የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም

ዛሬ የቀጠለውን የድሬደዋ ግጭት መቆጣጠር ከአቅሙ በላይ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አሳወቀ

ትናንት በድሬዳዋ ከተማ በተነሳ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰማ። የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ወካይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሚካኤል እንዳለ በድሬደዋ በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትባቸው ቀበሌ 6፣ ቀፊራ ደቻቱና መጋላ ፣ በቀበሌ 05 ገንዳ አዳ፣ እንዲሁም ቀበሌ 09 ገንደ ጋራ የሚባሉ ቦታዎች ናቸው መሆናቸውን ጠቁመውበድሬዳዋ ከጥቅምት 30 ጀምሮ ግጭት እንደነበር ፣ ትናንትናና ዛሬም ግጭት ተቀስቅሶ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛም መካከለኛም ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ሚካኤል ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሆስፒታል ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል።

ከፖሊስም ከሆስፒታልም የሞት አደጋ መድረሱን ለጊዜው መረጃ እንዳልደረሳቸው የተናገሩት ሓላፊው ግጭቱን ለማብረድ የፀጥታ መዋቅሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የግጭቱ ባህሪ ተለዋዋጭ እንደሆነና አንድ ቦታ በቁጥጥር ስር ሲውል ሌላ ቦታ አንደሚቀሰቀስና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አመላክተዋል።

ግጭቱ የብሔርና የሀይማኖት መልክ እንዲይዝ ሙከራዎች እንዳሉ የገለፁት ሓላፊው ጥፋተኞችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ካሉ በኋላ አሁንም ቢሆን የተፈጠረው ግጭት ከጸጥታ መዋቅሩ በላይ አይደለም በማለት ከከተማው አስተዳደር የጸጥታ ኃይል በተጨማሪ ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ እንደተሠማራ ተናግረዋል።

ግጭቱንም ለመቆጣጠር ሁሉም በጋራ እየሰሩ መሆኑን በማስረዳት ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ ከሚገኙ ሐሰተኛ መልእክቶች ራሱን እንዲጠብቅ ተማጽነዋል:: በግጭቱ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለመናገር መረጃዎችን ማጠናቀር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ጥቅምት 30 በነበረው ግጭት ግን ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

ጥቅምት 30 የተፈጠረው ግጭት መንስኤ የሁለት ሰዎች አለመግባባት መሆኑን በመግለጽ ይህም ሠፈር ለይቶ ድንጋይ ወደ መወራወር ማደጉን ገልጸዋል።አቶ ሚካኤል ዛሬና ትናንት የነበረው ግጭት ከፍተኛና ለቁጥጥር አዳጋች መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ስለደረሰው የጉዳት መጠን በአሃዝ ከማቅረብ ተቆጥበዋል::

ቀጣዮ ሃገራዊ ምርጫ ካልተካሄደ ፣ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ እንደሚያደርግ ህወሓት ገለጸ

በሀገር ደረጃ በዘንድሮው ዓመት ሊካሄድ ዕቅድ የተያዘለት ሃገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተጓጎል ከሆነ ትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ በማካሄድ ‘ዲ ፋክቶ ስቴት’ ለመሆን ወደ የሚያስችለውን ‘ቁመና’ ለመገንባት ምክረ ሀሳብ ማቅረቡ ታወቀ።

ትናንት ለንባብ የበቃው የህወሓት ልሳን የሆነው “ወይን” መጽሔት የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት ቀነ ገደብ እንዲካሄድ የሚያትት ጽሑፍ ይዞ የወጣ ሲሆን፣ ቢስተጓጎል ግን ሕገ-መንግስቱን መጣስ ብቻ ሳይሆን ‘ወደ ለየለት የፖለቲካ አለመረጋጋት’ ሊያመራ እንደሚችል በግልጽ የድርጅቱን አቋም አስነብቧል።

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ በሀገር ውስጥ የተንሰራፋውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት ሳይቆም ሃገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ስለማይችል ጊዜው መራዘም እንዳለበት እየመከሩ ይገኛሉ:: በተቃራኒው ደግሞ በሕገ-መንግስቱ መሠረት የተመረጠ መንግስት ካልቀጠለ ሁኔታው ከዚህ ወደ ባሰ ቀውስ ስለሚገባ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት የሚናገሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሉ። ከእነዚህም መካከል ህወሓት አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ ምርጫው መካሄድ አለበት በማለት አጥብቆ ከመሞገት ባሻገር አሁን ወደለየለት ዛቻና ፉከራ ተሸጋግሯል።

“ምርጫው ከተራዘመ ሊፈጠር የሚችለውን የሕጋዊ ቅቡልነት እጦት መላ የትግራይ ህዝብ ባሳተፈ እና በትግራይ ህዝብ ህልውና እና ደህንነት ጽኑ እምነት ያላቸውን በክልሉ የተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን በክልሉ ህጋዊ ምርጫ በማካሄድ እንፈታለን”  በማለትም ትናንት ለኅትመት ባበቃው ወይን የተሰኘው ልሳን መጽሔቱ ላይ አስታውቋል።

“እንደ ሃገር ሊያጋጥም ከሚችለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በተነጻጻሪ የተሻለ እና መንግሥታዊ መዋቅርን (Institutions) የገነባ እንዲሁም ራሱን ችሎ የቆመ መንግሥት (De facto state) ለመመስረት የሚያስችል ስራዎች ማሳለጥ ተገቢ ነው” ይላል በመጽሔቱ ላይ የሰፈረው የህወሓት አቋም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ‘አምባገነን’ ሲል የገለፀው በህወሓት አማካዬነት የቀረበው የወይን መጽሔት ጽሑፍ “ዋነኛው አጀንዳችን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓላማ ‘ሃገራዊ ምርጫውን አራዝሞ የፌደራል ስርዓቱን በመገርሰስ በአንድ ግለሰብ የሚመራ ስርዓት የማቆም ፍላጎት መሆኑን’ ሁሉም እንዲረዳው ማድረግ ነው” ካለ በኋላ ይህን አስተሳሰብ የሚሸከም ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር አስፈላጊዉን የፖለቲካ እና የሚድያ ሥራዎች እንሠራለንም ብሏል::

“የቡድኑ መሪ ፍላጎት ቢቻል ቢቻል ፍጹም አምባገነናዊ አካሄድ የተረጋገጠበት አሃዳዊ ስርዓትን ለማቆም መሆኑን ፍጹም ጥራጣሬ ሊገባን አይገባም” ሲልም የህወሓት አቋምን ያንጸባረቀው ጽሁፍ ያስረግጣል።ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ ውሁድ ፓርቲነት ለመቀየር የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል። ህወሓት ከዚህ በፊት በአቋም ደረጃ የውህደቱ ደጋፊ እንደነበር ቢናገርም፣ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ ግን “የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አይደለም ውሁድ ፓርቲ ሊሆኑ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል” በማለት ውህደቱ ግዜው እንዳልሆነ ጠቁሟል። በተጨማሪም ህወሓት በይፋም የውህደቱ አካል እንዳማይሆን በተደጋጋሚ አስታውቋል።

ትግራይ መንግስታዊ ቁመና (Defacto state – ራሱን ችሎ የቆመ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እውቅና ያላገኘ መንግሥት) ያላት ክልል የማድረጉ ሥራ የትግራይ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ጥናት አካሂደውበት በአፋጣኝ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚገባም ወይን አስነብቧል።

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ በአማራና ኦሮሚያ ካሉ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያዮ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መሠረታቸውን ኦሮሚያና አማራ ብሔራዊ ክልሎች ላይ ካደረጉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ጋር ስብሰባ አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮችን በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው በጽህፈት ቤታቸው ያወያዩት።

በሁለቱ ክልሎች ህልፈተ-ሕይወት እና የንብረት መውደም የሚያስከትሉ ሁኔታዎች መባባሳቸውን ተከትሎ ነው ስብሰባው መካሄዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።

በክልሎቹ በዋናነት እንቅስቃሴ እያካሄዱ የሚገኙ ፓርቲዎች የሕዝቡን ፍላጎት እና የነገ አቅጣጫ ቅየሳ እውን ማድረግ ይችሉ ዘንድ ውይይት ለማስጀመር የታለመ እንደሆነም እየተነገረ ነው::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በውይይቱ በዜጎች ላይ አንዳችም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትሉ ፖለቲካዊ ተሳትፎን የማካሄድን አስፈላጊነትን አንስተው ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጥልቀት ተነጋግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መሪዎች ሥራቸውን በሚከውኑበት ክልል ሰላምን እና መረጋጋትን ለማስፈን የበኩላቸውን አስተዋእጾ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የዛሬው ስብሰባ ባለፉት ሳምንታት በሁለቱም ክልሎች ከሚገኙ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄዱት ስብሰባዎች አንድ አካል ነው። በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከቅርብ ቀናት በፊት ከአዴፓና ኦዴፓ ጋር አብረው ለመሥራት መስማማታቸው አይዘነጋም::

ለህዳሴው ግድብ በግለሰቦች ስም ጭምር የተከፈቱ 400 ከአካውንቶች ወደ አንድ ቋት ተካተቱ

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሲባል ተከፍተው የነበሩ 4000 የገንዘብ አካውንቶች በአንድ ቋት መካተታቸው ተገለፀ::

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዞዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር  አቶ ኃይሉ አብርሃም በሰጡት መግለጫ ግንባታውን ለማፋጠን ሲባል በድርጅቶች ተቋማትና ግለሰብች ተከፍተው የነበሩ ከ4000 በላይ አካውንቶች ለሥራ ያመች ዘንድ በአንድ አካውንት ብቻ እንዲስተናገድ ተደርጓል::

በ2011 በጀት ዓመት 970 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በ2012 ሩብ ዓመት ደግሞ 168 ሚሊዮን 953 ሺኅ ብር ገቢ ተገኝቷል :: በመስከረም ወር በተለየ ሁኔታ 82 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል:: በቀጣይም በየወሩ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል:: ቀደም  ባሉት ዓመታት በህዝባዊ ተሳትፎ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በየወሩ ይሰበሰብ እንደነበር አይዘነጋም::

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሰኔ 15ቱን ግድያ አስመልክቶ ያቀረበው ሪፖርት በሕዝብ ተአማኒነት አጣ

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከሰኔ 15ቱ የከፍተኛ ባለስልጣናት እና የጦር መኮንኖች ግድያ ጋር በተያያዘ አጠናቅቄዋለሁ ያለውን መረጃ ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ትናንት ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ የተለያዩ የቴክኒክ፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ግድያውን አቀነባብረውታል የተባሉት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ እና ሌሎች አጋሮቻቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩ ኮምፒውተሮችን፣ ፍላሽ ዲስኮችንና አምስት ተሽከርካሪዎችን ፈትሾ የተለያዩ የውጪ ሀገራት ገንዘብና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን መያዙን ጠቁመው፤ በአጠቃላይ ይህንን መፈንቅለ መንግሥት ለማከናወን ዝግጅት የተጀመረው በሚያዚያ ወር መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሀኑ፣ ወንጀሉ በጀነራል አሳምነውና ለክልሉ ተቆርቋሪ ነን በሚሉ አክቲቪስቶች የተጠነሰሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህንንም ለማሳካት ኢመደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችንና እንዲሁም ሽፍቶችን በማደራጀት ተከናውኗልም ብለዋል።

በተለይ የክልሉና የፌደራል መንግሥት የተቃረኑ በማስመሰልና ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ በፓርቲው የተበደሉ በማስመሰል ኅብረተሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ይህንንም ሢሠሩ የክልሉ ስልጣን ያልሆኑ ሥራዎችንም ማከናወናቸውን አስታውቀዋል። ለአብነትም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንዲሁም ከአማራ ክልል 110 የሚሆኑ ሰዎችን በመሰብሰብ ለሰባት ሳምንታት የስለላ ስልጠና በመስጠት አሰማርተዋል ብለዋል።

ስልጠናው ስውር ጦርነት፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነት ላይ የሚያተኩር ነበር ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ለግለሰቦቹ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠናዎችም መሰጠቱን እና ስልጠናውን የወሰዱ ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ አሶሳ፣ አዋሳና አፋር የተሰባሰቡ መሆናቸውን አረጋግጠናል ሲሉ ተደምጠዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ከመከላከያ ሠራዊት በሥነ ምግባር ጉድለት ጭምር የተባረሩ እንደሚገኙበት አስረድተው የልዩ ኃይሉ አባል በማድረግ ለተግባሩ ዝግጁ እንዲሆኑ ተሰርቷልም ይላሉ።

