ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዮንቨርስቲዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እና ኅብረተሰቡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ወደ መረጋጋት የማይመልሱ ከሆነ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጡ።
በሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት የዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራሮች፣ ፕሬዚዳንቶች እና ሚኒስትሮች በተገኙበት በወቅታዊ የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ ላይ ዛሬ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ላይ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ምንጭ በማጥናት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተመክሯል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መረጋጋት የማይገቡ ከሆነ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል። የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅና ለማረጋጋት የጥበቃ አቅምን ማዘመን እና በቁጥር ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በቀላል ወጪ ሊተገበሩ የሚችሉ፣ እንደ አሻራ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መግቢያ በር ላይ በመትከል የቁጥጥር ስርዓቱን ማዘመን ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል።
ከቁጥጥር ስርዓቱ ባሻገርም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱን እና በአካባቢው የሚገኘውን ህብረተሰብ ማስተሳሰር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ችግር በመፍጠር ጉዳት እንዲደርስ በሚያደርጉ ተማሪዎች ላይ መንግሥት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ነው የገለጹት።
ተማሪዎችም ወደ ሞት የሚጋብዟቸውን አካላት ለምን ወደ ሞት እንደሚመሯቸው ቆም ብለው ማስተዋል እንደሚገባቸውም አጽንኦት የሰጡት ዶክተር ዐቢይ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከአካባቢው አስተዳደርና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ቀድመው መከላከል እንደሚገባቸው አስታውቀዋል::
አወዛጋቢው ኦነግ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና ተሰጠው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ህጋዊ የሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱ ታወቀ።
በለውጡ ማግስት ከተዳከመና ከተከፋፈለ የ40 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ከተቀመጠበት ኤርትራ ወደ ሃገር ቤት የገባው የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ነው እውቅና የተሰጠው። ከገባበት ዕለት አንስቶ በአባሎቹና በደጋፊዎቹ አማካይነት ለቁጥር አታካች የሆኑ ተደጋጋሚ ችግሮችን እና ግጭቶችን ሲፈጥር የከረመው ኦነግ በቀጣዮ ሃገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ህጋዊ ምዝገባ ለማካሄድ ከጠየቀ ረዘም ያሉ ወራት ተቆጥረዋል::
የግንባሩ አመራሮች እነ ዳውድ ኢብሳን ለመቀበል ከተደረገው የመጀመሪያ እንቅስቃሴ አንስቶ የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች በአዲስ አበባ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ከፈጸሙት ዘግናኝ ጥቃት አንስቶ በተደጋጋሚ እስካካሄዱት የባንክ ቤት ዘረፋ ድረስ፣ ድርጅቱ በአንድ ጎልማሳ ሰው የዕድሜ ዘመን ልክ ያላገኘውን ዕድል ተጠቅሞ ወደ ሃገር ቢገባም በፈጸማቸው አሉታዊ ተግባር በሕዝብ ዘንድ ክፉኛ ሲወቀስ መሰንበቱ ይታወሳል::
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ እና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘቱን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም ኦነግ ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ሰላማዊ ትግል ወዳድ ለሆኑ እና በመላው ዓለምለሚገኙ ወዳጆቹ፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ለአባላቱ እና ደጋፊዎቹ በሙሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ኦነግ በመግለጫው በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እየተጫወተ ላለው ሚናም ምስጋናውን አቅርቦ፤ በቀጣይም የህዝቡን ነፃነት፣ እኩልነት እና ዴሞክራሲን በማረጋገጥ በሀገሪቱ እና በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እሰራለሁ ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአባይ ጉዳይ በአዲስ አበባ ዝግ ስብሰባ ተቀምጠዋል
የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ እንደተወያዮ ተነገረ። ውይይቱ የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ጋባዥነት በዋሽንግተን ባደረጉት ውይይት በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው በመካሄድ ላይ ያለው።
