የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ አፍሪካ ጦር ዕዝ አዛዥ ጋር በመከላከያ ግንባታ ዙሪያ ተወያዮ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዣዥ ከሆኑት ጀነራል ስቴፈን ታውንሴንድ ጋር በዛሬው ዕለት ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡

አሜሪካዊው ጀነራል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሳምንታት በፊት ባገኙት ታሪካዊው የኖቤል ሰላም ሽልማት ደስታቸውን ከመግለጻቸው ባሻገር ሽልማቱለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው አበረታች ድል መሆኑን መስክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በአሜሪያካ መካከል ከወታደራዊ የጦር ኃይል አንጻር የነበረውን የረዥም ጊዜ የትብብር ግንኙነት አስመልክቶ የተወያዮት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ጀነራል ስቴፈን የሀገሪቱን ጦር ሠራዊት አቅም ለመገንባት የአጭር እና የረዥም ጊዜ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ዐቢይ አህመድ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እየተከናወነ የሚገኘውን የተሃድሶ ሥራ ከማስቀጠል አንጻር የተለያዩ ሥራዎች የተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሠራዊቱን ብቃት ያለው ባለሙያ ለማድረግ፣ ለየትኛውም አካል እና የፖለቲካ ተቋም ምንም ዓይነት አድልዎ ሳያሳይ ፣ ወገናዊነቱን ለዴሞክራሲ ብቻ ያደረገ እንዲሆን ሥራዎች በጥልቀት እየተተገበሩ እንደሆነ መግለጻቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ወቅታዊ መረጃ ለማወቅ ችለናል::

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብትን ለማስከበር የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ከሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር ተወያይተዋል ተባለ፡፡

በአዲሱ የሥራ ቅጥር የመጡትና የሚመጡትን እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሳዑዲ አረቢያ ሢሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብትና ጥቅም በሚከበርበት ዙሪያ ሚኒስትሯ ከሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ መወያየታቸው ተገልጿል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች፣የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እና የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች በተመለከተ በየጊዜው ውይይት በማድረግ ደረጃ በደረጃ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በድኅረ ገጹ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በፊት የታዩ የደመወዝ መከልከል እና ተዛማጅየመብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ የሚያስችሉ መደላድሎች እየተመቻቹ  ይገኛሉ ያለው መረጃ  በተጨማሪ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ሁለቱ ሀገራት በጋራ በትብብር ለመሥራት በሚያስችሏቸው ወሳኝ ነጥቦች ላይ ቅድመ ስምምነት ላይ እንደደረሱም ተገልጿል::

ቦይንግ 787  አውሮፕላን በጉዞ ላይ አደጋ ቢደርስ ተሳፋሪዎች ኦክሲጅን እንደማያገኙ ተጋለጠ

የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በጉዞ ላይ ሳለ አደጋ ቢደርስ ተጓዦች ኦክስጅን ላያገኙ እንደሚችሉ አንድ የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ ማጋለጡ ተሰማ:: አውሮፕላኑ ውስጥ በአደጋ ጊዜ ኦክስጅን የሚያሰራጨው መሣሪያ የተበላሸ ወይም የማይሠራ መሆኑን እንዳሳየው ይፋ ያደረገው ጆን ባርኔት የተባለ ግለሰብ ነው።

የቀድሞ የግዙፉ ተቋም ባልደረባ ባደረገው ሰፊ ጥናት ተንተርሶ በአንድ የቦይንግ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ሆን ተብሎ የማይሠሩ መሣሪያዎች እንደሚገጠሙም አመላክቷል:: የጆን ባርኔትን ክስ ያጣጣለ መግለጫ በፍጥነት የሰጠው ቦይንግ ፣ ሁሉም አውሮፕላኖቹ በጥራት እንደተሠሩ እና በደህንነት ረገድም አስተማማኝ እንደሆኑ ናቸው ብሏል። የድርጅቱ የቀድሞ የጥራት ተቆጣጣሪ ኢንጂነር ጆን፤ በጤና እክል ምክንያት ቦይንግን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ለ32 ዓመታት መሥራቱን እየወጡ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አረጋግጠዋል::

ቦይንግ በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ትችት እያስተናገደ ነው:: 787 ድሪም ላይነር በመላው ዓለም ረዥም ርቀት በመጓዝ የሚታወቅ አውሮፕላን ሲሆን ካምፓኒው ይህን አውሮፕላን ለተለያዩ አየር መንገዶች ሸጦት የሀብት መጠኑን ማግዘፍ ችሏል።

ባለሙያዋ ጆን ባርኔት አውሮፕላኑን ለማምረት ጥድፊያ ስለነበር ፣ ለጥራቱ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ቢልምቦይንግ በበኩሉ ይህ መረጃ ስህተት እንደሆነና ድርጅቱ ጥራት ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑን አስታውቋል።

ምስጢር አጋላጩ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2016 ላይ ለቢቢሲ አደጋ ሲከሰት ኦክስጅን የሚያሰራጨው መሣሪያው ላይ ችግር እንዳስተዋለና ይህ መሣሪያ በአግባቡ ካልሠራ፤ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ሕይወት አደጋ ውስጥ ይወድቃል ሲል አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር።

አውሮፕላኑ በ35,000 ጫማ ከፍታ እየበረረ ከሆነ እና የኦክስጅን ማሰራጫ መሣሪያው ካልሠራ፤ ተሳፋሪዎች በአንድ ደቂቃ ራሳቸውን እንደሚስቱ ፣ በ40,000 ጫማ ከፍታ ደግሞ በ20 ሰከንድ ራሳቸውን ከመሳታቸው ባሻገርይህ ሞት ወይም የአዕምሮ ጉዳት ሊያስከትልም ይችላል በመነገር ላይ ነው።

ግለሰቡ 300 የኦክስጅን ማሰራጫዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ፣ 75ቱ በተገቢው ሁኔታ እንደማይሠሩ ማረጋገጡን ይናገራል። ጉዳዩ በጥልቅ እንዲፈተሽ ለማድረግ ቢሞክርም የቦይንግ አመራሮች እንዳስቆሙትም አጋልጧል:: በ2017 ለአሜሪካው የበረራ ተቆጣጣሪ ኤፍኤኤ ችግሩን ቢያሳውቅም አንዳችም እርምጃ አልተወሰደም ብሏል። ኤፍኤኤ ግን በወቅቱ ቦይንግ ይህንን ጉዳይ እየፈተሸ መሆኑን ተናግሯል።

2017 ላይ ኦክስጅን በአግባቡ የማያስተላልፉ መሣሪያዎች ከአገልግሎት ውጪ መደረጋቸውን ያስታወሰው ቦይንግከእያንዳንዱ ተሳፋሪ ወንበር በላይ የሚገኘው የኦክስጅን ማስተላለፊያ በተደጋጋሚ መሞከሩንም ገልጿል።

ጆን ችግሮቹን ሲያጋልጥ፤ ቦይንግ በአንጻሩ የጆን ሙያዊ ታማኝነት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ በማድረጉ፤ ጆን ቦይንግ ላይ ክስ መስርቷል። ካምፓኒው በበኩሉ ሠራተኞቹ ማንኛውንም አይነት አስተያየትና ቅሬታ ለድርጅቱ እንዲያሳውቁ እንደሚያበረታታ እና አስፈላጊውን ምርመራ እንደሚያካሂድም አሳውቋል። ቦይንግ ውስጥ ስላለው አሠራር ያጋለጠ ሠራተኛ ጆን ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ አራት የቦይንግ አራት ሠራተኞች ለኤፍኤኤ ጥቆማ አቅርበው ነበር ።

