የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ሊወያዮ ነው

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንባሩን በማዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመሥረት በቀረበለት የውህደት ዝርዝር ጥናት ላይ ተወያይቶ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል።

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት የግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የቀረበውን ሃሳብ ተቃውመው ድምጽ የሰጡት የህወሓት አባላት ሲሆኑ ከቀድሞው የደህንነት ተቋም ሓላፊ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በስተቀር የህወሓት አባላት መሳተፋቸውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ተናግረዋል።

ውሳኔው በተሰጠበት ጊዜ ስድስት ሰዎች ብቻ መቃወማቸውን አስመልክቶ ድምጽ በሚሰጥበት ወቅት ከተሳታፊዎች መካከል መውጣትና መግባት ስለነበረ በአጋጣሚ የተፈጠረ ነው የሚከራከሩት አቶ አስመላሽ በውይይቱ ሁሉም እንደተሳተፉና በፓርቲያቸው አቋም ጸንተው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።

ወሳኝ ድምጽ በተሰጠበት ስብሰባ ላይ ሁለቱ አባላት ያለመገኘታቸው አጠያያቂ ቢሆንም የህወሓት ቁልፍ ሰው የሆኑት አቶ አስመላሽ በጉዳዮ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበው ሀቁን በዝምታ አልፈውታል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የድርጅቱ ውህደትን በተመለከተ ፣ ቀጣይ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ዛሬም ስብሰባውን ቢቀጥልም ውህደቱን ሙሉ ለሙሉ የተቃወሙት የህወሓት አባላት ግን በዛሬው ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፉ አቶ አስመላሽ ለቢቢሲ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው ከእርሳቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ያሳወቁት በ27 ዓመት ውስጥ ለአምባገነኑ ስርዓት ምቹ የሆኑ አፋኝ የሆኑ ህጎችን ሲያረቁ የቆዮት አቶ አስመላሽ ፤ ህወሓት የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ከዚህ ቀደምም አቋሙን እንዳሳወቀ፣ ነገር ግን ሂደቱ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እስከ ድርጅቱ ጉባኤ ድረስ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።

“ከአሁን በኋላ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በፓርቲው አቋምና ዓላማ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል” ያሉት አቶ አስመላሽ በህወሓት መጻኢ ዕድል ላይ “ከፓርቲው ውጪ ሌላ ኃይል መወሰን አይችልም” ሲሉ መቀሌ የመሸገውን ቡድን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።

ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ሃሙስ ማታ ይፋ ይሆናል አሉ

በሲዳማ ዞን የሚካሄደው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት በሚቀጥለው ሐሙስ አመሻሽ ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ።

ወ/ት ብርቱካን ዛሬ በሐዋሳ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፣ የሕዝበ ውሳኔ ሂደቱ በመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ በኋላ መረጃዎችን የማጓጓዝ እና በፍጥነት የማድረስ ችግር መስተዋሉን ልብ ማለታቸውን ጠቅሰው ይህም ችግር ውጤት በማሳወቂያ ጊዜ ላይ ሊንፀባረቅ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ ክስተት ውጤት የማሳወቂያውን ጊዜ ከአንድ ወይንም ከሁለት ቀን በላይ ያራዝመዋል ብለው እንደማያስቡ በተጨማሪነት ገልጸዋል::

የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልላዊ አስተዳደር ይሁን ወይስ አሁን ባለበት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ይቀጥል በሚለው የዞኑ ነዋሪ በመጪው ረቡዕ በሚከናወነውን ሕዝበ ውሳኔ ይለይለታል።

የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 2.3 ሚሊዮን ይጠጋል ፣የሕዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች በቁጥር ከስድስት ሺህ በላይ ሲሆኑ እነርሱም በ1692 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተሠማሩ ታውቋል። የድምፅ ሰጭዎች ምዝገባ ከጥቅምት 27 ቀን እስከ ኅዳር 06 ድረስ የተከናወነ ሲሆን ምዝገባውም ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ከጋዜጣዊ መግለጫው ጋር አያይዞ ያሰናዳው ጽሑፍ ያብራራል።

አንድ መቶ ስድሳ ያህል ቋሚ አና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ከሲቪል ማኅበረሰብ የተዘጋጁ ሲሆን የተወሰኑት እስካሁን ያለውን ሒደት በመዘዋወር ሲቃኙ ቆይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚወከሉ ታዛቢዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ወኪሎችን በተመለከተ ሁለቱም የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን እና ካለበት ክልል ጋር እንዲቀጥል የሚጠይቁ ድምፆች እንዲሰሙ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልልን እና የሲዳማ ዞንን ቢጠይቅም ፤ የዞኑ አስተዳደር ተወካይ ሲያስቀምጥ ክልሉ ሳይወክል  ቀርቷል:: “ይህም ያሳዝናል ” ያሉት ሰብሳቢዋ “በሁሉም ጣብያዎች የሲዳማ ዞን ወኪሎች ልኳል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ግን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፣ ሊልክልን አልቻለም። ከምክር ቤት ቀጥለን አስተዳደሩን ጠይቀናል፣ ተወካይ አልላኩልንም።” ሲሉ ተደምጠዋል::

