳልሆነ ያሳየ ነው ያሉት ዐቢይ አሕመድ መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ሆደ ሰፊነቱን አብዝቶ ሲያስታምም ከርሟል ሲሉም ተሰምተዋል።
ከሀይልና ጉልበት ይልቅም፤ ትምህርት እና ምክክር ይሻላል ብሎ መታገሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ትእግሰቱ ፍርሃት፤ ማስታመሙ ድካም፣ የመሰላቸው ካሉ ግን ተሳስተዋል ካሉ በኋላ፤ አንዳንዶች እንዲማሩ ተብሎ ሰፊ ልብ እና ትክሻ ሲሰጣቸው አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተው የዜጎች ህይወት ለአደጋ የሚጋለጥበት ምክንያት መፈጠሩንም አመላክተዋል።
“ያለፉትን ስህተቶች ለማረም እየሰራን በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ህጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አግባብም አልሚ ሁሉ ስራውን፤ አጥፊ ሁሉ ደግሞ በጥፋቱ ልክ ተጠያቂ እየሆነ እንደሚሄድም አስታውቀዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት የሀገሪቱን ሰላም፣ ደህንነት እና አንድነት ለማስጠበቅ ሲል ህግና ስርዓትን እንዲያስከብር ደጋግመው መጠየቃቸውን በማንሳት፥ ጥያቄያቸው ተገቢ መሆኑን እና መንግስትም ህግ የሚፈቅድለትን ሁሉ ለማድረግ አቅምም፣ ዝግጁነትም፣ ብቃትም አለው ብለዋል።
የፍትህ አካላትም ለአጥፊዎች ትምህርት፤ ለተጎጂዎች ካሳ የሚሆን የተፋጠነ ፍትህ በማስፈን ፍትህን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀረቡት የለውጡ ፍሬ፤ ዋልታ ረገጥ የብሄር እና የእምነት ጫፍ ላይ ቆመው ችግሮችን የሚያባብሱ ወገኖችም አስተያየቶቻቸው እና መልእክቶቻቸው ተጨማሪ ዕልቂትና ጥፋት ከሚያመጣ ማናቸውም ተግባር እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። “ነገሩን ሁሉ በስሜትና በወገንተኝነት መለኪያ ብቻ ሳንመለከት፤ ከስሜት በላይ ሆነን የተጋረጠብንን አደጋ በብልሃት መቀልበስ እንድንችል የዘወትር ትብብራችሁ እንዳይለየን እጠይቃለሁ” ሲሉም በመግለጫቸው ተማጽነዋል::
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በዜጎች ደህንነት ላይ ያሳየው ደካማነት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች ፍትህ ካላገኙ አሁንም ዶክተር አብይ በሚጓዙበት የተልፈሰፈሰ አካሄድ የዜጎች ዋስትና ሊረጋገጥ እንደማይችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
“ጠባቂዬ ፈጣሪ ነው” ያለው እስክንድር የመንግሥትን ጥበቃ እንደማይፈልግ አስታወቀ
የአዲስ አበባ ባለደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ፣ ጋዜጠኛና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ የሆነው እስክንድር ነጋ ትላንት በበርካታ ወጣቶች ተከቦ እንደነበር አረጋግጧል። ትናንት ቅዳሜ ምሽት 1፡00 አካባቢ፤ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከፍ ብሎ የሚገኘው የባላደራው ቢሮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ጨርሰው ሲወጡ ነው የኦሮሚያ ተወላጆች የሆኑ የመንጋ አባላት በከበባ ጥቃት ሊፈጽሙ መሞከራቸውንም ለቢቢሲ ገልጿል::
ቁጥራቸው ከ10 በላይ የሚሆን ወጣቶች ከቢሮው ውጪ ደጃፍ ላይ ጠብቀው እርሱንና አራት የባልደራስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን በቅድሚያ ለመክበብ ሲሞክሩ እነሱ አልፈዋቸው ቢሄዱም በነጻነት ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሰዎች በከበባ መልክ ተከትለዋቸዋል። እንቅስቃሴያቸው አስጊ ስለነበር እነ እስክንድር ወደ ኋላ በመመለስ የተደራጁትን አካላት ፖሊስ ይዞ እንዲጠይቅላቸው ሙከራ ቢያደርጉም አንዱ ብቻ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋል እንደቻለ ታውቋል::
