ጠ/ሚ ዐቢይ ከአሊባባ ባለቤት ጋር ተወያዩ፤ ካምፓኒው ከኤርምያስ አመልጋ ጋር የነበረው ውል አልታወቀም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከግዙፉ የቻይና ካምፓኒ “አሊባባ” ባለቤት ጃክ ማ ጋር መወያየታቸው ታወቀ። በውይይቱ ላይ ጃክ ማ በኢትዮጵያ ለመክፈት ባሰቡት ዓለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክ መገበያያ ዙሪያ ሠፊ ምክክር አድርገዋል።
መገበያያው የሀገሪቱን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ የሚደግፍ ነው ተብሎለታል። አሊባባ በኢትዮጵያ ለመክፈት ያሰበው ዓለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክስ መገበያያ፥ የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ ዲጂታል ስልጠና፣ ቱሪዝም እና ሎጂስቲክስን ያካተተ እንደሆነም ታውቋል።
የአሊባባ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በቀላሉ በዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅ ያግዛል ተብሎ የታመነበት ሲሆን፤ በተለይም አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በር ይከፍትላቸዋልም ነው እየተባለ ያለው።
የጃክ ማ ጉብኝት በአሊባባ ዋና መሥሪያ ቤት ሀንግዙ ቻይና ባለፈው ዓመት ከተደረገው ውይይት የቀጠለ ነው ከጃክ ማ ጋር በርካታ ቻይናውያን የንግድ ልዑካን አብረው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ተነግሯል።
አሁን በእስር ቤት ውስጥ የሚገኘው አቶ ኤርምያስ አመልጋ ከአሊባባ ጋር የስራ ግንኙነት መፍጠሩን እና የንግድ እንቅስቃሴ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል። አቶ ኤርምያስ ከአሊባባ ካምፓኒ ጋር የነበረው ውል እስከሁን በግልጽ ባይታወቅም የእስር ሁኔታው ግን ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ሲያነጋግር መቆየቱ አይዘነጋም።
በዮሐንስ ቧያለው የተማሩ የአማራ ክልል የሥራ ሓላፊዎች ዋሽንግተን ዲሲ ገቡ
የአማራ ክልል የሥራ ሓላፊዎች ልዑክ በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ድጋፍ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ዋሺንግተን ዲሲ ገብቷል።
በአዴፓ ቁልፍ ሰው አቶ ዮሐንስ ቧያለው የተመራው የአማራ ክልል የሥራ ሓላፊዎች ልዑክ ዋሺንግተን ዲሲ ሲደርስ፥ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ እና በዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አደረጃጀት ተወካዮች አማካይነት አቀባበል እንደተደረገለት ታውቋል።
በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ጋር በአልማ ድጋፍ እና በወቅታዊ የክልሉ እና የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የጉዞ ፕሮግራም እንደሆነም ነው ተገልጿል። በዚህ መሠት በክልሉ ልማት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
የአማራ ክልል የሥራ ሓላፊዎች ልዑክ በአሜሪካ ቆይታው በዋሺንግተን ዲሲ፣ አትላንታ፣ ኦሃዮ፣ ሚኒሶታ፣ ዴንቨር፣ ሲያትል እና ሌሎችም ከተሞች ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ልዑኩ ከሰሜን አሜሪካ ቆይታው በኋላ ወደ ካናዳ ቶሮንቶ በማምራት ተመሳሳይ ውይይቶችን እንደሚያካሂድ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ::
የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ፓርቲ ውህደቱን ለመቀላቀል በሙሉ ድምፅ ወሰነ
ሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅትና የመደመር ፖለቲካ አቀንቃኞቹ ወደውህደት ለመምጣት ያሳለፉትን ውሳኔ ተከትሎ አጋር ድርጅቶችም ለውህደቱ እየተዘጋጁ ነው:: ይህን ተከትሎ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ሀገራዊ ውህድ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ዛሬ በአሶሳ ከተማ ባካሄደው አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔ የኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ውህድ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲን እንደሚዋሃድ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አድጎ አምሳያ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር “ክልሉን በመራባቸው ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግቧል” ከማለታቸው ባሻገር ፤ ፓርቲው እንደ ሀገር ሊያበረክት የሚገባውን አስተዋጽዖ ለማበርከትም ሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በባለቤትነት ለመሳተፍና ለመወሰን ዕድል ተነፍጎት መቆየቱን ገልጸዋል።
