ኢህአዴግ አንድ – አገር አስራ አንድ? || ደረጀ ደስታ

ኢህአዴግ አንድ – አገር አስራ አንድ? || ደረጀ ደስታ

“አሃዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም” አይዟችሁ እሚለወጥ ነገር የለም – ይላል የሰሞኑ የኢህአዴግ ሰዎች የውህደት ወሬ።

ኢትዮጵያውያንና አንድነታውያን አንድ አገርና አንድ ባንዲራውያን …እሚል ማናናቂያ አነጋገርም እንደዋዛ ጣል መደረጉም እየጨመረ የመጣ ይመስላል። የሚገርመው ደግሞ በውህደት ደጋፊዎችና ነቃፊዎችም ጭምር እሚሰማ አባባል መሆኑ ነው። እነዚህ ጎራ ለይተው እሚከታከቱ ወገኖች አንዳንዴ ዞር ሲሉ ያዩናል መሰለኝ ምቾት አንሰጣቸውም። ትዝብታችን ይጠቅሳቸዋል። እኔ በልጥ እኔ በልጥ ጨዋታቸው በአንድነታውያን ፊት ያሳንሳቸዋል። ወደ ራሳቸው ስበውንም ሆነ ወደ ሌሎቹ ገፍትረውን ሊጥሉን አልቻሉም።

መበላለጥና መተናነስኮ የዘረኞች ጨዋታ ነው። ነጮች ዘረኞች ሲሆኑ እሚሰደቡት የበታችነትና የበላይነት ስሜት ስለሚሰማቸው ወይም የበታች ስለሆኑ አይመስለኝም። ዘረኝነት ከየትኛውም ወገን ቢመጣ እማይረባ ነገር ስለሆነ ነው። ስለሰዎቹ ሳይሆን ስለሀሳቡ። ነጭነትን እሚያከሩ ነጮች በነጮች ሳይቀር እሚሰደቡት ስለንጣታቸው የበታች ስለሆኑ አይደለም። ወደኋላ የቀሩ፣ ያልሰለጠኑ፣ አምጠው ቢወልዱ ወፈፌን፣ አብዝተው ቢንጧቸው ከትራምፕ እማያልፍ መሪ እማይወጣቸው በመሆኑ ሊሆን ይችላል። ቢወልዱ ሂትለርን ቢያምጡ ሞሶሊንን ቢያመጡ ስታሊንን ነው።

ዘረኝነትን በልጽገው አያሳምሩትም በዝተው አያጣፍጡትም አንሰው አያሳምሩትም፣ በዙም አነሱም ያው ጠነዙ ነው። በጥላቻ ስለተሞሉ የትም አገር እንደቆርቆሮ ይጮኻሉ። ዘረኞቹ ነጮች ዓለም ከነጭ ብቻ ነው የተሠራቸው ብለው ያስባሉ። ብሔርተኛ መንደርተኛም እንዲሁ ዓለም በሱ ብሔር ዙሪያ ብቻ ትዞራለች። ድህነትና በደል ያረፈው እሱ ብሔር ላይ ብቻ ነው። ሁሌም ሂዱልኝ ዉጡልኝ ነው። ጎሰኝነት ገዝቶም ተገዝቶም ታይቷል። ያው ነው። ወህኒ ቤት አጉረህ አታለዝበውም፣ ቤተመንግሥት አኑርህ አታንቀባርረውም- ምክንያቱም የልብ ክፋትና ጥላሸት፣ የጭንቅላት ዝግተና ትንሽነት መቸም አይለቅም። ወገን ለይቶ ያለቀሰም ሆነ ያስለቀሰ አንድ ነው። ሰውን በሰውነቱ ዜጋን በዜጋነቱ ያሳነሰ እድሜልኩን እንዳነሰ ነው። ዓለም ቢገለበጥ ሀሳብ ቢለጠጥ ሺ መጽሐፍ ቢገለጥ ዘረኝነት ከፍ አይልም- ይኸው ነው።

ደግሞ ብሔር ብሔረ-ጠቦች እሚል ጨዋታ ይወዳሉ። የብሔር ብሔረሰቦችን ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች “ብሄረሰቦችን” ትተው ለምን ስለ “ብሔር” ብቻ እንደሚዘምሩ አይታወቅም። “አንድነት ብላችሁ አንድ ላይ አትጨፍልቁን” ብለው ሲያበቁ መልሰው ደግሞ አንድ ብሄር ሆነው፣ ባንድ ባንዲራ፣ ባንድ ክልል ሲጨፈለቁ ተቃርኖውን ማሰቡ ይገርማል። አንድ አገር አንድ ባንዲራ አንድ ቋንቋ አትበሉን ብለው ይከሱና፣ ያው አንድ እነሱ ብቻ ሆነው፣ ነፋስ አይግባብን ብለው ፣ አጥረውና ታጥረው ያርፉታል። ማስፈን እሚፈልጉት እኩልነትን ሳይሆን የበላይነትን ነው። የትም አገር ተመሳሳይ ናቸው። ደግሞ ገድለው አይጨርሱም ሞተውም አያልቁም፥ መገዳደል የፖለቲካቸው እማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው። ምክንያቱም መግደል እሚፈልጉት ጎሰኝነትን አይደለም ጎሰኛውን ነው። ዘርን በዘር ነው። እሚሞተው ግን ሌላውም ጭምር ነው።

ሟችም ገዳይም እኔው ነኝ፤ ሁሉም ወገኔ ደሙም ደሜ ነው! ማለት እኮ አንድ ባንዲራ፣ አንድ ሰው፣ አንድ አገር የመሆን ጥቅምና ማስተዋልን ይጠይቃል። ሺ ጊዜ ቢፋቁ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆንን!!! እናም አሁን፣ እኛም ባገራችን ሞልቶ ዘረኛችን ሆነና፣ አንድነታውያን ምናምናውያን እያሉ ይራገማሉ። አንድነትና አንድ አገርነትኮ እኮ እሚታደሉት እንጂ እሚታገሉት ሀሳብ አልነበረም። እንደነሱ አባባል“ተሞክሮ” የከሸፈ እንኳ ቢሆን “ተችሎ” የተጠላ ሀሳብ አይደለም። አባቶቻቸው ሞክረው የገነቡትን፣ ውሪ ልጆች እያፈረሱት፣ ቅኖች የተመኙትን ጠማሞች እያናናቁት አንድነት አይመጣም። አንዴ የተገነጠለ ልብ እድሜል ልኩን ደጅ ደጁን ማየቱ የተለመደ ነው። እውነት ነው ምርጫ የለንም፣ ቤት ያፈራውን ጎሰኝነት እየተቃመሱ ማዝገም የግድ ነው። አንድም የይቅር አንድም የፍቅር ግዴታ አለብን! ስለዚህ እናንተም መብታችሁን እኛም ግዴታችንን ያወቅን አንድነታውያንን ለቀቅ አድርጉን። እናንተ አሃዳዊ ድርጅት እየሆናችሁ፣ “አሃዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም” አትበሉን። እንዴት አይታሰብ ይታሰባል እንጂ። ለኔማ ከሀሳብና ምኞትም አልፎ የህይወትም ሆነ የታሪክ ትዝታዬ ነው። ለናንተስ?!

LEAVE A REPLY