በቦይንግ 737 ማክስ ግንባታ ከተሳተፉ የቀድሞ ሠራተኞች አንዱ የሆነው አዳም ዲክሰን፤ ቦይንግ ውስጥ በፍጥነት በርካታ ምርቶች እንዲገባደዱ ጫና እንደሚደረግ መረጃ ሰጥቷል:: ባለፈው ወር የዴሞክራቶች የኮንግረስ አባል አልቢኖ ሲረስ፤ ከ737 ማክስ ዋና ሓላፊዎች አንዱ የላኩትን ኢሜል በማጣቀስ፤ የቦይንግ ሠራተኞች ከመጠን በላይ እንደሚሠሩ ከመናገራቸው ባሻገር ፣ ቤተሰባቸው በቦይንግ ሊሳፈሩ ሲሉ ጥርጣሬ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።

አማራ ክልል 20 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 600 ባለሀብቶች ፍቃድ ሰጠ

ባለፉት ሦስት ወራት ወደ 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ካፒታል ላስመዘገቡ 600 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ቢሮ የፕሮሞሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይኼነው አለም እንደገለጹት በክልሉ በ2012 በጀት አመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት፣ በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ 554 ባለሃብቶች የኢንቨስትመት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ600 ባለሀብቶች ፍቃዱ መሰጠት ችሏል። አፈጻጸሙ ከመቶ ፐርሰንት በላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ።

በሩብ ዓመቱ ወይም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ቢሮው 4 ቢሊየን 799 ሚሊየን ብር ካፒታል ለሚያስመዘግቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ባለሃብቶቹ ከተያዘው ዕቅድ በላይ 19 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት ፈቃድ ከወሰዱ 600 ባለሃብቶች ውስጥ 124 በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ 21 በጨርቃ ጨርቅ፣ 57 በቱሪዝም፣ 52 በኬሚካል ማምረት፣ 87 በእንጨትና ብረታብረት፣ 57 በግብርና ዘርፍ እና ቀሪዎቹ ደግሞ በኮንስትራክሽን፣ አበባ ልማት እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሠማራት ፈቃድ ወስደዋል ነው የተባለው::

ባለሀብቶቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል መባሉንም ከደረሰን ዜና መገንዘብ ችለናል::

ሀያት ሆስፒታልን ከኦሮሞው ቢልየነር  ዲንቁ ደያሳ ጋር ያዋሃዱት ባለቤቶች ተቀጡ

የሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል የቀድሞ  ባለቤቶች የአክሲዮን ድርሻቸውን ለሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ባለቤት  ድንቁ ደያሳና ወላጅ እናታቸው ዳንሳ ጉርሙ   ለባለሥልጣኑ ሳያሳውቁ መሸጣቸው ሕገ ወጥ ውሕደት ነው በሚል ጥፋተኛ  ተብለዋል::የሸማቾች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን  አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው ውሳኔውን ያሳለፈው::

የባለሥልጣኑ ዐቃቤአን ሕጎች የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደሩ ችሎት ተከሳሾቹን በነጻ ማሰናበቱ  አግባብ አይደለም በሚል ያቀረበውን አቤቱታ የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ ማንኛውም ነጋዴ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት በሚፈጸምበት ወቅት ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ይገባዋል ፣ የስር ፍርድ ቤቱ ሽያጭ በድርጅቶች መካከል የተደረገ ሲሆን ብቻ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ያስፈልጋል በሚል የሰጠው ውሳኔም አግባብ አይደለም በማለት ሽሮታል::

የሆስፒታሉ የቀድሞ ባለቤቶች መካከል አባትና ልጅ የሆኑት ኢብራሂም ናኦድ እና አሕመድ ኢብራሂም ድርሻቸውን ለመሸጥ በጠቅላላ ጉባዔው የወሰኑት ባለፈው ዓመት ነበር:: የኦሮሞ ተወላጁ  ታዋቂው ቢሊየነር  ዲንቁ ደያሳ ወላጅ እናት በሆስፒታሉ ላይ ካላቸው 95 ሚሊዮን ብር በላይ የአክሲዮን ድርሻ በገዙበት ወቅት ለባለሥልጣኑ  ነበረባቸው ሲል ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ ሰጥቷል::

