አንሞትም እንጂ ስንሞት ምን እንሆናለን ብለን ማሰባችን አንዳንዴ ያለ ነው። መቸም ለእውቀት የተጋ ሰው ቡድሃን ወይም ቡዲዝምን ገለጥ ገለጥ ማድረጉ አይቀርም። የትንሳኤ ቅብብሎሽ (ሪ-ኢንካሬንሽን) ማለት፣ በወዲያኛው ህይወት፣ ሰውየው ድመት፣ ላሚቱ እንቁራሪት ሆና ትመጣለች ማለት እኮ አይመስለኝም። የነፍስ ወገነፍስን ዘላለማዊ ፍሰት (ስትሪም ኦፍ ኮንሸስነስ?) ለማሳየት የታመነ አስተሳሰብ ይመስለኛል። መልካም ነፍስ አታንቀላፋም፣ እንደ ጦጣ ከሟች ወደ ህያው ሥጋ እየዘለለች ትኖራለች እንደማለት ነው። መድረኩን አጥተነው ሳናየው ቀርተን ይሆናል እንጂ የአጼ ቴዎድሮስ ነፍስ ይሄኔ አንዱ ጎረምሳ ውስጥ እየዘለለች ይሆናል።
ጠቅላያችን ሰባተኛ ንጉሥ ትሆናለህ ተብያለሁ ሲሉ ፍርስ ብለን ያልሳቅነው አገር ትፈርሳለች ብለን አይመስለኝም። የሥጋ ዝምድናቸውን ሳይሆን የነፍስ ውክልናቸውን መናገራቸው ነው ብለን በመገመት ሊሆን ይችላል። ነገሥታቱን እውን አስመስለው ከቤተመንግስቱ ሙዚየም ቁጭ ቁጭ ሲያደርጓቸው መቸም ከዚያ ሁሉ ዘመን የአንድ ሰው ነፍስ ውልብ ሳትልባቸው ቀርታለች ብለን አንጠረጥርም። የጃንሆይ ሐውልት የቆመው የተፈሪን ሱሪ ሳይሆን የተፈሪን ነፍስ የለበሰ አንድ ሰው በመኖሩ ሊሆን ይችላል። ደመቀ ይሁን ለማ እኛ ምን አገባን?
አሁን በፈረንጁ አገር ሁሉ በየበረዶውና ቃጠሎው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ እሚጮኸው ዳያስⶒራ ከዚያ ሁሉ የጥንት አርበኛ ሳያውቅ የጨለጠው ከነፍሱ ያስቀመጠው ነገር አለመኖሩን በምን እንከራከራለን? አሁን ከዚያች አገር አንዲት ነገር ያልበላ ያልጠጣ እድሜ ልኩን ሲፈጋና ሲሰደድ የኖረ አገሩን እየጠራ እንዲህ እሚያንቀጠቀጠው ምን ሆኖ ነው? ዋይ ይቺን ይወዳልና ወዲ ምናምን እሚለው ትግራዋይ ወያኔነት ሳይሆን ያ አሉላነት ያ ዮሐንስነት እያደረበት እንደሆነስ ማን ጠየቀ? ኢልመ ሐደራው! እሚለው ኦሮሞ ከነ ጎበና ከነ አባነፍሶ እንደሆነስ እነ ጦና እነ አባጅፋር አባመላ እረ ስንቱ።
ያ አዳራሽ ውስጥ ጠመንጃ ያንደቀደቀው የአማራ ልጅ የማን ነፍስ ይሆን? ከመጣህብኝማ አበንሃለሁ ያለው ብላቴናው አብን ያደረበት አድሮበት ነው እንጂ የትኛው ጦር ሜዳ ገብቶ ሠልጥኖ ነው? ተሰደብኩ ተነቀፍኩ ብሎ ቡራ ከረዩ እማይለው እስኪ ረጋ በሉና አገር ይርጋ እያለ ከምኒልክ ሸንጎ ስብሰባ የተቀመጠ እሚመስለው ተጨናቂ፣ በዚህ የተቀወጠ ዘመን የመታየቱ ምክንያት ምንድነው? ያው ነፍሲቱ በውስጧ ወርሳ እንዳሳደረችው ነውና ክፉ ከፉውን ብቻ እየተመለከተ ክፉ ክፉውን ብቻ እሚያደርግም መታየቱ ነፍስ ከልጓም እየሳበስ እንደሁ ማን አስተዋለ?
ለማንኛውም አርበኝነትም ሆነ መሰሪነት ውርስ እንጂ አዲስ ፈጠራ አይደለም። ኢትዮጵያዊነትም ቢሆን የነበረ የኖረ እንጂ ሰበርዜና አይደለም። ሞተናል ዋጋ ከፍለናል እንደሻማ ቀልጠናል ሥልጣን ይገባናል ካልሆነ ወይ ለምርጫ ወይ ለርግጫ ሮጣለሁ ማለት ልክ አይሆንም። ለሌላው ብርሃን ለመሆን እንደሻማ መቅለጥ ጥሩ ነው። ቀልጠው ሲያልቁ እሚጠፉ ከሆነ ግን ብላሽና ፉርሽ ነው። እስካለሁ ብርሃን ከሌለሁ ጨለማ ይሁን ማለት አለማስተዋል ነው። አዎ ሻማው ብርሃን ሰጭ ነው። ብቻውን በርቶ ራሱን አግንኖ ከሚጠፋ ለሌሎች ሻማዎች ብርሃን እያቀበለ ቢሄድ ብርሃን ይበዛል። ሻማው ለሌላው ሻማ መስጠት ያለበት እሳትን ሳይሆን ብርሃንን ነው።
ክቡራት እና ክቡራን ወገኖቼ ከአባቶቻችን የወረስነው እሳትና መንቦግቦግን ብቻ አይደለም ብርሃንና ጥበብን ነውና እሱንም እንቀባበል። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ማለት እሱ ማለት መስሎኝ። ታዲያስ እኔስ ብሆን የፌስ ቡክ ገጼን ምስል ሻማ ለሻማ ማድረጌ ለዚህ አይደል! አንዳንድ ጊዜ አይቆይም እንጂ በአጠገቤ ውልብ እሚል ነፍስ አያለሁ። ለምሳሌ አንዳንድ ቀን እንደዚህ እላለሁ። እስኪ እምትሆኚውን አያለሁ ሁልሽም የኔው ጉድና ነፍስ ነሽና ሁልሽንም ውድድ አደርግሻለሁ!