የአገራችን ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ መሆኑን ስመለከት እንደ ሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉልቤ በሐዘን ይሞላል፡፡ ዶ/ር ዓብይን እጅግ ተስፋ አድርገናቸው የነበረ ቢሆንም፣ ዙፋናቸው መርጋት ተስኖት በከባድ ማዕበል እንደተመታ መርከብ እየተንገጫገጨ ይገኛል፡፡
ለነገሩ አውቆ አበዶች በበዙበት ዘመን ዓብይ ብቻቸውን ምን ያድርጉ? እሳቸው አንድ ዕርምጃ ወደፊት በተራመዱ ቁጥር ሁለት ዕርምጃ ወደኋላ የሚጎትታቸው በዛ፡፡ ወፈ ሰማያት አክቲቪስት ነኝ ባይ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ፣ በማያውቀው ጉዳይ እየገባ ሲፈተፍት ይውላል፡፡ ዓብይ ሥልጣናቸውን ለመንጠቅ የሚመኘውን ሁሉየድሮ የአገራችን ነገሥታት ተቀናቃኝ ወንድሞቻቸውን ጠራርገው ወህኒ ይወረውሯቸው እንደነበረው እንዳያደርጉ ጊዜው የዴሞክራሲ ሆነ፡፡ በጣም አስቸጋሪነው፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ተስፋ አላት? ማን ሊያድናትስ ይችላል? ወደ ታች ወርጄ በጎጥና በብሔር ማሰቡን ባልወደውም የወቅቱ ሁኔታ ስለሚያስገድደኝ ቃላቱን በግድ እጠቀማለሁ፡፡ አንዱን ብሔር ከሌላው የማበላለጥ ዓላማ እንደሌለኝ ግን ከወዲሁ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡
አማራ ኢትዮጵያን አሁን ከገባችበት ማጥ ሊታደጋት ይችላል? በእኔ እምነት አይችልም፡፡ ምክንያቱም ያወቁና የበቁ የመሰላቸው የ1960ዎቹ የአማራ ተማሪዎች በማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍና ተለክፈው የራሳቸውን ብሔር ጨቋኝ ሌላውን ደግሞ ተጨቋኝ አድርገው በመሳል የፈጠሩት ትርክት፣ ውሎ አድሮ አማራ በጠላትነት እንዲፈረጅና ተደማጭነት እንዳይኖረው በማድረጉ ነው፡፡ ‹ውሻ በቀደደው ጅብ› ይገባል እንዲሉ፣ አማራን በጭፍን ለሚጠሉት ትልቅ ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡ እነዚያ አብዮተኛ ወጣቶች ባመጡት ጦስም ኢትዮጵያን በጥበብና በአርቆ አስተዋይነት በሰላም ሲመሯት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ባለሥልጣኖቻቸው ያለ ፍርድበግፍ ተገደሉ፡፡ ይህም ፈጣሪን ከማሳዘን አልፎ የታሪክ መሠረት እንዲነቃነቅ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ መፀፀትና ንስሐ መግባት ያባት ቢሆንም ትኩረት የሰጠው ግን የለም፡፡ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነውና እየሆነ ያለውይኸው ይመስለኛል፡፡ በሰኔ 2011 ዓ.ም. በክልሉ መዲናበባህር ዳር የተከሰተው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያጥሎት ያለፈው መጥፎ ጠባሳም ሌላው ጣጣ ነው፡፡በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ወይም በደንባራ በቅሎቃጭል ተጨምሮ እንደ ማለት ነው፡፡
ትግሬስ ሊያድናት ይችላል? አይመስለኝም፡፡ ለምን? ቢባል ሕወሓት ብዙ ነገር ስላበላሸና ተመዝኖ ቀልሎ ስለተገኘነው፡፡ ብዙዎች እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ብለው መስዋዕት የከፈሉለትን ትግል ወዳልሆነ አቅጣጫመራው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንዲሟሽሽና ጎጠኝነት እንዲጎለብት አደረገ፡፡ ሙስና አገሪቱን ጋጣት፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሰማይ ጥግ ደረሱ፡፡ ነገሩ ሄዶ ሄዶ ሕወሓት እንዲተፋ ከማድረጉም በላይ፣ ትግራይ በጥርጣሬ እንድትታይ አደረጋት፡፡
ኦሮሞስ? ‹‹ለዘመናት ኢትዮጵያን የመምራት ዕድሉን አግኝቼ አላውቅምና ተራው ለእኔ ሊሰጠኝ ይገባል›› ሲል የነበረው ኦሮሞ፣ በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ይህን ታላቅኃላፊነት በመረከቡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተደስቶ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለውጡ እንዲመጣ በተለይ ዶ/ር ዓብይና አቶ ለማ መገርሳ የተጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚረሳ አይደለም፡፡ በርካታ አመርቂ ተግባሮች መገኘታቸውም አይካድም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓለምአቀፍ የኖቤል ሽልማት እንዲያሸንፉ አስችሏል፡፡ ነገር ግንአንዳንድ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች የሚያራምዱት አፍራሽ ድርጊት የተገኘው ለውጥ ጥላሸት እንዲቀባናበአቃፊነቱ የሚታወቀው ኦሮሞ የማይመጥነው ስም እንዲሰጠው እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በምናባቸው የሚስሉት አረንጓዴ ሳር እንጂ ገደሉ በጭራሽ ሊታያቸው አልቻለም፡፡ ልጓም በሌለው የመንጋ ፖለቲካ እየተመሩ እጃቸው በንፁኃን ደም እየተጨማለቀ ነው፡፡ ይህም ድርጊት ሌላው ቢቀር የታሪክ ባለቤት በሆነው ፈጣሪ ዘንድ በበጎ እንደማይመዘገብ የታወቀነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሕዝቡ በዶ/ር ዓብይ ላይ የነበረው እምነት በመሸርሸር ላይ ስለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ኦሮሞ አገሪቱን ወደከፍታ ሊያወጣት እንደማይችል አያጠያይቅም፡፡
