ኢትዮጵያ ነገ || በቅርቡ የተገደለውና የቀድሞው የአይ ኤስ መሪ አቡ ባካር አል ባግዳዲ እህት በሰሜናዊ ሶርያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሏን የቱርክ ባለ ሥልጣኖች ገለጹ:: የ65 ዓመቷ ራስሚያ አዋድ የተያዘችው ሰኞ ዕለት “አዛዝ” በተባለ ከተማ በተካሄደ ከፍተኛ አሰሳ እንደሆነም ታውቋል ።
በአሰሳው ውጤታማ የሆኑት የቱርክ ባለሥልጣኞች ከአል ባግዳዲ እህት ስለ አይ ኤስ ጠቃሚ መረጃ ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ናቸው::ራስሚያን በመጠቀም ስለ አይ ኤስ ውስጣዊ አሠራር ባለሥልጣናቱ ማቀዳቸውን ሮይተርስ ምንጮቼ ያላቸውን የቱርክ ባለሥልጣናት ጠቅሶ ዘግቧል።
አል ባግዳዲ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በሚገኘው መኖሪያው በአሜሪካ ልዩ ኃይሎች መከበቡን ተከትሎ ራሱን ማጥፋቱ አይዘነጋም። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአልባግዳዲ ሞት መኩራራታቸውን ያመላከቱት የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች ፣ አይ ኤስ በሶሪያና በሌሎችም አገሮች አሁንም የጸጥታ ስጋት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተው ይከራከራሉ።
የታሠረችውን ሴት ማንነት ለማጣራት በተደረገው ጥረትናበኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ መሰረት አልባግዳዲ አምስት ወንድሞችና በርካታ እህቶች ያሉት መሆኑ ታውቋል:: ከነዚህ ምን ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ግን እስካሁን ግልጽ የሆነመረጃ የለም ተብሏል።
ራስሚያ አዋድ የተሰኘችው ሴት የተያዘችው ከአምስት ልጆቿና ከልጇ ባለቤት ጋር በምትኖርበት አካባቢ እንደሆነ የዘገበው አሶሽየትድ ፕሬስ ፤ ከጽንፈኛ ቡድን ጋር አብራ እንደምትሠራ ስለሚጠረጠር ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነም አስታውቋል::ተንታኞች ከራስሚያ ምን ያህል ጠቃሚ መረጃ እንደሚገኝ እንዲሁም ከአል ባግዳዲ ጋር ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፈችም ግልጽ መረጃ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በሀድሰን ኢንስቲትዮት የሚገኙ የሽብርተኝነት ተመራማሪ ማይክ ፕሬገንት፤ “በቅርብ ጊዜ ሊወሰዱ የታሰቡ ጥቃቶች የምታውቅ አይመስለኝም። ሆኖም አል ባግዳዲ ይተማመንባቸው የነበሩ ሕገ ወጥ ዝውውር የሚካሄድባቸውን መስመሮችን እና ታማኙ የነበሩ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል።” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እሷና ቤተሰቦቿን ከቦታ ቦታ በሚስጥር ስለሚያዘዋውሩ የአል ባግዳዲ ተባባሪዎችን በተመለከተ መረጃ ሊገኝ እንደሚችልም ተመራማሪው ተናግረዋል። መጃው ለአሜሪካ የስለላ ሠራተኞች እና አጋሮቻቸው የአይ ኤስን የውስጥ መስመር በግልጽ የሚያሳይ ነው ተብሎ ይጠበቃል።።