ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ አስቀድመው ያነጋገሯቸው ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ተስማሙ
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተወያዩት የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላልና ኦፕሬሽንን በተመለከተ ዘላቂ እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛነታቸውን አሳይተዋል እየተባለ ነው።
የሦስቱ ሃገራት ሚኒስትሮቹ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በተገኙበት ነው ውይይቱን ያካሄዱት። በውይይታቸው ላይ ሃገራቱ በአውሮፓውያኑ 2015 ላይ በካርቱም የደረሱትን ስምምት ተፈፃሚ ለማድረግ ግልፅ ሂደትን ለማስቀመጥ መስማማታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም በሃገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ አራት ስብሰባዎችን ለማካሄድም የተስማሙ ሲሆን በእነዚህ ስብሰባዎች አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በታዛቢነት ይሳተፋሉ ተብሏል። እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 15 ቀን 2020 ድረስም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደተግባቡ፣ የስምምነቱን አፈፃፀም ለመገምገምና ለመደገፍ ሁለት ስብሰባዎችን በዋሽንግተን ለማከናወን ስምምነት አድርገዋል።
ሦስቱ ሃገራት እስከ ጥር 15 ቀን 2020 ድረስ ከስምምነት መድረስ ከተሳናቸው፣ በካርቱም የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት አንቀፅ 10ን ወደተግባር ለመቀየር ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የተስማሙት። በመጨረሻም ሚኒስትሮቹ የአባይ ወንዝ ለሦስቱም ሀገራት ህዝቦች ልማት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ድንበር ተሻጋሪ ትብብር የማድረግ አስፈላጊነት ላይ ተወያይተው መግባባታቸው ተረጋግጧል።
ከዚህ ውይይት ቀደም ብሎም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳንና ከግብጽ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በኋይት ሀውስ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በጉዳዮ ላይ መክረዋል
አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በአፍሪካ ከሚገኙ ዩንቨርስቲዎች መካከል 10ኛ ደረጃን አገኘ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነዉ ተባለ:: ዮንቨርስቲው በዚህ ደረጃ ተመራጭ መሆን የቻለው በየጊዜው ባሳየው ጥረት እና መሻሻል እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ በአፍረካ ካሉ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ መመረጡን ተከትሎ ዛሬመግለጫ ሰጥቷል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በመግለጫው ላይ ዩኒቨርሲቲው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሰት በ1950 ዓ.ም እንደተቋቋመና የትምህርት ተቋሙ ሲመሰረት የመቀበል አቅሙ 33 ተማሪዎችን ብቻ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ የቅበላ አቅሙን እስከ 50 ሺህ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል::
ዩኒቨርሲቲው 13 ካምፓሶች፣ 10 ኮሌጆች፣ 2 የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩቶች፣ 12 የምርምር ኢንስቲቲዩቶች እና 2 የማስተማሪያና የከፍተኛ ህክምና መስጫ ሆስፒታሎችን በመያዝ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች፤ ማለትም በ73 የትምህርት መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር፣ በ345 የድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮች፣ በ90 የጥናትና ምርምር መስኮች የዶክትሬት መርሃ ግብሮችን እያከናወነ መሆኑን በመግለጫው ላይ ሰምተናል።
በዚህ መሠረት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እውቅናዎችን እና ደረጃዎችን እንዳገኘ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ በቅርብ ከተመዘገቡት ውጤቶች በአውሮፓውያኑ በ2014 ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች 18ኛ ደረጃ፣ በ2015 ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች የ16ኛ ደረጃን ማግኘቱን በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች በ10ኛ ደረጃ ሆኖ ሊመዘገብ መቻሉንየገለፁት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ደረጃ የደረሰው በየጊዜው ባሳየው ጥረት እና መሻሻል እንዲሁም በሚያደርገው ጥናትና ምርምር ኢትዮጵያ ከምትፈልገው የተማረ የሰው ሀይል ፍላጎት ጋር ለማጣጣም በተደረገው ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ኩራት ነው ያሉት ሓላፊ “አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትንሿ ኢትዮጵያ ነው፤ ዩኒቨርሲቲው ሌሎች ኢትዮጵያውያ ዩኒቨርስቲዎችን በያዘው የእድገት እና የመሻሻል ጉዞ ላይ የመውሰድ ግዴታ አለበትም “ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአድሚኒስትሬሽን እና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማቲዎስ ኢንሰርሙ ” ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው እድገት በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እዚህ ደረጃ የደረሰው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ባለው ተልእኮ ነው” ሲሉ የውጤቱን ምንጭ በራሳቸው ዕይታ ለመግለጽ ሞክረዋል::
ሃዋሳን የማያካትተው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ተጀመረ
የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በዛሬው ዕለት ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች መካሄድ ጀምሯል። በህዝበ ውሳኔው የሃዋሳ ሰዎች ለምርጫ ይመዝገቡ እንጂ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ የሆነችው ሃዋሳ ከተማ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ውስጥ እንደማትካተት ታውቋል:: የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከሁለት ወር በፊት ለሚዲያ አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ውስጥ የሃዋሳ ከተማን የተመለከተ ጥያቄ እንዳልቀረበ መግለጻቸው ይታወሳል::
በዛሬው ዕለት የተጀመረው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ እስከ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት 10 ቀናት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ይቀጥላል። ለህዝበ ውሳኔው በተካሄደው ዝግጅት ከ6 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ወስደው እንደተሰማሩና የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ ስርጭት መካሄዱንም ነው ምርጫ ቦርድ የገለጸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔን አፈጻጸም ሂደት አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፥ የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ማሳወቁ አይዘነጋም።
በደቡብ ክልል ግንባታቸው ተጀምሮ ከነበሩ ሆስፒታሎች መካከል የአስረ አንዱ ውል ተቋርጧል ተባለ
በደቡብ ክልል በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ወቅት ውል ተፈጽሞ ግንባታቸው ተጀምሮ ከነበሩ ሆስፒታሎች መካከል የአስረ አንዱ ውል ተቋርጧል ተባለ::
እንደ ክልሉ የጤና ቢሮ መረጃ መሠረት በወቅቱ ስድስት መቶ ሠላሳ አራት ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚያወጡ በጨረታ ለገንቢዎች የተላለፉት ሆስፒታሎች ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ቢባልም ከወሰን ማስከበር ችግሮች ፣ ከተቋራጮች አቅም ማነስ እንዲሁም በዋናነት የብር ዋጋ ከዋና ዋና የውጭ ገንዘቦች ጋር ሲነፃፀር በመውረዱ ግንባታዎች መጓተታቸው እንደ ምክንያት ተቀምጧል::
እያንዳንዳቸው 30 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ ተብለው የሚገመቱት ሆስፒታሎች ዋጋቸው ሦስት እጥፍ በማደጉ የጤና ቢሮው እና ገንቢዎቹ ግንባታው እንዲቆም ማስገደዳቸውን የደቡብ ክልል የሆስፒታሎች ግንባታ አስተባባሪ ኢንጂነር ሳሙኤል ሻሪፎ ተናግረዋል::
ከብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የዋጋ ንረት በተፈለገው ፍጥነት ግንባታውን ማካሄድ አለመቻሉ ውል እንድናቋርጥ አስገድዶናል የሚሉት ሓላፊ ግንባታቸው ከተጀመረ 21 ሆስፒታሎች ውስጥ ማጠናቀቅ የተቻለው በጉራጌ ዞን አገና ሆስፒታልና ወላይታ ዞን ገሱባ የሚገኙ የህክምና መስጫ ተቋማትን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል::
የብሮድካስት ባለስልጣን “የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን” በሚል አዲስ ስያሜ ሊደራጅ ነው
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በሚል ስያሜ እንደ አዲስ የሚያደረጀው አዋጅ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን ይህን ተከትሎ ባለስልጣኑ አዲስ ከሚቀበለው ተልዕኮና ሓላፊነት አንጻር አዲስ አደረጃጀት የመዘርጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል::
የኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ባለስልጣን የረራዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ተቋማትን ይዘት ከመቆጣጠር ባለፈ የዲጂታል መገናኛ ብዙኃንን እንዲቆጣጠር የሚዲያ ህጎችን የሰበሰበው ረቂቅ አዋጅ እንደ አዲስየሚያዋቅረው ሲሆን አዋጁ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል::
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የደረሰው ይህ ህግ መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው እና በመሻሻል ላይ ካሉ አዋጆች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል:: በአዋጁ ላይ መጨመርና መቀነስ ያለበትን ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዲሁም ሓላፊዎች ሃሳብ የሰጡበት ሲሆን ጠቀላይ ዐቃቤ ህግ ያቋቋመው የህግ አማካሪ ጉባዔ እና የህግ ማርቀቅ ሥራ ክፍል ከብሮድካስት ባለስልጣን በጋራ ህጉ የተሻለ የመገናኛ ብዙኃን ከባቢ እንዲኖር በሚያስችል መልኩ መሠራቱን ባለስልጣኑ አስረድቷል::
ቃና ቴሌቪዥን ላይ ተነጥሎ የነበረው ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ተነሳ
ቃና ቴሌቪዥን አሳሳች ነው በተባለው እና በአየር ሰዓቱ ባስተላለፈው የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ ምክንያት ከዓመታዊ ገቢው ላይ አምስት በመቶ እንዲከፈል የተላለፈበትን ቅጣት በመቃወም ለሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ባለሥልጣን ባስገባው የይግባኝ አቤቱታ መሠረት ውሳኔው እንደተሻረለት ለማወቅ ችለናል::
” ሌሎች የጥርስ ሳሙናዎች በቂ አይደሉም ለዚህም ነው ምርጫዬ ዳቦር ኸርባል የሆነው” በሚል ዓረፍተነ ነገር እናትና ልጅ የሚነጋገሩበት ማስታወቂያ ማስተላለፉን ተከትሎ በሌሎች የጥርስ ሳሙና አምራቾች እና አስመጪዎች ላይ ፍትኃዊ ያልሆነ የንግድ ውድድር ፈጽመዋል በሚል ቃናን ጨምሮ ሦስት ድርጅቶች ላይ የባለሥልጣኑ ዐቃቢያን ሕግ ክስ መመሥረታቸውን ኢትዮጵያ ነገ ከወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል::
ድርጅቶቹ ከ2011 ዓ.ም ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አምስት በመቶ እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የነበረ ቢሆንም ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ጥቅምት 18 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ጥፋተኛ አይደሉም በሚል ውሳኔው መሻሩን የሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስታውቋል: