ህውሃት በመግደል፤ ኦዴፓ እና አዴፓ ቆመው በማስገደል መብት እየጣሱ ነው።
የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ፣ መብታቸውን የማክበርም ሆነ የማስከበር ሙሉ ኃላፊነት የሚወድቀው በመንግስት ላይ ነው። መንግስት ሰብአዊ መብትን በቀጥታ ቢጥስ ወይም ጥበቃ ባለማድረጉ የዜጎች መብት እና ነጻነት መንግስታዊ ባልሆኑ ሌሎች አካላት ሲጣስ እና አደጋ ላይ ሲወድቅ ምንም ማድረግ ካልቻለ ውጤቱም ሆነ ተጠያቂነቱ እኩል ነው።
ገዳይህ መንግስት ይሁን በመንጋ የሚንቀሳቀስ ሥርዓት አልባ ቡድን ውጤቱ ያው ነው። የአገዳደሉ አይነት ይለይ ይሆናል እንጂ ሟች ነህ። አንድ በመንግስት የታዘዘ ወታደር ወይም ፖሊስ በጥይት ግንባርህን ብሎ ቢደፋህም ሆነ ጽንፍ የረገጡ እና በመንጋ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ቤትህን አቃጥለው፣ ንብረትህ አውድመው፣ አንተን እና ቤተሰብህን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ቢሔዱ ለሟች በደሉ ያው ነው።
በመንግስት አካላት የሚፈጸመው በደል እና ጥቃት የአፈና ሥርዓት መገለጫ ነው። ድርጊቱ በመንግስት ውሳኔ የሚፈጸም በመሆኑ ባለሥልጣናቱን ቀጥተኛ ተጠያቂ ያደርጋል። መንግስት እና ሕግ አለ ብለህ በሰላም በተቀመጥክበት አገር እና ቤት በመንጋ ተወረህ የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረብክ የሚሰማህ ስታጣ እና ተጨፍጭፈህ ስትገደል መንግስት አንድም በእጅ አዙር የሚፈጸመውን መጥፎ የወንጀል አድራጎት ይደግፋል (የእጅ አዙር አፈና)፤ አለያም የመንግስትነት ሥራውን በብቃት መወጣት ባለመቻሉ እና ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጉ ተጠያቂ ታደርገዋለህ።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ጥሪ ሲያቀርቡ ፈጥኖ የማይደርስ፣ በመንጋዎች ሲታረዱ ከእኛ እኩል ነገሩን በሬዲዮ የሚሰማ፣ ሰምቶም ምንም አይነት አፋጣኝ እርምጃ የማይወስድ፣ ሕግ የማስከበር ተግባሩን በአግባቡ የማይወጣ፣ አመጽ እና እልቂትን የሚቀሰቅሱ መገናኛ ብዙሃን እዛው ከመዲናዋ አዲስ አበባ መሽገው አገሪቱን ወደ ትርምስ ሲከቱ እያየ በሶሻል ሚዲያ የሚሰራጩ ተራ ሃሜቶች የሚያሳስቡት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከሕግ በላይ ሲሆኑ እያየ እንዳላየ ሆኖ የሚያልፍ መንግስት ለሚደርሰው ሰብአዊ ቀውስ ሁሉ ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል። ተጠያቂም ነው።
በሕዝብ ላይ ከሚደርሰው የማያባራ ግፍ እና ጥቃት በተጨማሪ በግላጭ እየታየ ያለው ወገንተኝነት የመንግስትን ኢ ፍትሐዊነትእና መንግስት ያለበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። አገር እያተራመሱ እና ለንጹሃን ዜጎች እልቂት ምክንያት የሆኑ እንደ ጃዋር መሃመ አይነት ግለሰቦችን በቦሌ እየሸኙ እና እየተቀበሉ እነሱ መሳሪያ ያደረጉት ወጣት ላይ ማላዘን ወይም እራሱን ለመከላከል የወጣን ሕዝብ የግጭት አካል አድጎ መሳለቅ የአስተዳደሩን ክሽፈት ነው የሚያሳየው።
የሃያ ሰባት አመቱ ክምር የፍትሕ ጥያቄ በወጉ ምላሽ ሳያገኝ እንደገና አገር በወሮበላ እየታመሰ መንግስት የዳር ተመልካች ሆኖ ሕዝብን ሆድ ማስባስ መዘዙ ብዙ ነው። ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የመንግስት ያለህ፣ የፍትህ ያለህ፣ የወገን ያለህ እያለ እየተጣራ ነው። በምስራቅ ሐረርጌ እና ድሬዳዋ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት እየተደረገ ያለው ነገር ብቻ የመንግስትን ክሽፈት እና የወደፊት አቅጣጫችንን አመላካች ነው።
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ የተቃዋሚ መሪዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታችው አካላት ሁሉ ድምጻችሁን ልታሰሙ ይገባል። የአብይ አስተዳደር እና ለውጡን እመራዋለው ያለው አካል በሥልጣን ውስጥ ውስጡን ሲሻኮቱ አገር እየተበላሸች፤ ወገንም እያለቀ ነው። እናንተም ከተጠያቂነት አትድኑም።