የአሜሪካ እና ዓለም ባንክ ተወካዮች ውይይቱ ላይ በታዛቢነት ተሳታፊዎች ሲሆኑ፣ በቀጣይ በሱዳን ካርቱም እና በግብጽ ካይሮ እንደሚወያዮ ከወዲሁ ተነግሯል። የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በግድቡ የውሃ አሞላል እና አስተዳደር ላይ ያተኩራል ተብሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጋባዥነት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳንና ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በዋሽንግተን መወያየታቸው የሚታወስ ነው። የሃገራቱ ሚኒስትሮች በጋራ በመከሩበት ወቅት የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላልና ኦፕሬሽንን በተመለከተ ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛነታቸውን አሳይተውም ነበር።
በአሜሪካ አወያይነት በተካሄደው የሃገራቱ የህዳሴ ግድብ ምክክር ሦስቱ ሀገራት በአውሮፓውያኑ 2015 ላይ በካርቱም የደረሱትን ስምምት ተፈፃሚ ለማድረግ ግልፅ ሂደትን ለማስቀመጥ እንደተስማሙም ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ በሃገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ አራት ስብሰባዎችን ለማካሄድም የተስማሙ ሲሆን፣ በእነዚህ ስብሰባዎች አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በታዛቢነት እንደሚሳተፉ መገለፁ አይዘነጋም።
እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 15 ቀን 2020 ድረስም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተግባቡት ኢትዮጵያ ፣ ግብፅና ሱዳንየስምምነቱን አፈፃፀም ለመገምገምና ለመደገፍ ሁለት ስብሰባዎችን በዋሽንግተን ለማከናወን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በመጨረሻም ሚኒስትሮቹ የአባይ ወንዝ ለሦስቱም ሀገራት ህዝቦች ልማት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ድንበር ተሻጋሪ ትብብር የማድረግ አስፈላጊነት ላይ መስማማታቸውም ይታወሳል።
ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደው የሦስቱ ሃገራት ስብሰባና የደረሱበትን የመግባቢያና የልዮነት ነጥብ አስመልክቶ እስካሁን ድረስ በማናቸውም በኩል ይፋ የሆነ መግለጫ ያልተሰጠ ከመሆኑ ባሻገር ውይይቱ ምስጢራዊ ይዘት የተላበሰ እንዲሆን መደረጉን ታማኝ ምንጮቻችን ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል::
አብን፣ አፌኮ ፣አዴፓ፣ ኦነግና ኦዴፓ የዮንቨርስቲ ጥቃቶች እንዲቆሙ በጋራ ጥሪ አቀረቡ
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እየደረሰ ያለው የንጹሃን ዜጎች ጥቃትና ግጭትእንዲቆም በክልሎቹ የሚሠሩ የፖለቲካ ጥሪ ማቅረባቸው ታወቀ።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) እና የአማራ ማኅበራዊ ራዕይ ግንባር በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን የገለጹት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ትላንት( ሃሙስ) ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፤ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር ከሚያላሉና ወደ ብጥብጥና ከሚያመሩ ማናቸውም ተንኳሽ ጉዳዮች ለመቆጠብ፣ ብሎም በሕዝቦች ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ለመቀልበስ በመተባበር ለመሥራት መወሰናቸውንም አስታውቀዋል።
“ልዩነቶች ቢኖሩንም፣ ልዩነቶቻችን ከአገራችን እና ሕዝባችን የማይበልጡ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ለአገሪቱ ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹ በሁለቱ ክልሎች እና ዩኒቨርስቲዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ የድርሻቸውን በመወጣት፣ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች አንድነት ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የዛሬ ሳምንት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰውና የሁለት ተማሪዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ጥቃት በኋላ በደምቢዶሎ፣ በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲም ተማሪዎች መሞታቸው አይዘነጋም። እስካሁን ድረስ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ጥቃት ተሳትፈዋል የተባሉ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉና በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሰላም ለማስፈን የጸጥታ ኃይሎች መሠማራታቸውም ተሰምቷል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር በበኩሉበዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ የተከሰተውን ለመቆጣር እየሠራ መሆኑን ገልጾ፤ ግጭቱን መቆጣጠር ከአቅሜ በላይ አይደለም ቢልም አሁንም በመላ ሃገሪቱ ያሉ ዮንቨርስቲ ውስጥ ተማሪዎች በስጋት ላይ ይገኛሉ::
መንግሥትና የግል ባለሃብቶች በጋራ የሚሠሩበት የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሊጀመር ነው
በመንግስት እና በግል አጋርነት ጥምረት የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ታወቀ ።
ዕቅዱ በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እንዲደረግም በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ የተቋቋመው የመንግስትና የግል አጋርነት ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉ ተረጋግጧል።
