ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለ”መውሊድ አን’ ነቢ” በዓል መልዕክት አስተላለፉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የነቢዩ ሙሐመድ (ሠዓወ) የልደት በዓልን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል::
በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች በታላቅ ድምቀት በየዓመቱ ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓሎች መካከል ኢድ- አል አድሃ አንዱና ዋነኛው ሲሆን ኢድ አል አድሃ የመስዕዋት (የዕርድ) በዓል በመባል ይታወቃል፡፡
በእስልምና የዘመን አቆጣጠር መሠረት፣ የኢድ-አል ፍጡር በዓልን ተከትሎ ከአስር ሳምንታት በኋላ ወይም በአስራ ሁለተኛው የዙል ሂድጃ ወር ውስጥ የሚከበረው የዒድ-አል አድሃ በዓል፣ የሐጅ ሥርዓት በሚከናወንባቸው አምስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ የሚካተት ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መሆኑ አይዘነጋም፡፡
ነገ ጥቅምት 29 ቀን የሚከበረው 1494ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል “መውሊድ አን’ነቢ”ይሰኛል፡፡ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር መሠረትራቢአል አወል የተሰኘው ሦስተኛው ወር በገባ በ12ኛው ቀን በየዓመቱ የሚከበረው “መውሊድ” የቃል ምንጩ አረብኛ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹የመወለጃ ቦታ ወይም የመወለጃ ዕለት›› ማለት ነው፡፡
መውሊድ በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ነቢዩ መሐመድ (ሰለላ አለይህ ወሰላም) እና የሱፊ ሸኾች የተወለዱበትን ወይም የሞቱበትን ዕለት ለማሰብ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የነቢዩ መሐመድ የልደት ቀንም “መውሊድ አን’ነቢ” ተብሎ በመጠራት በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ የእምነቱ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሮ ይውላል፡፡
ሰሞኑን አወዛጋቢውና ጽንፈኛ ብሔርተኛው ጃዋር መሀመድ ያሰማውን ተራ የሆነ የድረሱልኝ ጩኸት ተከትሎ የተለየ ተልዕኮ ያነገቡ የግለሰቡ ደጋፊዎች በፈጠሩት ሃይማኖታዊ ጥቃት ንጹሃን ሙስሊምና የተለያዮ ዕምነት ተከታዮች ሕይወታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ብዙዎች ለከፋ አካል ጉዳት መዳረጋቸው ይታወቃል::
በአስከፊው የታንዛኒያ ዕስር ቤቶች የሚማቅቁ ኢትዮጵያውያንን ለማውጣት ጥረት ተጀመረ
በታንዛንያ የተለያዩ ዕስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ። ኢትዮጵያውያኑ ታንዛኒያ ውስጥ ለዓመታት በአስከፊ ሁኔታ በዕስር ላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ በተለያዮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲዘገብ እንደነበር ይታወቃል::
ኢትዮጵያውያኑን ዕስረኞች ወደ ሀገር ቤት የመመለሱ ምክክር በአምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የተመራ ሲሆንየታሳሪ ቤተሰብ አባላት፣ ዘመድና ወዳጆች፣ የኤምባሲው የዳያስፖራ የስራ ክፍል አስተባባሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል ። ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ በህገ ወጥ መንገድ ለመግባት የታንዛንያን ድንበር ሲያቋርጡ በፖሊስ ተይዘው በዕስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎች ስላሉበት ሁኔታም በፕሪቶሪያ ምክክር ተደርጓል ነው የተባለው።
በታንዛንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎችን ለመደገፍና ለመመለስ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የታሳሪ ቤተሰቦች እና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ዜጎችን በሰላም ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ማበርከት ስለሚገባቸው አስተዋጽኦ በምክክር መድረኩ ላይ መነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