ታዲያ ከላይ የተጠቀሱት ‹‹ትልቅ ነን›› እያሉ የሚመፃደቁት ብሔረሰቦች ፈተናውን ማለፍ ካልቻሉ፣ ይህችን መከረኛ አገር ማን እንደገና በእግሯ ሊያቆማትና ከውርደት ሊያወጣት ይችላል? አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሁለት ነገሮች መፍትሔ መስለው ይታዩኛል፡፡ እነሱም ድብልቅ የሆነው ዜጋና ‹‹አናሳ›› ወይም አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ ታሪክን አስደግፌ ትንሽ ለማብራራት ልሞክር፡፡
ድብልቅ ዜጎች
ድብልቅ ስል ከተለያዩ ብሔሮች የተወለዱ ማለቴ ነው፡፡እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ አለ፡፡ እንዲያውም ከሌላው ጋር ያልተቀላቀለ ‹‹ንፁህ›› ዘር አይገኝም ነው የሚባለው፡፡ በእርግጥ ባለፉት 30 ዓመታትበነበረው የዘር ፖለቲካ ድብልቅ ለሆኑት ዜጎች አማራጭስላልነበረ፣ ሕዝቡ የግድ አንዱን ብሔር እንዲመርጥ ይገደድ ነበር፡፡
ድብልቅ የሆነ ሁሉ ለአገራዊ አንድነት ይጨነቃል ብሎለመደምደም ቢያስቸግርም (ምሳሌ አሁን አገሪቱንእየበጠበጡ ካሉት ውስጥ ድብልቅ የሆኑ ይገኙበታል)፣አብዛኛው ለአገሩ ቀናዒ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ታሪካችን ለዚህ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ከሚያንገበግባቸውና ሕዝቡን ያለ አድልዎ በእኩል ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ድብልቅ መሪዎቻችን ውስጥ እምዬ ምኒልክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና መንግሥቱ ኃይለማርያም ይገኙበታል፡፡ ዶ/ር ዓብይ አህመድም ከዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው፡፡
‹‹አናሳ›› ብሔረሰቦች
‹‹አናሳ›› ብሔረሰቦች የሚባሉትን ሳስብ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑትና ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የጋምቤላውኦባንግ ሜቶ፣ የጉራጌው ብርሃኑ ነጋ፣ ‹‹እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ›› ያሉት አፋር ወንድሞቻችን፣ ከመድረክ ለምን እንደ ጠፉ ባላውቅም የቤንሻንጉል ጉምዙ ያረጋል አይሸሹም፣ የሐድያው በየነ ጴጥሮስ፣ የሶማሌው ሙስጠፋ ዑመር፣ ወዘተ ትዝ ይሉኛል፡፡ ዘርዝሬ አልጨርሳቸውም እንጂ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ከምባታ፣ ጠንባሮ፣ አገው፣… በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ናቸው፡፡ እስቲ እነሱም ይደመጡ፡፡ አገር የመምራት ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡ እነሱ ለዚች አገር አድዋ ላይ አልተሰውምን? ካራማራ ላይ አጥንታቸውን አልከሰከሱምን?
ታሪክም እንደሚያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ ተዓምርየሚሠሩት ያልተገመቱ ሰዎች ናቸው፡፡ በጥንት ዘመንበአገዎች ሲመራ የነበረውን የዛግዌ ሥርወ መንግሥትእዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ መንግሥት የአክሱምሥርወ መንግሥትን ባጠፋችው በዮዲት ጉዲት እጅግፈራርሳ የነበረችውን አገር መልሶ ከመገንባቱም በላይ፣ዛሬ ድረስ ዓለም የሚደነቅበትን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን በረቀቀ ጥበብ ከአለት ፍልፍሎ መሥራትየቻለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት መሐንዲስ እንደሆኑ የሚነገርላቸውየአፄ ቴዎድሮስ የኋላ ታሪክም ከቁጥር የሚገባአልነበረም፡፡ ለቁም ነገር በቅተው በመሳፍንት አገዛዝሥር ወድቃ አበሳዋን ስታይ የነበረችውን አገር አንድያደርጋሉ ተብለው አልታሰቡም፡፡ ነገር ግን የማይቻልየሚመስለው እንዲቻል አደረጉ፡፡ ለትውልድ የሚተርፍታሪክም ሠርተው አለፉ፡፡
ማጠቃለያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ማሻሻልያለባቸውን አርመው በያዙት ራዕይ በፅናት ቢገፉበትአሁንም አልረፈደም ባይ ነኝ፡፡ ፈጣሪም ከእሳቸው ጋርነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙ ሰው በዚህ እንደሚስማማአሌ አይባልም፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኃጢያት ውጤት የሆነውንብሔርን የሚያመልኩትን ወደ ጎን ትቶ፣ ወደ ሌሎችድብልቆችና ሲናቁ ወደ ነበሩት ‹‹አናሳ›› ብሔሮች ፊቱንማዞር አለበት፡፡ እንደ እነ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጊዜውየጉልበት አይደለምና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አገርየመምራት ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ፡፡ ቸርያሰማን!