ለውጡን ተከትሎ ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉት ውህደት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ሁሉም ዜጎች ያለመድሎ በሀገራቸው ጉዳይ በጋራ ለመምከርና ለመወሰን የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ አድጎ ጠቁመው ፤የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ህዝቦች በሕብረ ብሔራዊ ጥላ ስር ሆነው ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር ተደምረውና ተባብረው ለላቀ የሀገር ብልጽግና እንዲተጉ የሚያስችል ነው ሲሉ መስክረዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው“ውህደቱ በሀገር ጉዳይ ባይተዋር ከመሆን ይልቅ በጋራ የመምከርና የጋራ ውሳኔ ለማሳረፍ ከማስቻሉም በላይ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረግጥ ነው” በማለት ተናግረዋል:: የክልሎችን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብት ይበልጥ በማጠናከር ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት በጋራ ሆነው ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የቤጉህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር ደግሞ ባለፉት ዓመታት ከነበሩት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ውጪ የሚገኙ ድርጅቶችን “አጋር” የሚለው አሠራር አግላይ በመሆኑ፤ በሀገራቸው ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል ሲሉ አምባገነኑ ኢሕአዴግ ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ያለፉትን ግድፈቶች በማረም ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ቅቡልነት ያለው ዘላቂ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እንደሚያስችል ያላቸውን ዕምነት አመላክተው ፤ ቤጉህዴፓ በድርጅታዊ ጉባዔው የውህደቱን አስፈላጊነት ያረጋገጠ ከመሆኑ በተጨማሪ በቀጣይም ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የተጀመሩ በርካታ ሥራዎችን ለማስቀጠል የጋራ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በኢትዮጵያ ማስጀመር የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ ተደረገ
ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በኢትዮጵያ ማስጀመር የሚያስችል መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ሆኗል። ግብይቱን በኢትዮጵያ ማስጀመር የሚያስችለው ስምምነት ከአሊባባ ካምፓኒ ጋር በተፈረመ ስምምነት ነው ይፋ የሆነው።
ይህን ስምምነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከአሊባባ ተወካይ ጋር በመፈራረም ቀጣይ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን እውን አድርገውታል።
በስምምነቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በበርካታ ዘርፎች እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቁመው ቴክኖሎጂው ከሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር እየተያያዘና እየተቆራኘ እንደሆነም አስታውቀዋል።ቴክኖሎጂው አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር ለሃገራትና ህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍ ያለ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር ከአሮጌው ወደ አዲሱ መሸጋገሪያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሐመቴክኖሎጂ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር ከአሮጌው ወደ አዲሱ መሸጋገሪያ መሆኑን ጭምር አስረድተዋል።
ግብይቱ በታዳጊ ሃገራት የግሉን ዘርፍ ተሳታፊነት በማሳደግ ፣ በተለይም ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፥ ዓለም አቀፍ የገበያ መረጃዎችን በማድረስ በኩል ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድግ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 አመታት ከአፍሪካ በዲጂታል ኢኮኖሚው መስክ ቀዳሚ ከሆኑ 5 ሃገራት መካከል አንዷ ለመሆን የያዘችውን እቅድ ለማሳካት አጋዥ ነው ሲሉ መስክረዋል።
የግብር ስርዓቱን ቀላልና ግልጽ በማድረግ እና የደንበኞችን ስጋት በመቀነስ አነስተኛ ግብር እንዲኖር እንደሚያግዝም ቴክኖሎጂው የላቀ ሚና እንደሚጫወትም አብርርተዋል።
የአሊባባ መስራችና ባለቤት ጃክ ማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለዲጂታል ቴክኖሎጂው የሰጠችው ትኩረት፤ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በኢትዮጵያ ለማስጀመር እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ኢትዮጵያ የምታመርታቸውን ምርቶች በአሊባባ አማካኝነት በዓለም ገበያ ግብይት እንድትፈፅም የሚያስችል እንደሆነ ከወዲሁ እየተነገረለት ይገኛል።
የትዊተር ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ ኢትዮጵያ ገብተዋል
የትዊተር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለአንድ ወር በቆየው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ እና ጋናን የጎበኙ ሲሆን የመጨረሻ መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ አድርገዋል፡፡