በቦርዱ ውሳኔ መሰረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዳማ – አዋሽ – ሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድን በጥምረቱ ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት እንዲካሄድም ተነግሯል።
ይህን ተከትሎ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቱ እየተካሄደ ሲሆን ውጤቱን ተከትሎም ወደ ግንባታ ሥራ ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል። የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚሳተፍበትን ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱ አይዘነጋም።
ይህ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት ተግራዊ ተደርጎ አበረታች ውጤት እንደተገኘበት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።
ቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሟቾችን አስከሬን ያለቤተሰብ ዕውቅና በመቅበረቻው ተወገዙ
በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ሳቢያ ሕይወታቸውን ካጡት አንዱ መሀል ሚስተር ኩሪያ አንዱ ናቸው:: ግለሰቡባለፈው ሐሙስ በአደጋው የሞቱና አስክሬናቸውን ለመለየት ያልተቻለ ተሳፋሪዎች በተመሳሳይ ሬሳ ሳጥን፣ በመደዳ ሲቀበሩ እሳቸውም አብረው መቀበራቸው ታውቋል።
ልጃቸው ዚፓራ ግን ይህ አሳዛኝ ነገር ሲከናወን በሥፍራው አልተገኘችም ነበር። በዕለቱ የቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦታው መኖራቸው ቢነገርም፤ ዚፓራና ቤተሰቦቿ ስለ ክንውኑ የሰሙት ዘግይተው ስለነበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአደጋው ከሞቱ ተሳፋሪዎች የሦስቱ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ስለ ሥነ ሥርዓቱ የተነገራቸው ከቀናት በፊት ነበር። ስለዚህም በዕለቱ መገኘት የቻሉት ከ157 የሟቾች ቤተሰቦች ሁለቱ ብቻ ናቸው። “ቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአባቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ሳስበው ያንዘፈዝፈኛል” ስትል ዚፓራ ሀዘኗን በምሬት ገልጻለች።
እስካለፈው ሳምንት ድረስ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ሥፍራ የሰዎች አስክሬን እንዲሁም የአውሮፕላኑ ስብርባሪም ሲገኙ መቆየቱ ተሰምቷል። በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ባለፈው ወር አካባቢውን ሲጎበኙ፤ የሰዎች ቅሪተ አካል እና ቁሳቁሶችም ማየታቸው እንዳስደነገጣቸው ተናገረዋል።
በአደጋው የሞቱና አስክሬናቸውን ለመለየት ያልተቻለ ተሳፋሪዎች በተመሳሳይ ሬሳ ሳጥን፣ በመደዳ ተቀብረዋል::የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሱ ይታወሳል።
የሰዎች አስክሬን እና የአውሮፕላኑ የመረጃ ቋትም ተሰብስቦ ነበር። አደጋው የደረሰው በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ እክል ምክንያት ሲሆን፤ ከዓመት በፊት ኢንዶኔዥያ ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ ማክስ 737 መከስከሱን ተከትሎላለፉት ዘጠኝ ወራት ከበረራ ታግዷል።
የቢቢሲ ባልደረቦች አደጋው የደረሰበትን ሥፍራ በጎበኙበት ወቅት የአውሮፕላኑ የተለያዩ ክፍሎች ወዳድቀው አግኝተዋል። አካባቢው እየተጠበቀ ስላልነበረ እንስሳት በተከለለው ሥፍራ ገብተውም ተመልክተዋል። በአካባቢው ዝናብ ሲበረታ ችግሩ መባባሱን ያስተዋሉ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች አንዳች እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው እንደነበርም ተሰምቷል።
ልጇን ሳምያ ሮዝን በአደጋው ያጣችው ናዲያ ሚሊሮን፤ “በአካባቢው በግልጽ የሚታየውን የሰዎች አጥንት ነዋሪዎች ይሸፍኑት ነበር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎችን ቅሪተ አካል እንዲሸፍን እንፈልጋለን” ብላለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሩ መኖሩን አምኖ፤ በኢንሹራንስ ምክንያት እርምጃ መውሰድ አለመቻሉን ለሟቾች ቤተሰቦች አስታውቆ ነበር። ሆኖም ከቤተሰቦች ጫና ሲበረታበት እና የቢቢሲን ምርመራ ተከትሎ ችግሩ መቀረፉ ተሰምቷል።
ከዚህ ቀደም ለፎረንሲክ ምርመራ የተነሱ የአጽም ቅሪቶች ተሰባስበው በሬሳ ሳጥን ተከተዋል። አካባቢው የቀብር ሥፍራም ተደርጓል። የሟቾች ቤተሰቦች፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሊያሳውቃቸው ይገባ እንደነበር አሁንም በመግለፅ ላይ ናቸው።
ጉዳዩን አስመልክቶ ቦይንግ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ሆኖም “በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በላየን ኤር አደጋ ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሰዎች መጽናናቱን እንመኛለን፤ ድጋፍ በማድረግም እንቀጥላለን” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ዚፓራ ኩሪያ ባለፈው ወር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛ የአባቷን አስክሬን ለመውሰድ ጥረት ብታደርግም የደረሰችው ዘግይታ እንደነበርና “ቦታው ላይ በጊዜው አለመገኘቴ ልብ ይሰብራል” ስትልም የተሰማትን ሃዘን ገልጻለች።
የአባቷ ሥርዓተ ቀብር የሚካሄድበትን ቀን ብታውቅ እንደማትቀር ጠቁማ “አባቴን እንዳልሰናበተው አደረጉኝ” በማለት ቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ክፉኛ ወቅሳለች።