ተከሳሾች በበኩላቸው “ያደረግነው ግብይት ውህደት ሊባል አይችልም፣ ለዚህም ምክንያቱም ግብይቱ የተፈጸመው በግለሰቦች መካከል እንጂ በድርጅቶች መሀል አይደለም” በሚል ተከራክረዋል:: የተደረገው የአክሲዮን ግብይት በሁለት ነጋዴዎች መካከል እንጂ በድርጅቶች መሀል አይደለም በማለት ለባለሥልጣኑ የማሳወቅ ግዴታ እንደሌለባቸው በመግለጽም ተሟግተዋል::

ክሱን የተመለከተው የባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ክርክሩን ካደመጠ በኋላ  የአቃቤ ሕግ ይግባኝን በመቀበል የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን  በዚህም መሠረት ከሆስፒታሉ የ2011 ዓመታዊ ገቢ ላይ አምስት በመቶ የገንዘብ መቀጮ እና የውህደት ድርጊቱም እንዲቆም ወስኗል:: ከዚህ በተጨማሪ በግለሰቦቹ መካከል የተደረገው አክሲዮን ግብይት እንደ ውህደት የሚቆጠር ነው ሲል ብይን ሰጥቷል::

የኢትዮጵያው ፎርቹን ጋዜጣ በ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል አገልግሎቱን ሊያሰፋ ነው

ከ20 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ በኅትመት መገናኛ ብዙኅን ዘርፍ ከቆዮ ት በጣሚዲያዎች መካከል አንዱ የሆነው ፎርቹን ጋዜጣ ለ10 ዓመት የሚቆይ የተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ካፒታሉን ወደ 40 ሚሊዮን ብር ሊያሳድግ መሆኑ ተሰማ::

የፎርቹን ጋዜጣ አሳታሚ የኢንዲፔንደንት ኒውስ ኤንድ ሚዲያ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል  ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ተቋሙን የማሻሻል ጥናት ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል:: ” ያለፉትን ሃያ ዓመታት ስንከተላቸው የቆዮት የኅትመት የመገናኛ ብዙኃን ሥራ ተምሳሌቶች ከቴክኖሎጂ መሻሻል ጋር አብሮ መዝለቅ የማያስችል በመሆኑ ይዘት ፣ ተደራሽነትና ብዝኅነትን ለማካተት የሚያስችል የኅትመት ሚዲያ ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቀርጸናል” ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል::

ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዮት መረጃዎች ይዘታቸውን ጠብቀው በአጭር ምስልና ድምጽ በምስል እንዲሁም በድምጽ ብቻ በማድረግ አንባቢዎቻቸውን በቀላል መልኩ በሚይዙት ተንቃሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካኝነት በኅትመት ሥራዎቻቸው የሚያካትቷቸውን ይዘቶች ሳይለቁ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችን ይከውናሉ::

ፎርቹን ጋዜጣም ይሄንን በመከተል የኅትመት ስርጭትን ብቻ የሚያከናውን ብቻ ሳይሆን የይዘት ባለቤት መሆኑን ከግምት ውስጥ በመክተት  ያለውን ይዘት የተለያየ የቪዲዮ ሥራዎችን ፣ አጫጭር የሬዲዮ ድምጾችን (ፖድካስት) እንዲሁም የጋዜጣ ስርጭቱን ሳያቋርጥ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው ተብሏል::

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአሳታሚነት ሚና ወደ ይዘት ባለቤትነት በመቀየር በቋንቋ፣ በይዘትና ተደራሽነት መሄድ የሚያስችሉ አካሄዶችን በመፍጠር መሥራት የሚያስችለውን አካሄድ እንደሚከተል ነው የድርጅቱ ባለቤት የገለጹት::

“ይህ ሒደት የችሎታና የዐቅም ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሰማኒያ የሚሆኑ ሰዎችን እናሠለጥናለን” የሚሉት ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ሙያተኞቹ ሪፖርተሮች፣ ምስል ፈጣሪዎች፣ የመተግበሪያ ባለሙያዎች ፣ የገበያ ጥናት እና የአስተዳደር ባለሙያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል::