ዜጎችን መመለስ ላይ ትኩረቱን ባደረገው ውይይት የተገኙ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ታሳሪዎች የሚጠየቁትን ወጪ ሸፍነው ወደ ሃገራቸው እንዲመልሱ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእያንዳንዱ ዕስረኛ የሚያስፈልገው ወጪ ዳሬሰላም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዝርዝር ተለይቶ እንዲቀርብና ቀጣይ ሥራዎችን በዝርዝሩ መሰረት ለማከናወን ከመግባባት ላይ እንደተደረሰ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መገንዘብ ችለናል።
በተደረሰው መግባባት መሰረት ታሳሪ ዜጎችን ለመመለስ ዳሬሰላም ከሚገኘው ኤምባሲ፣ ከተባበሩት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንና አጋዥ መረጃዎችን በመለዋወጥ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድጋፉን ያለማቆረጥ እንደሚሰጥ ኤምባሲው ማሳወቁን ለማወቅ ተችሏል።
አማራ፣ ትግራይና ጅግጅጋን የተቆጣጠረው የአንበጣ መንጋ ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ያሰጋል ተባለ
በኢትዮጵያ አማራ ክልልና በተወሰነ የትግራይ ክልል ውስጥ ባሉ ቦታዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በቁጥጥር ሥር መዋል ካልተቻለ፤ ይህ ሰብል አውዳሚ የሆነው የአንበጣ መንጋ ወደ ጎረቤት አገራት ሊዛመት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አሳወቀ።
ከላይ የተጠቀሱትን ስፍራዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን የተባባሩት መንግሥታት ድርጅትበመግለጫው ላይ አረጋግጧል::በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ዋቢ ያደረገው መግለጫ አርሶ አደሮቹ በሰሜን አማራ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች ማጣታቸውን ይፋ አድርጓል። ሰሞኑን አንበጣው ወደ የተከሰተባቸው ቦታዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ አውሮፕላን መላኩን መንግሥት አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም።
ሆኖም ወረራውን ለመከላካል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ አልሆነም:: እንደ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከሆነ መንግሥት አንበጣውን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ዕንቅፋት ሆኖበታል::
“የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን ለመሥራት በአፋጣኝ ያለውን አቅምና ሀብት ተጠቅሞ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል” በማለት በፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ፋጡማ ሰይድ የችግሩን ግዝፈት አመላክተዋል:: የበረሃ አንበጣ መንጋው በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በሰብል እና በግጦሽ ላይ ጉዳት አስከትሏል።
ይህ ሰብል አውዳሚ የአንበጣ መንጋ ከየመን ወደ ሀገራችን መግባቱንና ሁኔታው አስጊ መሆኑን ኢትዮጵያ ነገ አስቀድሞ በዜና ሽፋኑ መዘገቡ ይታወሳል::
የአንበጣ መንጋው 350 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ በቀን 1.8 ሚሊየን ቶን እፅዋት ሲያወድም እንደነበር ፋኦ ግምቱን ያስቀመጠው ዓለም አቀፉ ድርጅት ፤ የመከላከል ሥራው ከተዳከመም አንበጣው በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም ወደ ሰሜን ምሥራቅ ኬንያ፣ የኤርትራን የተወሰኑ አካባቢዎች ፣ የሱዳን ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ሊዛመት እንደሚችል ፋኦ ከወዲሁ የማስጠንቀቂያ መልዕክቱን ይፋ አድርጓል።
በሀሰተኛ ሰነዶች ከመንግሥትና የግል ባንኮች 60 ሚሊዮን ብር ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
የተሰረቁ ቼኮችን እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽ ገለጸ።
ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ የምርመራና የክትትል ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራመጀመሩን በኮሚሽኑ የከባድ ሌብነትና ዘረፋ ምርመራ ማስተባበሪያ ሓላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ ተናግረዋል።
በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙት ከ70 በላይ ግለሰቦች፣ከተለያዩ የግል ተቋማት ቼኮችን በመስረቅ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ፣ ከተለያዩ የግል ባንክ የደንበኞች የባንክ ሂሳብ ውስጥ 60 ሚሊየን 843 ሺህ 601 ብር ወጪ አድርገው እንደወሰዱ በምርመራ መረጋገጡን ሓላፊው ይፋ አድርገዋል።
በተመሳሳይ መንገድ ወጪ ተደርጎ ሊወሰድ በሂደት ላይ የነበረ ከ28 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን እና ከተጠርጣሪዎቹ እጅ የተለያዩ የባንክ ቼኮች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች እንደተያዙም ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም በተጠርጣሪዎቹ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ የተገኘ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ እንዲታገድ መደረጉን ያመላከተው የኮሚሽኑ መረጃ እነዚህ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ተግባሩን የፈፀሙት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባንኮች፣ ከወረዳ አስተዳደር፣ ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት መረጃ የሚሰጧቸውን ሠራተኞች አስቀድመው በመመልመልና በጥቅም በመተሳሰር መሆኑን አጋልጧል::
ቃፍታ ሽራሮ የሚገኙ አጋዘኖችና የዱር እንስሳት በአዲስ በሽታ እያለቁ ነው
በቃፍታ ሸራሮ ፓርክ ኤፍ ኤም ወይም ዲ ፉት ኤንድ ማውዝ የሚል መጠሪያ ያለው አዲስ በሽታ የዱር እንስሳትን እየገደለ ነው ተባለ። በሽታው በተለይም አጋዘኖችን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቃ እንደሆነ ተሰምቷል::
እስካሁን ድረስ በበሽታው ምን ያህል ቁጥር ያላቸው አጋዘኖች እንደሞቱ ለማወቅ ባይቻልም በስፍራው የተገኘውየቢቢሲ ዘጋቢ እንዳረጋገጠው ግን በርካታ አጋዘኖች መሞታቸውንና፤ በዛው መጠን ብዛት ያሉትም በጽኑ መታመማቸውን ዘግቧል::
የፓርኩ ባለሞያ ሃፍቶም እንደገለፁት ይህ በሽታ የዱር እንስሳትን እንዲሁም ቤት እንስሳትን ከማጥቃቱ በተጨማሪበቀላሉም የሚተላለፍ እንደሆነና እስካሁን ባለው ሂደት የዱር እንስሳት ብቻ የተጠቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል::በበሽታው የተጠቃ እንስሳ ጆሮውና መቀመጫው ላይ የመቁሰል ምልክት እንደሚታይበት ባለሙያዎች ጥቆማ ሰጥተዋል::
በምዕራብ ትግራይ የሚገኘው ቃፍታ ሸራሮ ፓርክ ከ200 ሺሕ ሄክታር በላይ ስፋት ያለው መሬት ይሸፍናል:: በቦታውበርካታ ዓይነት የዱር እንስሳትና ብዛት ያላቸው እጽዋትይገኙበታል።በተለይም ዝሆንና አጋዘን በብዛት የሚኖሩበት ሲሆንከሰሞኑ በአካባቢው የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ከ1500 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ውድመት አድርሷል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ ዕለት ምሽት ላይ በፓርኩ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከትናንት ወዲያ ጥቅምት 26፣2012 ዓ.ም በቁጥጥር ማዋል መቻሉ ታውቋል:: በተመሳሳይ ቀን ዓዲ ጎሹ በተባለ ሌላ ኣቅጣጫ እንደ አዲስ የተነሳው ቃጠሎም ከፍተኛ ጉዳትእንዳደረሰ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል:: ፓርኩ በፌደራል መንግሥት ስር የሚተዳደር ቢሆንም አጥር እንደሌለውና በበጎ ፈቃደኝነት ተሰማርተው የሚሠሩ ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ መሆኑ ታውቋል
በተለያዩ ጊዜያቶች በተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ እንደሚነሳና የአካባቢው ታጣቂዎች (ሚሊሻ) ገብተው እርዳታ እንደሚሰጡ ያመላከተው ዜና በፓርኩ ውስጥ ወርቅን በማውጣትና ማርን በመቁረጥ የተሰማሩ እረኞች በአብዛኛው እሳት ቃጠሎውን እንደሚያስነሱ ያሳያል ።