የአረብ ፓርላማ በህዳሴው ግድብ ላይ የግብፅን አቋም እደግፋለሁ አለ
የአረብ ፓርላማ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብን አስመልክቶ የግብፅ መንግሥት የያዘውን አቋም እንደሚደግፍ ገለፀ::
በጉዳዮ ላይ ዘው ብሎ የገባውና አንዳችም የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሃሳብ በህዳሴው ግድብ ላይ የማቅረብ መብት የሌለው የአረብ ፓርላማ እንዲህ ዓይነት የወረደና ልዮነት ፈጣሪ የሆነ ሃሳብ መሠንዘሩ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የተለያዮ የዓለም ሀገራት ዘንድ አግራሞትና ትዝብትን ፈጥሯል::
የአረብ ፓርላማ የህዳሴው ግድብ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰች ያለችውን ኢትዮጵያን በማውገዝ የግብፅ አቋምን እንደሚደግፍ አቋሙን ያሳየበትን ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መጻፉን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋግጧል ።
ሚሻል ቢን ፋህም አል ሳላሚ (የአረብ ፓርላማ ፕሬዝዳንት) በትዊተር ለዓለም ባሰራጩት አስገራሚ መልዕክት ይህን የምክር ቤቱን አቋም የሚገልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መላካቸውን አስታውቀዋል:: በተመሳሳይ ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው የግብፁ “አልሀራም” ጋዜጣም የአረብ ፓርላማ ለግብፅ አጋር መሆኑን በይፋ ማወጁን በዘገባው ሠራው ዘገባ ላይ አካቶታል::
በሌላ በኩል የአረብ ፓርላማ ለተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጉዳዮንና አቋሙን አስመልክቶ ደብዳቤዎች መላኩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዶቼ ቬሌ አስታውቋል። የሚኒስትር መ/ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ይህ ግን አዲስ ነገር አይደለም ይላሉ። “ከተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡት መግለጫዎች ከተጀመረው የውይይት ሀዲድ ለማስወጣት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው” በማለት የአረብ ሀገራት ፓርላማ አቋምን ጨምሮ የሚደረጉትን ግፊትና ጫናዎች አጣጥለዋል።
ሲዳማ ክልል መሆኗ ከተረጋገጠ ኢጄቶዎች ፖሊስና የልዮ ኃይል አባልነት ተመርጠዋል
የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ዛሬ ረቡዕ ህዳር 10/2012 ዓ.ም ሕዝበ-ውሳኔ ላይ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን የድምፅ አሰጣጥ ተግባር ሲያከናውኑ ውለዋል:: ሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልል ይሁን ወይስ በደቡብ ክልል ውስጥ ይቀጥል የሚለውን ለመለየት ለረዥም ጊዜ የቆየው ውዝግብ ነገ ይፋ በሚሆነው ውጤት መቋጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በሕዝበ-ውሳኔው ለመሳተፍ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ጎጆ ለደቡብ፤ ሻፌታ ለሲዳማ ምልክት ሆነው ቀርበዋል።
ድምፅ መስጠት የጀመረው ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ነው ቢባልም መራጮች ወደ ጣብያዎች ማምራት የጀመሩት ከንጋቱ 10 ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው ሃዋሳ ዛሬ ድምፅ ለመስጠት በወጡ እና ረዥሙ ሰልፍ ሳይበግራቸው በሚጠባበቁ ሰዎች ተጠለቅልቃ ታይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚያዚያ 2010 ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ ፖለቲካዊ ለውጦችን ማካሄዳቸው ይታወቃል።
በአፋኝና አምባገነን ስርዓት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ወደ አንፃራዊ ዴሞክራሲ እና የነፃነት ተስፋ ወደሚታይባት ሀገርነት እንደመጣች በዓለም መድረክ ሲመሰከርም ተስተውሏል። ለሁለት አስርታት ተኮራርፈው የነበሩት የኢትዮጵያ እና ኤርትራን መንግሥታት እርቅ ያወረዱት በጠ/ሚ ዐቢይ ዘመን መሆኑን ተከትሎ የለውጡ አጋፋሪየኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል:
ይሁንና የድኅረ ዐቢይ ጊዜ ብሔር ተኮር ግጭቶች በየቦታው የተስተዋሉበት፣ ሰላም የራቃቸው አካባቢዎች የበረከቱበት ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምን በማስከበር ረገድ ስስአቋም ነው ያላቸው ተብለውም እየተተቹ ነው። ባለፉት 20 ወራት በተለያዩ ቦታዎች ብሔርን አስታከው በተከሰቱ ግጭቶች ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በርካታ ንጹሃን ዜጎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዛሬ ለክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደባት ሲዳማ ዞንም ከሌሎች የተለየች አልነበረችም። ሲዳማ ክልል መሆን አለባት የሚለው ጥያቄ ጎልቶ መሰማት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ሕዝበ-ውሳኔው ሐምሌ ላይ መካሄድ አለበት ያሉ ሰልፈኞች ከሌሎች የዞኑ ነዋሪዎች ጋር ተጋጭተው ሕይወት መጥፋቱ፤ ንብረት መውደሙምና ዘግናኝ ዕልቂት መፈጸሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
‘ኤጄቶ’ የተሰኘው ሲዳማ ክልል መሆን አለባት የሚለውአቀንቃኝ የወጣቶች ክንፍ በወቅቱ ጥፋት አድርሷል ተብሎ ተወቅሶ ነበር። በዚህ ግጭት ቢያንስ 25 ሰዎች መሞታቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት መውደሙም በጊዜው ተገልጿል።
ከኢህአዴግ ዘመነ-መንግሥት በፊት የነበረው ሕገ-መንግሥት ሲዳማን ክፍለ-ሃገር ሲል ይጠራት ነበር። ውልደቱ 1987 ዓ.ም. የሆነው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ዘጠኝ ክልሎች አሉት። አዲስ አበባና እና ድሬዳዋ ደግሞ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። ሕገ-መንግሥቱ ክልላቱን የከፋፈለው ብሔርን መሠረት አድርጎ መሆኑ ይታወቃል።
ነገር ግን የሲዳማ ብሔር ከሌሎች ከ50 በላይ ብሔሮች ጋር በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲካተት ተደረገ። የሲዳማ ሕዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ 4 በመቶ እንደሆነ እና አምስተኛው ትልቁ ብሔርም እንደሆነ ይታመናል። ተንታኞች ይህ እውነታ ሲዳማ ክልል ትሁን ለሚለው ሃሳብ ትልቅ ማሳመኛ ነው በማለት ይከራከራሉ።
ሲዳማ ክልል እንድትሆን ሕዝበ-ውሳኔው የሚበይን ከሆነ የሲዳማ ክልል 10ኛው ሆኖ ይመዘገባል። አልፎም የራሱን ሕገ መንግሥት ማውጣት እና የፖሊስ ኃይል ማቋቋምም እንደሚችል ህገ መንግሥቱም ይፈቅድለታል። በተጨማሪም የራሱ በጀት የሚመደብለት ይሆናል።
ይህን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ነገ መረጃዎችን ያቀበሉ ታማኝ የዜና ምንጮች በርካታ የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ የደቡብ ክልል ባለሥልጣናት ከምርጫ ውጤቱ በኋላ የራሳቸውን የፖሊስና የልዮ ኃይል ባለፈው ሐምሌ ወር በተለያዩ የሲዳማ ዞኖች ከፍተኛ ኹከት ሲፈጥር በሰነበተው እና ራሱን ኢጄቶ እያለ በሚጠራው ቡድን አባላት ለማዋቀር ከወዲሁ ውስጥ ውስጡን ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል::
የሲዳማ ክልል ትሁን አቀንቃኞች የቋንቋና የባሕል ዕድገት ሌላኛው ክልል የመሆን ጥቅም ነው በማለት እያብራሩ ይገኛሉ። ምንም እንኳ ሲዳማ ክልል መሆን አለባት የሚለውን ሃሳብ ተቃውመው አደባባይ የወጡ ባይኖሩም፣ ሲዳማ ክልል ከሆነች ሌሎችም ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ብለው የሚሰጉ በርካቶች ናቸው። ለምሳሌ ደቡብ ክልል ውስጥ ብቻ እንኳ የወላይታ እና ሃዲያ ሕዝቦች ክልል የመሆን ጥያቄን ማነሳሳት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር አዲስ ፈተና ይዞ ሊመጣ ይችላል። የክልል እንሁን ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም ማለት ደግሞ ብሔር ተኮር ውጥረቶች ይጨምራሉ እንጂ አይቀኑስም ማለት ነው።
የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ ዞን ውስጥ ያለውን ብሔር ተኮር ውጥረት ያረግበው ይሆን የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ቢቀር እንኳ ሕዝበ-ውሳኔው ለቀጣይ ሃገር አቀፍ ምርጫ መሞከሪያ ይሆናልና በጎ ጎኑ ያመዝናል የሚሉ ድምፆች እየተሳተፉ መሆናቸውን አጠቃላይ የሲዳማን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያስቃኘው የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።
በሕዝበ-ውሳኔው ለመሳተፍ ቢያንስ ላለፉት ስድስት ወራት ሲዳማ ዞን ውስጥ ነዋሪ መሆንን የሚያሳይ መታወቂያ መያዝ ዋነኛ መሥፈርት ነበር።
በምርጫ ወረቀቱ ላይ ሁለት ምልክቶች ሠፍረዋል። አንደኛው ጎጆ፤ ሌላኛው ደግሞ የሲዳማ ብሔር ባህላዊ ዕቃ ሻፌታ ነው። ሻፌታ ብለው የሚመርጡ ሲዳማ ክልል እንድትሆን ድምፃቸውን ሰጥተዋል ማለት ሲሆን ጎጆ መራጮች ደግሞ ሲዳማ ዞን በድቡብ ክልል ውስጥ እንድትቀጥል የሚሹ መሆናቸው ተገልጿል። የእዚህ ታሪካዊ ምርጫ ውጤት ነገ ዕለተ ሐሙስ አሊያም አርብ እንደሚታወቅ የምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉን በተመለከተ ኢትዮጵያ ነገ ከቀናት በፊት መዘገቡ አይዘነጋም::
ድምጻቸው ጠፍቶ የከረሙት ደመቀ መኮንን ስለ ውህደቱ መግለጫ ሰጡ
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህደት በዋልታ ረገጥ እሳቤዎች ለተወጠረችው ኢትዮጵያ ወደ እንድትመጣ አማራጭ እንደሚሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ድምፃቸው ጠፍቶ የሰነበተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዛሬው ዕለት የኢህአዴግን ውህደት አስመልክተው መግለጫ በሰጡበት ወቅት ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በከፍተኛ የመዋቅር ችግር ውስጥ መቆየቱን ማስታወስ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ይህም ኢትዮጵያን ብሄርና በሀገራዊ ማንነት በሚሉ ሁለት ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች እንድትወጠር ማድረጉን ነው ያብራሩት።
ውህድ ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትንና ብዝሃነትን እንዲሁም የግልና የቡድን መብቶችን ባከበረ መልኩ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ይሰራል ያሉት የለውጡ ከፍተኛ ተዋናይ፤ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም፣ አሳታፊነት፣ በዜጎች ለውጥ የሚለካ እድገት የውህደቱ ማጠንጠኛ ተጨማሪ ሃሳብ እንደሆኑ አመላክተዋል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በድርጅቱ ውህደት፣ በአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራምና በህገ ደንብ ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱም ሥራ አስፈጻሚው በሦስቱም አጀንዳዎች ላይ የሚያግባባና የሚያቀራርብ ሃሳብ ማንጸባረቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም::
ኢ/ር ታከለ ኡማ ለተንቀሳቃሽ ቁሳቁስ ማከፋፋያነት የተዘጋጁ ሞዴል ባሶችን ጎበኙ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተበላሽተው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ እና ለተንቀሳቃሽ ቁሳቁስ ማከፋፋያነት እንዲውሉ የተዘጋጁ ሞዴል ባሶችን ጎበኙ።
የአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ለረዥም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥባቸው የቆዩ ባሶችን በከተማዋ በሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች አማካኝነት እድሳት እና ጥገና ተደርጎላቸዋል::8 ለወጣቶች የመስሪያ ቦታ እንዲሆን የተዘጋጁ ስድስት ሞዴል ባሶችንም ለሥራ አጥ ወጣቶች ምክትል ከንቲባው አስረክበዋል።
