የደብረ ታቦር ዮንቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ ዕርቀ ሠላም አወረዱ
ከጥቂት ቀናት በፊት ውዝግብ የተፈጠረበት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እርቀ ሠላም መፈጸማቸው ታወቀ። በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከቀናት በፊት የተወሰኑ ተማሪዎች የሚበሉት ምግብ እንደተመረዘ በመናገራቸው አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ዉዝግብና ተቃውሞው ከተፈጠረ በኋላ የዩኒቨርሲቲው፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ መሰንበታቸው ተገልጿል። ይህን ተከትሎ በተማሪዎች መካከል እርቀ ሠላም በማውረድ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመግባት ስምምነት ላይ መድረሱ ነው የተሰማው።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ባለው ባዬ፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሽ ፊት ለፊት በተማሪዎች መካከል እርቀ ሠላም መፈጸሙን እና ተስተጓጉሎ የነበረው የመማር ማሥተማር ሥራ ወደነበረበት የቀድሞ ሠላማዊ ገፅታ መመለሱን አረጋግጠዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ክለሳ መጠናቀቁ ተገለጸ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ላይ ያደረገውን ክለሳ እንዳጠናቀቀ ገለጸ፡፡
የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲው ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ 8 አመታትን አስቆጥሯል:: በዘርፉ የተማረ ሰው ከማፍራት ጀምሮ በርካታ አላማዎቹን ማሳካት ቢችልም ፖሊሲው የተለያዮ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ አሁን ላይ የተሠራዉ ክለሳ ሥራ ፈጠራን ማዕከል በማድረግ የነበረውን ክፍተት ማሟላት እንደሚችል ተነግሮለታል ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢጅነር ጌታሁን መኩሪያ የፖሊሲ ክለሳው በሳይንስና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ የተመረቁ ወጣቶች ወደ ኢንዳስትሪውና አገልግሎት ዘርፉ ለማስተሳሰር የፖሊሲ አቅጣጫ ስለሚያስፈልግ እንዲሁምዲጅታል ኢኮኖሚውን የመገንባት ሂደት በፖሊሲው ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል ታስቦ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና መስራችና መሪ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ለገበያው በዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ ምርቶችን ማምረት የሚችሉ ኢንዳስትሪዎች ለመገንባ አስተዋጽኦ እንዲኖረውም ታስቦ መሆኑም ተገልጿል።
መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራ ተርታ ለመሰለፍ የሚደርገው ጉዞ መሪ እንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂ እንዲሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ቴክኖሎጅ በባህሪው ፈጣን ለውጥ ስላለው ክለሳውን ማካሄዱ አስፈላጊ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በፖሊሲው ክለሳ ሂደቱ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ በማዘጋጀት የተካተቱ ሲሆን ፣ በቴክኖሎጂ ዙርያ የተሰማሩ ተቋማትና ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ አካላት ተወካዮችና የዘርፋ ተመራማሪዎች ሲሳተፉ መሰንበታቸው ታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) የቴክኖሎጂና ሎጂሰቴክስ ዳይሬክተሯ ሻሚክ ሲሪማን በበኩላቸው ፤ ኢትዮጲያ የኢኮኖሚ ለውጧን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የጀመረቸውን እንቅስቃሴ በማድነቅ የተከለሰውን የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ወደ ተግባር በማስገባት በዘርፉ የሚጠበቀውን ለውጥ እንዲመጣ ተስፋ የተጣለበት ነው ሲሉ በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ላይ ተናግረዋል፡፡
በየመን ያሉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እየተሞከረ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ
በፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በፖለቲካ ሳምንታዊ መደበኛ ጋዘጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አምባሳደሮች ያደረጉትን ገለጻ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገሮች ከአውሮፓ ህብረት ጋር በደረሱት የኮቶኖ የትብብር ስምምነት አንቀጽ 8 መሰረት፤ የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው አጠቃላይ ትብብር አቶ ገዱ ገለጻ ማድረጋቸው ተጠቁሟል። በሌላ በኩል በሳምንቱ ከተከናወኑ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ አንጻር በኦስሎ በኢትዮጵያና በኖርዌይ መካከል በተደረገው ሶስተኛ ዙር የፖለቲካ ምክክር ፣ ሁለቱ ሃገራት ግንኙታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸውን በመግለጫው ላይ ቃል አቀባዮ ትንታኔ ሰጥተውበታል።
ኖርዌይ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ አጠቃላይ የማሻሻያ ስራዎችን እንደምትደግፍና ትብብሯን አጠናከራ እንደምትቀጥል መግለጿን ያመላከቱት አቶ ነብያት ፤ በሁለቱ ሃገራት በተደረገው ውይይት በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተተገበሩ ያሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ማሻሻያዎችን በተመለከተም ገለጻ ተደርጓል፡፡
ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንጻር-በሱዳን ህዝቦች ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ምክር ቤት ሴክሬታሪ ጀነራል ሳልዋ ሞሃመድ ማህጎብ የተመራ ከ50 በላይ አባላት ያሉት የሱዳን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የ3 ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ መግባቱንም ከጋዜጣዊ መግለጫው መረዳት ተችሏል።
ቡድኑ በዛሬ ጠዋት ቆይታው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ጋር ውይይት ማድረጉም ተሰምቷል። በቆይታውም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንደሚወያይ እና የተለያዩ ቦታዎችን እንደሚጎበኝ ነው የተነገረው፡፡በተጨማሪም ዛሬ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቲያትር በኢትዮጵያ እና በሱዳን የሙዚቃ ባለሙያዎች በሚዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ እንደሚታደም ታውቋል።
በተመሳሳይ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራና ከከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከምሁራን፣ ከስነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ከሚዲያ አካላት የተውጣጣ ከ50 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ወደ ዩጋንዳ እንደሚጓዝ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡
ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንጻር- መንግስት ለዜጎች በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መጠለያ ውስጥ የነበሩ 100 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በመተማ በኩል በሁለት አውቶብስ በትናንትናው ዕለት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መደረጉን የገለጹት አቶ ነቢያት፤ በየመን ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው የነበሩ 103 ዜጎች የጀቡቲ ኤምባሲን ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር እና ከጅቡቲ መንግስት ጋር በመተባበር ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁንም ይፋ አድርገዋል፡፡
በታንዛኒያ 1 ሺህ 300 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለማስመለስ ሥራው በሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑንና በሌሎች ቦታዎች በተለይም በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ችግር ላይ እንዳይወደቁ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ከመግለጫው ሰምተናል::
የአማራ ክልል ሠላምን ለመጠበቅ፤ ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
የአማራ ክልልን ሠላም ለማስጠበቅ የክልሉ ህዝብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የክልሉ ሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ አበባው ውቤ ጥሩ አቅርበዋል፡፡
“የክልሉ ሰላም በህዝቡ መዳፍ ውስጥ ይገኛል ” ያሉት አመራር፣ በአንዳንድ የክልሉ ቦታዎች ሃገር ሰላም መሆኑን የማይፈልጉ አካላት ኅብረተሰቡን በዘር እና በሃይማኖት ለማጋጨት ትንኮሳ ያደረጉባቸው ግዜያቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የሰው ህይወትና ንብረት የጠፋ ቢሆንም የክልሉ ህዝብ የብሔርና ሃይማኖት ልዩነት ሳይነጥለው ግጭቶቹን በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ሓላፊው ገልጸዋል፡፡
በሁከትና በረብሻ የግል እና የቡድን አጀንዳቸውን ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የክልሉ ወጣቶች በአስተዋይነትና በሰከነ መንገድ ነገሮችን ሊፈትሹ ይገባዋል ብለዋል አቶ አበባው ፤ በተለይም ምሁራን እና የትምህርት ተቋማት ስለ ክልሉ ሰላም ሊተጉ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ አልፎ አልፎ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት የፀጥታ አካላት በትዕግስትና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሓላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም መክረዋል፡፡
ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ገንዘብና ጌጣጌጥ ኤርፖርት ላይ ተያዘ
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን የውጭ ሀገር ገንዘብና የብር ጌጣጌጦች መያዛቸው ተሰማ።
ትናንት ሃሙስ ህዳር 11 ቀን ኢትዮጵያዊ በሆነ መንገደኛ 86 ሺህ 350 ዩሮ እና 89 ሺህ 90 የስዊዝ ፍራንክ ከአዲስ አበባ ወደ ውጭ ሀገር ሊወጣ ሲል መያዙ ታውቋል። ተጠርጣሪው ገንዘቡን በጉዞ ሻንጣዎቹ ውስጥ በያዛቸው ልብሶች በመደበቅ ይዞ ሊወጣ ሲል ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
በተያያዘ ዜና ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሁለት ኤርትራዊ መንደኞች ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ ጃኬት ውስጥ የብር ጌጣጌጦችን ደብቀው ወደ አዲስ አበባ ሊያሳልፉ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የጉምሩክ ኢንተለጀንስ ሠራተኞች በተደረገ የመንገደኞች ቅድመ ስጋት ትንተናና ክትትል መሠረት በተደረገ አካላዊ ፍተሻ መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በፍተሻው 17 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም የሚመዝን የተሠራና ያልተሰራ ግምታዊ ዋጋው 716 ሺህ ብር የሚሆን የብር ጌጣጌጥ የተያዘ ሲሆን፤ በድምሩ በምንዛሪ ዋጋ ከ5 ሚሊየን 610 ሺህ ብር በላይ የሆነ የውጭ ሀገር ገንዘብና 716 ሺህ ብር የሚገመት የብር ጌጣጌጥ ተይዟል።