እኛ ላይ ከሚደርስብን የግድያ ዛቻ አንፃር ከበባው አስጊ ነበር የሚለው እስክንድር ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደዚህ ዓይነት ነገር ተፈጥሮ እንደማያውቅ ፣ ወጣቶቹ ብዛት ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር አደጋ ለማድረስ በጣም ቀላል እንደነበርና
ወጣቶቹ ጥቃት ለማድረስ የቦታ መረጣ ጉዳይ ነበሩ ሲል ክስተቱን አብራርቷል::
«በእኛ ድምዳሜ ለከበቡን ሰዎች ቦታው አመቺ አልነበረም፤ እኛም ተመለስን። ፊት ለፊታችን ጨለማ ነበር። ከጨለማው ወደኋላ ተመልሰን። እንደ አጋጣሚ አንዲት ፖሊስ ስትመጣ አገኘን። አጠራጣሪ ሁኔታ ስላለ ሰዎቹን እንዲያዙልን እንደምንፈልግ አመለክትን። ተጨማሪ ኃይል ፈልጋ ነበር። በዚያ መሃል ነው እንግዲህ ልጆቹ ተሰባስበው ከአካባቢው የሄዱት።” በማለት የሚናገረው የባላደራው ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ፤ ከአንድ ወጣት በቀር የተቀሩት በሚኒባስ እንዳመለጡ እና ግለሰቡን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት የፖሊስ አባልና ምክትል ሳጅን ሆኖ መገኘቱን አረጋግጧል።
«ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ቃል ሲሰጥ ነው ምክትል ሳጅን መሆኑን ያወቅነው ። መጀመሪያ ላይ በአካባቢው ምን ሲያደርግ እንደነበር ሲጠየቅ ተማሪ ነኝ ብሎ ነበር ፣በኋላ ፖሊስ ሆኖ ተገኝቷል። እኛ ቃል ሰጥተን ወደየቤታችን ሄደናል እሱ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ተደርጓል። ዛሬ ጠዋት ተመለሱ ተብለን ስንሄድ ነገ ኑ ተብለናል። ልጁ በዕስር ላይ ይሁን ወይም ለቀውት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም» ብሏል
በርካታ የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚደርሰው እስክንድር ነጋ ከመንግሥት በኩል ጥበቃ እንዲደረግለት ፈጽሞ እንደማይፈልግም በዚህ መልክ ተናግሯል:- ” እኔ ጥበቃ እንዲደረግልኝም አልፈልግም። የሚያስፈልገው አሁን በተያዘው ልጅ ላይ ጥብቅ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ፤ ፍትሃዊ የሆነ፤ ሳይንሳዊ የሆነ፤ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ልጁ እንዲመረመር ነው። በተለይ ከእርሱ ጋር አብረውት የነበሩት ልጆችን አፈላልጎ መያዝና ለምን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳደረጉ መጠየቅ ብሎም ጉዳዩን እስከ ሥር ድረስ ሄዶ መመርመር ነው የሚያስፈልገው። ይሄን ብቻ ነው እኔ ከመንግሥት የምፈልገው።»
እስክንድር ወጣቶቹ ተዘጋጅተውበት እና አጥንተው እንደመጡ ይናገራል። የዕለተ’ለት እንቅሰቃሴያችን ከግምት ውስጥ ገብቷል የሚል ጥርጣሬ እንዳለውም ጠቁሟል። «ሁልጊዜ በዚህ ሰዓት ነው የምንጨርሰው። ቅዳሜ ማታ ጨርሰን በእግራችን ነው የምንንቀሳቀሰው። ለምሳሌ እኔ ከጊዮርጊስ ተነስቼ ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር እስከ አራት ኪሎ ደረስ እሄዳለሁ። የተጠና ነው የምለው ለዚህ ነው። ለማናቸውም ዝርዝሩ በፖሊስ የሚረጋገጥ ነገር ነው።» ሲል የመንጋውን አመጣጥ አብራርቷል::