ከዚህ የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጠሪ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ዋና ስራ አስፈፃሚ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ሽፋን አግኝቷል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው ጃክ ፓትሪክ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከቴክኖሎጂ ንግስቷ ቤተልሄም ደሴ እና የአፍሪካ ቴክ ኔክስት አንደኛው መስራች ከሆነው ኖኤል ዳንኤል ጋር ውይይቱ ያደርጋሉ ተብሎ እየተገለጸ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከሌሎቸ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር ሰፊ ቆይታ ይኖራቸዋል፡፡
የትዊተር ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ በአሜሪካ የኮሙፒውተር ፕሮግራመር እና ኢንተርኔት ሥራ ፈጣሪ እንዲሁም ስኩዌር የተባለው የሞባይል የክፍያ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ነገ ከጥቂት ቀናት በፊት የትዊተር ሓላፊ ለሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ መዘገቡ ይታወሳል::
መደመር መጽሐፍ ትናንት በናይሮቢ ቢመረቅም ሽያጩ በእጅጉ ወርዷል
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ “መደመር” መፅሐፍ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በትናንትናው ዕለት ተመርቋል:: የጠቅላይ ሚኒስትሩን መጽሐፍ ያስመረቀው ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው። ናይሮቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያን እንዲሁም የሌሎች ሃገራት ዲፕሎማቶች በምርቃቱ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።
መጽሐፉ እስካሁን ለገበያ የቀረበው በአማርኛና ኦሮምኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያውያን ውጭ ሌሎች ዲፕሎማቶችገዝተው ለማንበብ ያልቻሉ ቢሆንም፣ የመጽሐፉን ይዘት በተመለከተ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ባለሟሎች፤ አማካሪዎችና ሌሎችም የፌደራል መሥሪያ ቤቶች የሥራ ሓላፊዎች በእንግሊዝ አፍ ወይም ቋንቋ ማብራሪያ መስጠታቸው ታውቋል።
መጽሐፉ አሁን ያለውን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር አጋዥ ነው ያሉት ማብራሪያ ሰጪዎቹ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ ከተለያዩ እሳቤዎች ሃሳብ ያዋጣ በመሆኑ ሚናው በተግባር የሚለካ ለውጥን ለማምጣት ዕድል ይፈጥራል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
መደመር መጽሐፍ በናይሮቢ እንዲመረቅ ያስተባበሩት አምባሳደር መለስ አለም “ኬንያዊያን ጎረቤቶቻችን ሳይሆኑ ወንድሞቻችን ናቸው፤ ለዚህም ነው መጽሐፉን እዚህ እንዲመረቅ የሻተ ነው” ካሉ በኋላ “በአሁኑ ወቅት የሚገጥሙን ችግሮች ማንኛውም በለውጥ ሂደት ላይ ያለ አገር የሚገጥመው ችግር ነው ፤ ይህንንም በቀላሉ ለማለፍ መደመር መጽሐፍ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል” ብለዋል።
መጽሐፉ በኢትዮጵያ በ13 ከተሞች ከሳምንታት በፊት መመረቁ አይዘነጋም። ከአገር ውጭ ሲመረቅ ደግሞ ከአሜሪካ ቀጥሎ የናይሮቢው ፕሮግራም ሁለተኛው ነው። በናይሮቢው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ‘መደመር’ መጽሐፍ ለገበያ የቀረበ ሲሆን 3 ሺህ የኬንያ ሺልንግ ወይም ደግሞ 30 የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል:: አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ገበያ ወደ 890 ብር ገደማ ያወጣል።
ዋጋው መጽሐፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሸጥበት በ3 እጥፍ የጨመረ መሆኑና መጽሐፉ በሃገር ውስጥ ቋንቋዎች ብቻ ለገበያ መቅረቡ ለሸመታው ማሽቆልቆል ምክንያት በመሆኑ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብዙም ሽያጭ እንዳልተፈፀመ ቢቢሲ ዘግቧል::
በሱዳን በኩል የገባ 189 ሽጉጥ ከበርካታ ጥይቶች ጋር ጎንደር ላይ ተያዘ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በህገ-ወጥ መንገድ 189 ቱርክ ሠራሽ ሽጉጦችን ከጥይቶች ጋር ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰማ።ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው የወረዳው ማዕከል በሆነው በሳንጃ ከተማ በሚገኘው የፍተሻ ኬላ ላይ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ጸጥታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤቱ ሓላፊ አቶ አንተነህ ታደሰ አስታውቀዋል።
ትላንት ከቀኑ 6፡30 ላይ በፍተሻ ኬላው በተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር ከተያዘው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በተጨማሪም 40 የሽጉጥ ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-44463 አዲስ አበባ በሆነ ፒክአፕ መኪና የጦር መሳሪያዎቹን ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም ከሓላፊው ገለጻ መረዳት ተችሏል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው ከሱዳን ሀገር በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በኩል በድብቅ ተጓጉዞ የመጣ መሆኑንም አቶ ታደሰ ሲናገሩ ተደምጧል።