በቀጣይ ከ400 በላይ የሚሆኑ ያለሥራ የቆሙ አውቶቢሶች በተመሳሳይ መልኩ ለተንቀሳቃሽ ማከፋፈያነት በሚያመች መልኩ ጥገና ተደርጎላቸው በየወረዳው ለወጣቶች እንደሚከፋፈሉ ተገልጿል። ተንቀሳቃሽ ባሶቹ በዋናነት በቅርቡ ግንባታው ሲጠናቀቅ በሰዓት 80 ሺ ዳቦ ለሚያመርተው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈያነት የሚውሉ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
ለዓመታት ለነዋሪው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት የአንበሳ የከተማ አውቶቢሶች አሁንም ለነዋሪው ተጨማሪ የመሥሪያ ቦታ አማራጭ መፍጠራቸውን የገለፁት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ በቀጣይነት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ባሶች ዕድሳት በማድረግ ለወጣቶች አማራጭ የመሥሪያ ቦታ እንዲሆኑ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። የሸገር ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቅርቡም አዲስአበባን እና አካባቢዋን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተጨማሪ ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚካሄድ ከንቲባው ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ም/ ርዕሰ መስተዳር ርስቱ ይርዳው ከህዝቡ ጋር ውይይት አደረጉ
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከደቡብ ኦሞ ዞን ፣ ምዕራብ ኦሞና የካፋ ዞን አመራርና የአርብቶ አደር ተወካዮች ጋር መወያየታቸው ታወቀ፡፡
ሁሉን አቀፍ ዕድገትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሪዎች በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ የተመቸ የመልካአ ምድር አቀማመጥ እንዳለ በመግለፅ ከዚህ ተጠቃሚ መሆን አንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡
አጋጣሚው ቁጭት የሚያሳድር በመሆኑ ቁጭቱን ወደ ሥራ በመቀየር ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ርስቱ ይርዳው የአካባቢው ነዋሪዋችም ያለውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በማቅረብ ዙሪያ ከተሰብሳቢዎቹ ጋር ጥልቅ ውይይት አድርገዋል::
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስት ይርዳው በትናትናው ዕለት በደቡብ ኦሞ ዞን ባደረጉት ጉብኝት የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ እና የአርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ህይወት ለማሻሻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል::
በተመሳሳይ ኢትዮጵያና በኬንያ አርብቶ አደሮች መካከል የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ በደቡብ ኦሞ ዞን የተገነባው የድንበር ላይ የመገበያያ ማዕከልን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የጎበኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያና በኬንያ አርብቶ አደሮች መካከል የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ የተገነባው የገበያ ማዕከል በሁለቱ ሀገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል::
በክልልነት ጥያቄ በደቡብ ክልል በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ ለመቋጨት ዛሬ የመጨረሻ የምርጫ ሂደት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።