«ከእኛ ውጭ የሆኑ፤ በአካባቢው የነበሩ፤ ወጣቶቹ ሲመጡ እና እኛ ላይ ሲያደርጉ የነበረውን የተከታተሉ ሰዎችን ምስክር እንዲሆኑ ይዘን ነው የሄድነው። አስፈላጊ ስለሆነ ማለት ነው። ይሄንን መሠረት አድርጎ ከመንግሥት ትክክለኛ የሆነ ምርመራ አድርጎ እርምጃ እንዲወሰድ ነው። ምክንያቱም ከኃይል እርምጃ ኢትዮጵያ አታተርፍም። በኃይል የሚፈታ የፖለቲካ ጥያቄ የለም።» ያለው እስክንድር ነጋ ፤ “ምናልባት በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ተለቋል ካሉን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን የነበረውን ሁኔታ እናስረዳለን። ምስክሮች ይዘን ወደላይ አቤት እንላለን ብለን እናስባለን። በዚያም ደረጃ የማይፈታ ከሆነ ከዚያም ወደላይ ሄደን ማሳሰብ እንፈልጋለን። በመንግሥት ውስጥ ሁለት ሃሳብ አለ ብለን እናስባለን። ብጥብጥ የሚፈልግ ኃይልና ብጥብጥ የማይፈልግ ኃይል አለ። ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ጥግ ድረስ ሄደን አግባብ ያለው ምርመራ እንዲደረግ ነው የምንፈልገው። ይሄ ልጅ ንፁህ ከሆነ እንዲለቀቅ ነው የምንፈልገው። የግድ መታሠር አለበት የሚል አቋም የለንም።» ሲል ለትክክለኛ የፍትህ ስርዓት ተገዢ መሆኑን በጨዋነት አስታውቋል::
«.እኔ የሚጠብቀኝ እግዚአብሔር ነው ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ ባሻገር እኔ በግሌ ጥበቃ ይገባኛል ብዬ አላስብም። ጉዳዩ ከእኔ ጋር የተያያዘ አይደለም። የተነሳው ጥያቄ እኔ ኖርኩ አልኖርኩ የሚኖር ነው። በዲሞክራሲያዊ መንገድ እልባት እስካላገኘ ድረስ ማለት ነው። መኖር አልፈልግም ማለት ግን አይደለም» ታላቁ እስክንድር ነጋ፤«ለሚስቴ መኖር እፈልጋለሁ፤ ለልጄ መኖር እፈልጋለሁ። ኖሬም ደግሞ ለሕብረተሰቡ ገንቢ የሆነ አስተዋፅዖ ማድረግ እፈልጋለሁ። ጥበቃ ግን ይከብደኛል። ኅሊናዬም አይፈቅደውም። ካለው ዛቻ አኳያ፤ በተለይ ደግሞ ትላንት በተግባር ስላየነው አያሳስበኝም ማለት ግን አልችልም፤ ያሳስበኛል» ለቢቢሲ አቋሙን ይፋ አድርጓል::
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለኦነግ መረጃ ያቅብሉ እንደነበር ግንባሩ አስታወቀ
የቲም ለማ የለውጥ ቡድን በኢሕአዴግ ውስጥ የበላይነቱን መያዙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን የቻሉት ዐቢይ አህመድ ከ11 ዓመት በፊት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር የመረጃ ልውውጥ ግንኙነት እንደነበራቸው መናገሩ በርካቶችን እያወያየ ነው።
ከአርባ ዓመት በላይ የትጥቅ አድርጎ ምንም ውጤት ለማግኘትና አንድ ቀበሌ እንኳን ለማስተዳደር ያልቻለው የኦነግ ጦር የምዕራብ ዕዝ መሪ የነበረው ለገሰ ወጊ የተባለው ግለሰብ ላይ ሊፈጸም ታቅዶ ስለነበረው ጥቃት በተመለከተ ለኦነግ አመራር ዶ/ር ዐቢይ መረጃ አቀብለው እንደነበረ ግንባሩ ገልጿል።
ኦነግ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጥቃቱ ቀደም ብለው በግንባሩ የጦር መሪ ላይ ሊፈጸም ስለታቀደው ጥቃት መረጃ በውጪ ለሚገኙት አመራሮች መስጠታቸውን አረጋግጧል።
ለገሰ ወጊ የተገደለው ከ10 ዓመት በፊት የነበረ ሲሆን ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ በጊዜው ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መተላለፉ አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የ78 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን ጥቃትና ግጭት ለማረጋጋት ከህዝብ ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት፣ መቀመጫውን ኤርትራ አድርጎ ከነበረው ኦነግ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ጠቅሰው እንደነበርም የስብሰባው ተሳታፊዎች ይናገራሉ።
ረቡዕ ዕለት በሐረር ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ይህንን ጉዳይ የሚያመላክት ነገር አንስተው የነበረ ሲሆን ሐሙስ አምቦ ከተማ ውስጥ በተደረገው ተመሳሳይ ውይይት ላይ ደግሞ ስለ ለገሰ ወጊ አገዳደል ማንሳታቸውን የተለያዮ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው።