መፈንቅለ መንግሥቱ በዋናነት የክልሉን ስልጣን ለመቆጣጠር የታቀደ መሆኑን የገለፁት አቶ ብርሃኑ፤ ከተሳካ በኋላ በዞንና በወረዳዎች ላይ ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ የተባሉ ባለሰልጣናት ላይ ተጨማሪ ርምጃ ለመውሰድ የታጠቀ ኃይል ተዘጋጅቶ እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፤ የጀነራሎቹን ግድያ በተመለከተ በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ “እርምጃ ከተወሰደባቸው በኋላ የመከላከያ ሠራዊቱ በየብሔሩ ይበታተናል፣ መፈንቅለ መንግሥቱንም ለማሳካት ቀላል ይሆናል በዚህም የፌደራል ስልጣንን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል” በሚል የተፈፀመ ነው ሲሉ ለብዙዎች ያልተዋጠና አጠራጣሪ የሆነ መግለጫ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ ጄነራል ሰዓረ ሲመቱ በቦታው የእርሳቸውን ግድያ ተከትሎ ጀነራል ብርጀሃኑ ጁላ ሊገኙ ስለሚችሉ እርሳቸውም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ተነግሮ እንደነበርም ዐቃቤ ህጉ በሪፖርታቸው አመላክተዋል::

ጀነራል ብርሃኑ በስፍራው ባለመገኘታቸው የግድያው ሰለባ ሳይሆኑ ቀርተዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ይህንንም ለማድረግ ተመልምሎ ጎንደር ውስጥ የሰለጠነ ወታደር የባህር ዳሩ ድርጊት ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ ለጀነራል ሰዓረ ጥበቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ ደውሎ እንደነገረው ገልፀው ወታደሩም ጀነራል ሰዓረንና ጄነራል ገዛዒን እንደገደላቸውም አብራርተዋል።

ለመፈንቅለ መንግሥቱ ማስፈፀሚያ ከመንግሥት በጀትና ከባለሃብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ ግልና የቡድን መሳሪያዎች ተገዝተዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በአጠቃላይ ባህር ዳር ላይ 3 ሻምበሎችን ከክልሉ ልዩ ኃይል ውጪ በማደራጀት በርዕሰ መስተዳድሩ፣ በአዴፓና በፓሊስ ጽህፈት ቤቶች፣ በክልሉ እንግዳ ማረፊያ፣ እንዲሁም በፖሊስ ኃላፊዎች ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙን አብራርተዋል።በዚህም 15 ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች ደግሞ የመቁደሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በሰኔ 15 ወንጀል በባህር ዳር 200 በአዲስ አበባ ደግሞ 147 ሰዎች ተጠርጥረው ተይዘዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፣ 70 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶ እየተፈለጉ ሲሆን 31 ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው በማለት ቀሪዎቹ 39 ግለሰቦች ግን አለመያዛቸውን ጠቁመው፤ በባህር ዳር ደግሞ 47 ተጠርጣሪዎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ተደርጎ በአጠቃላይ 55 ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት መሆኑን አስረድተዋል።

አዲስ አበባ ከተያዙት መካከል 5 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ወደ መሳሪያ ማዘዋወር የተቀየረ ሲሆን 61 ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ተወስኗል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ ነገር ግን 13 የሚሆኑት ቅድመ ምርመራ ክስ ስለተዘጋጀ በዚህ ሳምንት ይከሰሳሉ ሲሉም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ባህር ዳር ላይ 15 ተከሳሾች ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የተከሰሱ ሲሆን እነዚህም የሟቾች አጃቢዎችና የሥራ ሓላፊዎች ናቸው ተብሏል።ምርመራውን ለማካሄድ የፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ የኢንፎርሜሽን ደህንነት፣ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት፣ የመከላከያ ሠራዊት ባለሙያዎች፣ የአማራ ክልል ፖሊስና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ መሳተፋቸውንከመግለጫው መረዳት ተችሏል።

በደህንነት መስሪያ ቤት መረጃ ብቻ በሚያስበይነው የጸረ ሽብር ህግ ላይ ውይይት ተደረገ

በደህንነት መስሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎችን ለብይን የሚዳርገውን አሠራር በሚያስቀረው አዋጅ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ። ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የነበረው የፀረ ሽብር ህግ አዋጅ የሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ይጥሳል፤ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ለማሰር ተጠቅሞበታል የሚል ክስ እየቀረበበት ይገኛል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲሻሻል የቆየው ይህ ህግ በይዘትም ሆነ በአተገባበሩ ላይ በርካታ ችግሮች ሲስተዋሉበት እንደነበረ ነው የሚነገረው። በዚህ መሠረት 13 አባላት ያሉት የህግ አማካሪ ጉባኤ ረቂቅ አዋጁን ሲፈትሽ ቆይቷል፤በተለያዩ አካላትም ጥናትና ውይይት ተደርጎበታል።

