ጸብ እና ሽምግልና || ያሬድ ኃይለማርያም

ጸብ እና ሽምግልና || ያሬድ ኃይለማርያም

በተደጋጋሚ እንዳስተዋልኩት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ግጭቶች ከተከሰቱ እና ብዙ ጉዳት ካደረሱ በኋላ በመንግስት ሚዲያዎች ሁሌም ተደጋግሞ የሚታይ አንድ ነገር አለ። በተጋጪዎች ወገኖች ያሉ የአገር ሽማግሌዎች በአዳራሽ እንዲሰባሰቡ ይደረግና እርቅ፣ ምክክር እና ስለ ተጋጪዎቹ ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር እና የቆየ ውህደት ይወሳል፣ ጥናት ይቀርባል፣ ምርጥ ምርጥ ንግግሮች እና ጥቅሶች ከዚህም ከዛ ይወረወራሉ። እኔን ግራ የሚገባኝ ታዲያ መቼ ሽማግሌዎቹ ተጣሉና ነው መንግስት እነሱን የሚሸመግለው። ሽማግሌዎቹን የመፍትሔ አካል ማረግ አንድ ነገር ሆኖ እነሱን ማስታረቅ ምን ይሉታል። በመጀመሪያ የግጭቱ ምንጭ ምንድን ነው? እነማን ናቸው ከግጭቱ ጀርባ ያሉት? እነማን ናቸው ሜዳ ላይ የተጋጩት? ሽማግሌዎቹ ያላቸው ተደማጭነትስ ምን ያህል ነው? እነዚህን ሁሉ ነገሮች በቅጡ ማየት ተገቢ ነው።

ግጭት በተነሳ ቁጥር የአገር ሽማግሌዎችን በየሆቴሉ ሰብስቡ ማሳሳም ያልበላን እንደማከክ ነው። ስንቴ ነው በአማራ እና በኦሮሞ፣ በኦሮሞ እና በጋሙ፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል፣ ወዘተ … መካከል እርቅ እና ምክክር የሚደረገው። ከዛም አፍታ ሳይቆይ ተመሳሳይ ግጭቶችስ የሚከሰቱት። መንግስት ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ቀድሞ ለመገመት፣ እንዳይከሰቱ ለማስቀረት፣ ሲከሰቱም በአፋጣኝ እንዲቆሙ ለማድረግ፣ የጉዳት መጠኖችን ለማስቀረት እና ለግጭት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በቅጡ በባለሙያ አስጠንቶ በዘለቄታው እንዲቀረፉ ለማድረግ የሚያስችለውን ስልት ነድፎ ካልተንቀሳቀሰ፤ በግጭቱ ከደረሰው ጉዳት አልፎ በየሆቴሉ ለፕሮፓጋንዳ በሚያመች መልኩ ሽምግልና እያሉ ገንዘብ እና ጊዜ ማጥፋት ሌላ አገራዊ ጉዳት ነው። እንዴት ሁሌ አንድ አይነት ስልት እየተከተሉ ያ አልሰራ ሲልስ ሌላ የተሻለ አማራጭ አይታሰብም?

ሌላው ዋና ቁምነገር ሽምግልና የሚሰራው ግጭቱ በሁለት ጨዋዎች መካከል ሲሆን ነው። ከተጋጪዎቹ መካከል አንዱ ወይም ሁለቱም ጨዋነት የራቃቸው ከሆነ ሽምግልና ገደል ይገባል። በመንጋዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ግን በማህበረሰብ መካከል እንደተፈጠረ ግጭት ቆጥሮ ሽምግልና መጀመር በራሱ ግን ለነገሩ የተሰጠውን የተዛባ ግንዛቤ ነው የሚያሳየው። የመንጋ ጸቡ ከሕግ እና ከዜጎች መብትና ነጻነት ጋር ነው። ለዛ ደግሞ መፍትሔው ሕግ እንጂ ሽምግልና አይደለም። ባይሆን ትውልድን የማነጽ ሥራ በሰፊው ሊሰራበት ይገባል።

LEAVE A REPLY