የኦነግ መግለጫ ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት መንግሥት በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀስ በነበረው የኦነግ ቡድን ላይ ዘመቻ ሊያካሂድ እንደነበረ መናገራቸውንም አመላክቷል።
አሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዐብይ አህመድ በወቅቱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለገሰ ወጊ የተባለውን የግንባሩ ጦር መሪን ለመግደል ክትትል እያደረጉ መሆኑን መረጃ እንደሰጡት ያመነው ኦነግ፤ ነገር ግን በወቅቱ በመረጃው መሰረት ለገሰ ወጊ ከጥቃቱ እራሱን እንዲያድን በአመራሩ ቢነገረውም፣ እሱ ግን የእራሱን ውሳኔ መውሰዱን በመግለጫው ላይ አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነጸነት ግንባር በመግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ወቅት እንዳደረጉት ዛሬ መንግሥታቸው ከግንባሩ ጋር ተቀራርቦ ከመስራት አንጻር ጉድለቶች አሉበት ብሏል
“ህዝቡ አሁን ያለውን መንግሥት ለኦሮሞ ፖለቲካ አዲስ ነው በሚል የሚያቀርበውን ትችት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ለኦነግ የሰጡትን መረጃ ለዚህ እንደምላሽ እየተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል” የሚለው ኦነግ፤ የግንባሩ ከፍተኛ አመራር ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ሚካኤል ቦረን ለዚህ መግለጫ መውጣት ሦስት ምክንያቶች እንዳሉ በሓላፊው በኩል ለቢቢሲ አስታውቋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በተደጋጋሚ የለገሰን ግድያና ከኦነግ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማንሳታቸው ለትግሉ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የሚያሳይ ቢሆንም፣ ሌላ የሚያመለክተው ነገር አለው የሚሉት አቶ ሚካኤል “ለለገሰ መገደል በእኛ በኩል ጉድለት እንዳለ ለማስመሰልና አላስፈላጊ ጥርጣሬ ኀብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጥር ይችላል” የሚል ዕምነት እንዳሳደረባቸው ይጠቁማሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ በማንሳታቸው ደስተኛ የሆነ እንደማይመስል የአቶ ሚካኤል ቦረን ንግግር በግልጽ አሳይቷል። “ይህን ጉዳይ በተደጋጋሚ ማንሳታቸው ለምን አስፈለገ? ህዝቡ እንዳይሳሳትም የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ለማስቀመጥ ነው አሁን መግለጫውን ያወጣነው” ይላሉ።
አቶ ሚካኤል አክለውም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ስለለገሰ ብቻ ያነሳሉ?” በማለት ከመጠየቃቸው ባሻገር “አገር የሚያስተዳድር መንግሥት ለረጅም ዓመታት በግንባሩ አባላት ላይ ጥቃት ሲያካሂድ እንደቆየና አሁንም በዚህ ወቅት ጥቃቱ እንዳልቆመ” ይገልጻሉ።
“ከዚህ በፊት ለገሰን በተመለከተ ስላደረጉት ነገር ከሚናገሩ ይልቅ ዛሬ ስልጣን በእጃቸው እያለና የኦነግ አመራር አዲስ አበባ ውስጥ ባለበት ጊዜ፤ ዛሬ ከዚያ የበለጠ መስራት ይቻላል” ሲሉም ወቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ ላይ ስለተጠቀሰው ጉዳይ እስካሁን በይፋ የሰጠው አንዳችም መግለጫ የለም።
አምቦ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተቃወሙት ከሌላ ከተሞች ተጭነው የመጡ መሆናቸውን ታዬ ደንደአ ገለጹ
በሕወሓት መራሹ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የታሰረውና ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመበት ታዬ ደንደአ ከሁሉም የኦሮሞ ማኅበረሰብ በላቀ የአምቦ ሕዝብ አምባገነኑን ስርዓት ለመጣል ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን አስታወቀ::