ዛሬ በተመሳሳይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲወያዮበት ተደርጓል። ረቂቁ ቀድሞ በነበረው የጸረ ሽብር አዋጅ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች ተደረገውበት የተዘጋጀ ሲሆን፣ አስፈጻሚ አካላትንም ተጠያቂ የሚያደርግ ድንጋጌ የያዘ መሆኑ ተገልጿል።

ረቂቅ ህጉን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፥እየተሻሻለ የሚገኘው የፀረ ሽብር ህግ መሰረታዊ የህገ መንግስት መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም ህጉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የሽብርተኝነት ስጋት መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለትርጉም ተጋላጭ እንዳይሆን መደረጉን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ፥ እንደ ወንጀሉ ባህሪና መጠን ተመጣጣኝ ቅጣት ማስቀመጡን አንስተዋል።በረቂቅ አዋጁ በደህንነት መስሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎች ለብይን የሚዳረጉበት አሰራር እንዲቀር መደረጉም ተጠቁሟል።

ረቂቅ ህጉ የተቋማትን ሃላፊነት በግልፅ ያስቀመጠ፤ አስፈፃሚ አካላት በሽብርተኝነት የተጠረጠረ አካልን በቁጥጥር ስር ሲያውሉና ሲመረምሩ ለሚፈጽሙት ስህተት ተጠያቂ የሚሆኑበት አንቀፅን ያካተተ ነው ተብሏል::

ሃዋሳ ከተማ ሰላምና ደህንነቷ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል ተባለ

በሃዋሳ ከተማ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከህዝቡ ጋር ከተሠሩ ሥራዎች ከተማዋ ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ መመለሷን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጸ።

ምክትል ከንቲባው ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በደቡብ ክልል እና በሃዋሳ ከተማ በተከሰቱ ችግሮች ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከኅብረተሰቡ ጋር በተሰራ ስራ ችግሮች ተቀርፈው ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለሷን አስረድተዋል።

የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውም መሻሻል ማሳየቱንም አንስተዋል። በፀጥታ መዋቅሩ ላይ ማሻሻያ በማድረግ እንዲሁም የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር በህገ ወጥ ሺሻ እና ጫት ቤቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈም ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ጊዜ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎች በህዝቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑም ተነግሯል። በቀጣዮቹ 2 ዓመታት ውስጥም በከተማዋ የሚገኙ 403 ጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳት ዕቅድ መያዙንም ሰምተናል።

በሱዳን ዩኒቨርስቲ አማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ በዲግሪ ሊሰጥ ነው

ካርቱም የሚገኘው ኢንተርናሽናል ዮንቨርስቲ ኦፍ አፍሪካ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በዲግሪ ደረጃ ለማስተማር ስምምነት ላይ ደርሷል:: በተያያዘ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዮንቨርስቲ ዓረብኛ ቋንቋን በዲግሪ ደረጃ ሊሰጥ መሆኑ ተነግሯል::

በነሃሴ ወር ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን  እና ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲዎች የተውጣጣ አንድ ቡድን ወደ ሱዳን ተጉዞ ነበር::ልዑኩ ከሱዳኑ ዮንቨርስቲ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት የአማርኛና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎችን በሱዳን ዮንቨርስቲ እንዲሰጥና የዓረብኛ ቋንቋ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በተጨማሪ  በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዮንቨርስቲ እንዲሰጥ የሁለትዮሽ ስምምነት ተካሂዷል::

ቀደም ሲል ካርቱም ዮንቨርስቲ ውስጥ አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ይሰጥ ነበር:: የሱዳኑ ኢንተርናሽናል ዮንሸርስቲ  ኦፍ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ዮንቨርስቲ በመሆኑ ከአፍሪካና ከተለያዮ የዓለም አገራት የተውጣጡ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን በዚህ ዮንቨርስቲ እንዲከታተሉ ያስችላል ተብሏል::

LEAVE A REPLY