በእንግሊዘኛ ብቻ ተደራሽ የነበረውን ኅትመት በአዲሱ ስትራቴጂ መሠረት ኦሮሚኛ ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ ቋንቋዎችን አካታች ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ያመላከቱት የፎርቹን ዳይሬክተር  የሚዲያ ተቋሙ ለመጀመር የሚያስፈልገው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርሰውን ሀብት እስካሁን ባለው ካፒታል ተቋሙ ማድረግ ስለማይችል 70 በመቶ የሚሆነውን ሀብት የማፈላለግ ሥራውን ከኅብረተሰቡ ለማግኘት እንደሚሠራም ይፋ አድርገዋል::

የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች የውጭ ንግድ በ150 ሚሊዮን ብር አሽቆለቆለ

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዮት በ2012 ዓ.ም ሩብ በጀት ዓመቱ ውስጥ መሰረታዊ የግንባታ ብረታ ብረት ምርቶችን በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ 10 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡ ታወቀ::

በነዚህ ሦስት ወራት በውጪ ንግዱ የተሳተፉ የዘርፉ ኩባንያዎች ከ10 በላይ ሲሆኑ ለምርቶች የገበያ መዳረሻ የአፍሪካ የአውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ 20 ሀገራት ነበሩ ተብሏል::

የሩብ ዓመት ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ150 ሚሊዮን ብር ወይም የአምስት ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ለዚህም ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የኃይል መቆራረጥና ማነስ በምክንያትነት ቀርበዋል::

በከፍተኛ መጠን ከውጭ የሚገባውን ያለቀለት ብረታ ብረት እና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ዘርፉ ሚናው ከፍ ያለ ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ግን ምርቶቹን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በ2012 ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን የኢንስቲትዮቱ ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ፊጤ በቀለ ይናገራሉ::

የውጪ ምንዛሬ ዕጥረቱም ፋብሪካዎች ከማምረት አቅማቸው በታች እንዲሠሩ ማድረጉ ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን ጥቅም ከማሳጣቱም በላይ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር መንስዔ መሆኑ ተጠቅሷል::

ንግድ ባንክ ሠራተኞቹ ሥራ ላይ ሆነው ስልክ እንዳይጠቀሙ ከለከለ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ30 ሺኅ የሚልቁ ሠራተኞቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ የደንበኛ አገልግሎት የሚሰጡ የድርጅቱ ሠራተኞች በሥራ ሰዓት የስልክ ጥሪን ጨምሮ የማኅበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች የሞባይል ስልክ አገልግሎቶችን እንዳይጠቀሙ ከለከለ::

በሲስተም መጨናነቅ ምክንያት እና የኤቲኤም ማሽኖች በአግባቡ ባለመሥራታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞቹ ቅሬታ እየጠነከረ የመጣበት ባንኩ በስትራቴጂክና ኢኖቬሽን ክፍሉ አማካይነት አጠናሁ ባለው የዳሰሳ ጥናት መሠረት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ከአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል::

ለዚህ ችግር መንስኤ በምክንያትነት ከተቀመጡ ነጥቦች መሀል የደንበኞች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ዋነኛው ሆኖ በመገኘቱ  የውስጥ ዕርምጃው አስፈላጊ እንደሆነ በማስታወሻው ላይ በግልጽ አስፍሯል::

“አጠቃላይ ስር ነቀል ለውጥ እስኪደረግ ድረስ አገልግሎት ሰጪዎች የሞባይል ስልኮቻችሁን በሥራ ሰዓት ከመጠቀም ተቆጠቡ ” በማለት ተከታይ ዕርምጃ ዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስታውቋል::

መመሪያውን ተላልፎ የተገኘም ሠራተኛ በቅርብ ሓላፊዎች አማካይነት አስፈላጊው አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድበት የውስጥ ማስታወሻው ይገልጻል:: ይሁን እንጂ የቀጥቱ ምንነት በቀጥታና በግልጽ አልሰፈረም::

LEAVE A REPLY