በመጥረቢያ አንገቴ፣ ተቀልቶ ከሚወድቅ
ጥርሴ በመዶሻ፣ ተወቅጦ ከሚደቅ፣
ራሴ በቋጥኝ፣ ከሚፈጠፈጥ
እሳት ከሚያጋየኝ፣ በጎጆዬ ውስጥ፣
በሜንጫ፣ ገጀራ፣ ከምከተከት
ነፍስ ከማያውቁት፣ ከልጆቼ ፊት
ሞትን እያየሁት፣ ብዙእጥፍ ከምሞት፣
መንገድ ለመንገድ፣ ከሚጎተት በድኔ
ፈርጦ ከሚወጣ፣ ከአፎቱ ዓይኔ፣
ደሜ ቦይ ከሚቀድ፣ ባፌ ተደፍቼ
“በለው” እንጂ “አይዞህ”፣ የሚል ሰው አጥቼ፣
አርደው በቆርቆሮ፣ የትም ከሚጥሉኝ
ይበሉኝ ይመስል፣ ከሚዘለዝሉኝ
ሞት እንኳ ጨክኖ፣ ከሚዘገይብኝ፣
ቀለብ ከሚያረጉኝ፣ እንዳህያ ሬሳ
ላነር፣ ለቀበሮ፣ ለጅብ፣ ለጥንብ አንሳ፣
እጆቼን ዘርግቼ፣ ዓይኔን አንጋጥጬ
ሃፍረቴንም ሽጬ
የምለምንህ፣ አንት የኔ ፈጣሪ
እንድትሰጠኝ ነው፣ ጨካኝ ያገር መሪ!
ግን፣ እኩል የሚያሥር፣ እኩል የሚገድል
ሽባ የሚያደርግ፣ የሁሉን ዘር እኩል
እኩል ዓይን አውጥቶ፣ እኩል የሚያውር
እኩል ሟጦ፣ ዘርፎ፣ እርቃን የሚያስቀር፣
ወዳታች ዘቅዝቆ፣ እኩል የሚገርፍ
እኩል በኤሌትሪክ፣ የሚያንዘፈዝፍ
እኩል የሁሉን ጥፍር፣ የሚነቅል በፒንሳ
እኩል የሚያኮላሽ፣ ሳያባልጥ ጎሣ፣
በወንድ ልጅ ብልት፣ አንጠልጥሎ ኮዳ
እኩል የሚያስገፋ፣ የሥር ቤት ግድግዳ፣
እኩል የሚያሰቃይ
ቁም ስቅል የሚያሳይ፣
ያገሪቱንና የዓለምን ሕግ፣ የሚጥስ ጧት ማታ
ፍርድ ሲገመድል፣ የማያመነታ
ማእቀብና ዛቻ፣ ፍፁም የማይፈራ
ፍትሃዊ ነኝ ብሎ፣ ጭራሽ የሚኮራ
ሜጫንና ገጀራን፣ የሚያደርግ ማረሻ
እንዲመረት ምርት፣ የራብ ማስታገሻ
ብሔር ብሔረሰብ፣ የማያበላልጥ
እኩል የሚፈልጥ፣ እኩል የሚቆርጥ፤
የመረገጥ መብትን ለዘጌቹ ሁላ
እኩል የሚያካፍል፣ ምንም ሳያዳላ
እኩል አፈር ድሜ፣ ሁሉን የሚያስበላ፣
የሚገዛ አካል፣ የሚረግጥ መሪ
አድለኝ እባክህ፣ አንት የኔ ፈጣሪ!
ምን ፍትህ ይገኛል፣ ከዚህ የበለጠ
ከሜንጫ ከዱላ፣ ሁሉም ካመለጠ።
የኑሮ ውድነት፣ ያድርገኝ እምሽክሽክ
እንደጠፉ ይቅሩ፣ ውሃና ኤለትሪክ፣
ጦሜን ልዋል ልደር፣ የምቀምሰው ልጣ
የመናገር መብቴን፣ ተገፈፍኩ አልልም
ሰልፍ ተከለከልኩ፣ ብዬ አላማርርም፣
ምንም ሳልተነፍስ፣ አንገቴን ደፍቼ
ከገባሁ በሰላም፣ ከቤቴ ወጥቼ፣
በድንጋይ ክምር፣ መንገዴ ሳይዘጋ
ኑሮን መኖር ከቻልኩ፣ በፍፁም ሳልሰጋ፣
ልጆቼን ካገኘሁ፣ ከነአንገታቸው
እግራቸው ባለበት፣ እንዲሁም እጃቸው
ሁሉም አካላቸው፣ ባለበት እስካለ
ከዚህ የበለጠ፣ ምን ዲሞክራሲ አለ?
አይረግጡ እረግጦ፣ የሚገዛ መሪ
አጣህልኝ እንዴ፣ አንት የኔ ፈጣሪ?!
|| 11/05/2019 ||