በኢትዮጵያ የፕሬስ ገዞ ውስጥ ትልቅ አሻራ ከጣሉት ትንታግ ጋዜጠኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የሆኑት አምባሳደር አሀዱ ሳቡሬ የቀብር ስነስርአታቸው በትላንትናው እለት በአሜሪካው የካሊፎርኒያ ግዛት፣ በሎሳንጀለስ ከተማ በሚገኘው የድንግል ማሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን ፍትሐት ጸሎት የተደረገላቸው ሲሆን የተለያዪ አሳዛኝ እና አስገራሚ ገድሎቻቸው በቤተሰቦቻቸው እና በወዳጅ ዘመዶቻቸው ከተነገሩ በሁዋላ በሆሊይ ክሮስ የመካነ መቃብር ስፍራ በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቋል።
በተወለዱ በ94አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ብዙዎች “አባባ” እያሉ የሚጠሯቸው ስለ አምባሳደር ጋዜጠኛ አሀዱ ሳቡሬ ከተላለፉት በርካታ ምስክርነቶች መካከል የሚከተለው የግጥም ድርድር ይገኛል:-
የተባለለት ሰው አሃዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ፣
ትልቅ ሰው እጥተሻል እሪ በይ ሃገሬ፣
ለተክለጊዮርጊስ በቅጡ እዘኚለት ከል ልበሺና፣
ሥራውን ጨርሶ ወደ አባቱ ሲሄድ የዘመናት ጀግና።
ጋዜጠኛም ሆነው ኢትዮጵያን በአያሌው ይወዱ ነበር፣
አምባሳደር ሆነው ወክለው አስከብረው ይኖሩ ነበር፣
ታስረው ሲማቅቁም ኣልካዷትም ነበር ፣
ለኢትዮጵያ ያላቸው አክብሮትም ፍቅርም አብሮ ተቀበረ።
አሁን ጌዜዎት ነበር ምስክር መሆኛ፣
ወጣቱ ተለክፎ በዘውግ መጋኛ፣
ዘረኝነት ውጦት አእምሮው ላሽቆበት ሆኖ በሽተኛ፣
ሃገርዎን ሲያምሳት እንደ ባእድ አርበኛ።
ጥቁር ጤፍ ነጭ ጤፍ ማኛ እንዳልበላ፣
አሁን እርስ በርሱ ወገን ተበላላ፣
እስቲ ቀና ብለው ይዩትማ ዛሬ፣
ምክርዎን ይለግሱት ይለፉ በድሬ።
በባእድ አገር ወደ ሎሳንጀለስ መጥተው፣
ቀሪውን እድሜውን አባት አያት ሆነው፣
እውቀቱን ለመቅሰም የእድሜ ገደብ የለው፣
ምሳሌ ሆኑልን ትምህርት ቤት በ75አመት ገብተው።
በድንግል ማርያም ቤ/ን ቆመው አሜን፣ አሜን ፣አሜን ሲሉ፣
በዓል ነው አዘቦት እሁድ ነው አይሉ፣
ከፈጣሪዎ ጋር ድምፅዎን ከፍ አድርገው ይነጋገራሉ።
ዲፕሎማት ደራሲ ጋዜጠኛ ነዎት፣
ሃይማኖት ጠባቂ ታላቅ አባት ነዎት፣
የሚወዱት አምላክ በእቅፉ ይቀበሎት፣
መላእክት አጅበው ያድርስዎ ፅባዖት።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር።
* የድሬዳዋው፣ የአ/አበባው፣የሎሳንጀለሱ ፣የኢትዮጵያ ብርቅዬ፣ሃቀኛ ልጅዋ ለተከበሩ አባባ አሀዱ ሳቡሬ :-ተጻፈ ከታዛዥ ልጅዎ ከወ/ሮ ቅድስት ነጋሽ እኤእ11/23/19 ።
|| በታምሩ ገዳ ||