ህወሓት ውህደቱን አስመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ዶ/ር ደብረፂዮን ገለፁ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በቅርቡ ስለ ኢሕአዴግ ውህደት የወሰዱትን አቋም አስመልክቶ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ እንደሚጠራ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገለፁ።
ም/ ርዕሰ መስተዳደሩ ዶ/ር ደብረጺዮን በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለሀገር አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሠሞኑን አወዛጋቢ የሆነውን የኢሕአዴግን ውህደት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ህወሓት በትግራይ ሕዝብ መስዋዕትነት የተገነባ መሆኑን የገለፁት አወዛጋቢው የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ በጉባኤው የህወሓት ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ስለ ውህድ ፓርቲ የወሰዱትን አቋም አባላቱና ህዝቡ እንዲመክሩበት ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል።
“የሥራ አስፈጻሚውና ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደው አቋም ትክክል መሆኑና አለመሆኑ የጉባኤው ተሳታፊዎች ተወያይተው ይደግፋሉ አልያም የራሳቸውን አቋም ይዘው ይወጣሉ” ሲሉ የተናገሩት ዶክተር ደብረፂዮን ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ጉባኤው የደረሰበት አቋም የህወሓት ድርጅታዊ ውሳኔ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
በቅርቡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና ምክር ቤት ውህድ ፓርቲ ለመመስረት የተከተለው አካሄድ ከድርጅቱ ህገ ደንብና አሠራር የወጣ እና የሃዋሳው ጉባኤ ያስቀመጠውንአቅጣጫ የሚጥስ በመሆኑ ህወሓት በልዩነት መውጣቱን አስታውሰው ፤ የህወሓት አቋም ስለውህደቱም ሆነ ስለ ኢሕአዴግ ዕጣ ፈንታ የድርጅቱ አባላት በጉባዔያቸው ተወያይተው ካፀደቁት በኋላ መሆን እንዳለበት ሀሳብ ቢያቀርብም ተቀባይነት አልገኘም በማለት የአካሄድ ስህተት አለ ሲሉ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።
“የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና ምክር ቤት አባላት የእህት ድርጅቶች አባላት ውክልና በመያዝ የአመራር ሚናውን የሚወጣ እንጂ አንዱን አፍርሶ ሌላ ድርጅት እንዲመሰርት ስልጣንና ሓላፊነት አልተሰጠውም” በማለት የሦስቱን ድርጅቶች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ያብጠለጠሉት ዶክተር ደብረፂዮን “የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚፈጥሩት ጥምረት እንደ ኮንትራት ስምምነት የሚታይ በመሆኑ ስለ ፕሮግራሙና አካሄዱ ሳይወያዩ ውህደት መፈፀም ተገቢ አለመሆኑ የህወሓት አቋም ነው” በማለት ዳግም የድርጅታቸውን ፍላጎት አንፀባርቀዋል።
“ህወሓት ጉዳዩን ወደ አባላቱና ወደ ህዝቡ ከማውረድ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የጀመራቸውን የለውጥና የልማት ስራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አሁን ባለው ሁኔታ ውህደቱ የማይታሰብ መሆኑን ጭምር ይፋ አደርገዋል::