ለተገኘው ለውጥም ሆነ ለነበረው ከፍተኛ የሕዝብ ትግል የአምቦ ነዋሪ ልዮ ምልክትና ለሌሎች መነሳሳት ተምሳሌት እንደነበር የተናገረው የኦዲፒ ከፍተኛ አመራር የሆነው ታዬ ደንድአ ይህንን ዕውነታ በመቀልበስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በከተማዋ ነዋሪ ጥላቻ ለማስመሰል የሚሠሩ ወገኖች በኦዴፓ ውስጥም ሆነ በውጭ መኖራቸውን አረጋግጠዋል::
ሰሞኑን በከተማዋ የነበረውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እነዚህ ኃይሎች ከሌላ ቦታ ሰዎችን በማምጣት ሽብር ለመፍጠር መሞከራቸውን የገለጹት ታዬ ደንደአ ሀቁ የአምቦ ነዋሪና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም መልካምና የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን በፌስ ቡክ ገጹ አስታውቋል::
|| ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ ||
ኃይሌ ገብረስላሴ በግፍ ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂ ከጃዋርና መንጋዎቹ ይልቅ ፌስ ቡክ ነው አለ
አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ በፌስቡክ ላይ የተሰራጩ ሐሰተኛ ዜናዎች ከሳምንት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ ለ78 ሰዎች ሞት ሰበብ ለሆነው ግጭትና ጥቃት ምክንያት ናቸው ሲል የችግሩን ጠንሳሽና በአስነዋሪው ግድያ ላይ የተሳተፉ መንጋዎችን የሚከላከል አስተያየት ሰጠ::
ችግሩ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ተጽእኖና ተደማጭነት ያለው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተርና አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ የመንግሥት ባለስልጣናት የተመደቡለትን የግል ጠባቂዎቹን በማንሳት ህይወቱን ለአደጋ ለማጋለጥ ሞክረዋል በማለት ያሰራጨውን የማህበራዊ መገናኛ መድረክ መልዕክት ተከትሎ መሆኑን ቢያምንም የችግሩን ምንጭና አመጹ ከተነሳ በኋላ በኦ ኤም ኤን ቴሌቪዥኑ ጭምር እሳቱን ሲያ ቀጣጥል የነበረውን ጃዋር መሐመድና ተከታዮቹን ከመተቸት ይልቅ ፌስ ቡክን ወቅሷል::
መንግሥትና የተለያዩ ወገኖች ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው ችግር ሃይማኖታዊና የብሔር ገጽታ እንደነበረው ማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆኑ የሚያምነው ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዳንድ መልዕክቶችን ከገጹ ላይ እንዲነሱ ካላደረገ ፌስቡክን ሊከስ እንደሚችል ለቢቢሲ መግለጹን ተመልክተናል ።
ሰማኒያ ለሚጠጉ ሰዎች መገደል ዋነኛ ምክንያቱ “ፌስቡክ ነበር ብዬ አምናለሁ” ያለው ኃይሌ የወቀሳ ጣቱን በፌስ ቡክ ላይ መቀሰሩን እና በአደባባይ ከታየው ዕውነታ ማፈንገጡን ተከትሎ በርካቶች እየተቹት ይገኛሉ።
ምስሎቹ የሚያሳዩት በኢትዮጽያዊያን የተፈጸሙ ድርጊቶች አይደሉም ብሎ የሚያምነው ኃይሌ”ወገኖቼን አውቃቸዋለሁ፤ እንዲህ አይነት አስቀያሚ ድርጊቶችን አይፈጽሙም” ሲልም የአደባባይ ዕውነታን ለመካድ የቀረበ አስተያየት ሰንዝሯል።
ከሩጫው ባሻገር ስኬታማ የንግድ ሰው የሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ በሩዋንዳ የተከሰተው የዘር ፍጅት ካጋጠመ ረጅም ጊዜ አለመሆኑን በማስታወስ “ኢትዮጵያ ልትጠነቀቅ ይገባል” በማለት አሳስቦ፤ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ በኋላ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለማሳየት ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን የገቡበትን ችግር ለአብነት ጠቅሷል።