ከዚህም የተነሳ ወደምርጫ ጣቢያዎች የተንቀሳቀሰ አካል ማግኘት የሚችለውን የአንደኛውን ወገን ብቻ ወኪል መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል:: የሕዝበ ውሳኔ ሒደቱን በደረሰው ሪፖርት እና በመስክ ጉብኝቶች ታዝቧቸው የእርምት እርምጃዎች መካከል የአስተዳደር አካላት እና የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በሁለት መቶ ሜትር ርቀት መገኘት የማይገባቸው ሰዎች፤ እንዲሁም የተከለከሉ ምልክቶች መታየት አንደኛው እንደሆነ የምርጫ ቦርድ መግለጫ ያስረዳል።

የሕዝበ ውሳኔው በሚካሄድበት ዕለተ ረቡዕ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ቀድሞ ተገልፆ የነበረ ሲሆን፤ ይህ የሥራ ክልከላ የግል የንግድ ተቋማትንም እንደሚጨምር ብርቱካን ተናግረዋል። ለሕዝበ ውሳኔው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከአዲስ አበባ ተነስተው በመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥበቃ እየተደረገለት ወደዞኑ በመምጣት ላይ ነው። ከፍተኛ የተመዝጋቢ ቁጥር የታየባቸውን የምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት ተጨማሪ 175 ጣቢያዎችን ቀደሞ ምዝገባ ከተደረገባቸው ጣቢያዎች ጎን የሚያቋቁም መሆኑን ቦርዱ አረጋግጧል።

ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የርቀት ትምህርት እንደሚጀመር  ተገለጸ

በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ከ5ኛ እስከ12ኛ ክፍል ድረስየርቀት ትምህርት ማስተግበሪያ መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሆነ የትምህርት ሜኒስቴር ገለጸ።

የርቀት ትምህርቱ መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ሲተገበር የቆየ ቢሆንም፤ ወጥነት ባለው መልኩ በሀገር ደረጃ ለመተግባርና የትምህርት ጥራቱንም ለመከታተል በሚያመች መልኩ የትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዳይሬክቶሬት፣ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ረቂቅ የርቀት ትምህርት ማስተግበሪያ መመሪያ መዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኗል ነው የተባለው።

ረቂቅ ማስተግበሪያ መመሪያው ስለ ርቀት ትምህርት ተጠቃሚዎች፣ የሞጁል አዘገጃጀት፣ ማጠናከሪያትምህርት መስጫ ማዕከላት አደረጃጀትና ትምህርት አሰጣጥ፣ የምዘና ስርዓት፣ የተማሪዎች ምዝገባና ሪከርድ አያያዝ፣ የሚመለከታቸው አካላት ተግባርና ሓላፊነት እንዲሁም የተቋማት የፍቃድ አሰጣጥና ስረዛን ያካተተ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

እየተዘጋጀ ባለው ረቂቅ የርቀት ትምህርት ማስተግበሪያ መመሪያው ዙሪያ ከክልል በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ትምህርት ሚኒስቴር  ይፋ አድርጓል። ረቂቅ ሰነዱ በቀጣይም ከዘርፉ ባለሙያዎች እና ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎበት ሲፀድቅ በተግባር  ላይ ይውላል::

በጎንደር አርማጭሆ ሰዎችን ሲያግቱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ ሰው በማገት ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በህግ እንዲቀጡ መደረጉን የወረዳው አስተዳደር ገለጸ።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገስጥ አሳምናቸው ያለፈው ዓመት ግለሰቦች ታግተው ገንዘብ እንዲያመጡ የሚጠየቁበትና በዚህም ስጋት በርካቶች አካባቢውን ለቀው የተፈናቀሉበት ወቅት እንደነበር ጠቁመዋል። ሰው በማገት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወትና ንብረት ለአደጋ ያጋለጡ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደራጀ ዘመቻ መከናወኑንም አስረድተዋል።

በዚህ መንገድ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ በዘጠኙ ላይ ክስ ተመስርቶ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም በድርጊታቸው በመጸጸት የወሰዱትን ገንዘብ መልሰው ያስረከቡ መኖራቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ በእርቅ ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረው እጃቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ባልሆኑና በጸጥታ አካላት ላይ የተኩስ አጸፋ የወሰዱ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎቸ ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። በቀጣይም በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ሰምተናል::

የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ:: በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ያለው የኢንዱስትሪ ሳምንት ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት ይቆያል ተብሏል።

“የአፍሪካ ኢንዱስትሪን ለአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ማመቻቸት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው ያለው። የአፍሪካ ህብረት ሳምንቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ በአህጉሪቱ አካታች፣ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ፥ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ መንግስታት እንዲሁም ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ  መልዕክት አስተላልፏል።

በኢንዱስትሪ ሳምንቱ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጭዎች  ተሳትፈዋል።ጀማሪዎችን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማበረታታ የኢንዱስትሪ ሳምንቱ ትኩረት ፣ ይህም በአህጉሪቱ አምራች ዘርፉን በማጠናከር በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥ ተወዳደሪ ለመሆን ያግዛል ነው የተባለው።

ሳምንቱን የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የንግድና ኢንዱስትሪ፣ ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል እና የመንግስታቱ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ተቋም በጋራ አዘጋጅተውታል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በመጭው ሃምሌ ወር ላይ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ይታወቃል።

LEAVE A REPLY