ጃዋር በጠራው ስብሰባ የተገኙት ቄስ ከሥራ ተባርሪያለሁ ያሉት ውሸት ነው ተባለ
በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሰንበት ተማሪዎች አስተባባሪ የሆኑት አባ ሳሙዔል ብርሃኑ፤ ጃዋር መሐመድ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ቡራኬ በመስጠታቸው ከሥራቸው መባረራቸውን መናገራቸውን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ቀሲስ አማረ አባ ሳሙዔል አልተባረሩም ሲሉ ወቀሳውን አጣጥለዋል።
አባ ሳሙዔል ስብሰባው ላይ የተገኙት በኦሮሞ ማኀበረሰብ አባላት ተጋብዘው እንደሆነ በመግለጽ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ አስኪያጅም በበኩላቸው በወቅቱ ጃዋርን በሚቃወመው ሠልፍ ላይ ታድመው ነበር ሲሉ ከሰዋል። አባ ሳሙዔል የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በትርፍ ሰዓታቸው አነስተኛ ክፍያ እየተከፈላቸው የሚያገለግሉ ካህን ናቸው እንጂ የእኛ ቋሚ ተቀጣሪ አይደሉም ሲሉ ቀሲስ አማረ በአጋጣሚው የተፈጠረውን ሁኔታም በግልፅ ያስቀምጣሉ።
እኔ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም አይደለም የወጣሁት የሚሉት አባ ሳሙዔል “ፀሎት በኦሮምኛ እንዳደርግ በማኀበረሰቡ ተጋብዤ ስብሰባውንም ተካፍያለሁ” ካሉ በኋላ ስብሰባውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ አማረ ካሳዬ መልዕክት እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ቀሲስ አማረ እንዲሁ የኦሮሞ ማኀበረሰብ ለአባ ሳሙዔል ያቀረበላቸውን ጥሪ አንደነገሯቸው አስታውሰው እንዲሄዱ እንደፈቀዱላቸው ግን የጃዋርን መገኘት ግን እንዳላነሱላቸው ይናገራሉ። የጃዋርን መገኘት ቢነግሯቸውም ኖሮ “ሃሳብ እሰጠዋለሁ እንጂ አልከለክለውም፤ መገኘት መብቱ ነው” ሲሉም ያክላሉ።
አባ ሳሙዔል በበኩላቸው የጃዋር መሐመድ አቀባበል ላይ ዋና ተዋናይ ነበርክ፤ በማለት ድርጊታቸው ሥራ አስኪያጁንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናንን ማስቆጣቱን በመግለጽ “የእኔ ልጅ፣ ላንተም ለቤተ ክርስቲያኒቷም ደህንነት ሁኔታውን እስክናጣራ ድረስ አገልግሎት ላይ እንዳትገኝ ታግደሃል” የሚል ደብዳቤ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል። እኔ የተገኘሁት ጸሎት ለማድረግ ነው ያሉት አባ ሳሙዔል ደብዳቤውን የጻፉት ቀሲስ አማረ ራሳቸው በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር ሲሉም ተደምጠዋል። ቀሲስ አማረም ሰልፉ ላይ መገኘታቸውን አረጋግጠው፤ ከሠልፉ በኋላ በርካታ ምዕመናን እየደወሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን አልሸሸጉም።
እርሳቸው እንደሚሉት ሊያነጋግሯቸው ፈልገው ወደ ግል ስልካቸው ደጋግመው የደወሉ ቢሆንም ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን በመጥቀስ ይህ የተፈፀመው ቅዳሜ በመሆኑ እሁድ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቷ ቢመጣ ሊፈጠር የሚችለውን ግርግር ለማስቀረት በሚል “የእኔ ልጅ ጃዋር ስብሰባ ላይ መገኘትህ እኔንም ኀብረተሰቡንም አሳዝኗል፤ በዚህ ምክንያት ላንተም ደህንነት ለቤተ ክርስቲያኒቷም ሲባል በነገው ዕለት እንዳትመጣ ወደፊት የሚደረገውን እንወስናለን” ብለው በስልክ መልዕክት እንደላኩ ጠቁመዋል።
ሕዝቡ በጃዋር ላይ ተቃውሞውን ያሰማው “ኦሮሞ ስለሆነ ወይንም ሙስሊም ስለሆነ ሳይሆን በድርጊቱ ነው” የሚሉት ቀሲስ አማረ እርሳቸውም ማዘናቸውን አስታውቀዋል። አባ ሳሙዔል፤ የቤተክርስቲያኒቷ ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ አማረ ‘ጃዋር ቤተ ክርስቲያን እንዲቃጠል ሲያደርግ ነበር፤ የቤተ እምነቱ ተከታዮችንም ሲያስገድላቸው ነበር’ በማለት ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ ሰዎች ጋር ነበሩ ማለታቸውን ተከትሎ ቀሲስ አማረም ይህንን ማድረጋቸውን አምነዋል። ይህንን ያደረግኩት ግን “ነገሩ በጣም ስለከነከነኝና ስላሳዘነኝ እንጂ መውጣትም አልነበረብኝም፤ መውጣትም አልፈልግም ነበር ሲሉ ያብራራሉ። ይህ የቤተ ክርስቲያናችን አቋምም ነው በማለት “ክርስቲያን በመሆን ብቻ መገደልን መገፋትን” እንደሚቃወሙ ይናገራሉ።
አባ ሳሙዔል በበኩላቸው ጃዋር በሚመራው ስብሰባ ላይ ተገኝተው የሚቀርብበትን ክስና ወቀሳ በመጠየቅ መልስ ለማግኘት መሄዳቸውን ገልፀዋል። “አባ ሳሙዔልን ያስመጣኋቸው እኔ ራሴ ነኝ፤ የተቀበልኳቸውምና አገልግል ያልኩት እኔ ራሴ ነኝ። ኦሮሞ በመሆናቸው ምንም የተፈጠረ ነገር የለም” ሲሉም አስተዳዳሪው ዕውነታውን ግልፅ አድርገዋል።
እንዲህ አይነት ስብሰባ ለእኔ አዲስ አይደለም የሚሉት አባ ሳሙዔል በበኩላቸው ከዚህ በፊትም አንዱዓለም አራጌ ወደ አሜሪካ በሄደበት ወቅት በቤተ ክርስቲያን ተጋብዞ ፀሎት ማድረጋቸውን አስታውሰው “ከጃዋር ጋርም የተለየ ነገር አላደረግንም ፤ በተመሳሳይ የሀገሪቷን ሁኔታ ተነጋግረን እኛም በአገራችን ጉዳይ ለመወያየትና ለመካፈል መብት ስላለን ገብተን ተወያይተን ወጣን” ብለዋል።
የትላንትናው ደብዳቤ እንዴት እንደተጻፈ ባላውቅም ከዚህ በፊት ግን በተመሳሳይ መድረክ ላይ ተገኝቼ ፀሎት አድርጌ አውቃለሁ የሚሉት አባ ሳሙዔል፤ ከስብሰባው በኋላ ጃዋር ‘ፀልዩልን ቤተክርስቲያንም ይሁን መስጂድ የሚጠብቁት ቄሮና ቀሬ ናቸው፤ ስለዚህ እናንተም በፀሎት ከጎናችን እንዳትለዩን’ በማለት ተነጋግረን በሰላም ተለያየን በማለትም አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል። ከስብሰባው እንደወጡ ከሥራ መታገዳቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ሲደርሳቸው ሀዘን እንደተሰማቸውም በተጨማሪነት አመላክተዋል።
“የማከብረው የምወደው ልጄ ነው፤ መልዕክቱንም ስልክለት ልጄ ብዬ ነው የላኩት። አሁንም ልጄ ነው የምለው እርሱ እንደዚህ ሆኖ በመጥፋቱ በጣም ነው ያዘንኩት”በማለትም አስተዳዳሪው በሀሰት በቀረበባቸው ውንጀላ ማዘናቸውን ይፋ አድርገዋል ።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትምህርት ሚኒስቴርና አጋሩን አስጠነቀቀ
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሃይማኖትና የፖለቲካ አጀንዳዎች ማቀንቀኛ ሊሆኑ አይገባም ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስጠነቀቀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወቅታዊው የዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋትና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፤ እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ጥልቅ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚታየው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስተጓጎል መንስዔዎችን ከመለየት፣ የቦድርዶችና የተቋማቱ አመራሮች ችግሮችን እየለዩ በወቅቱ ከመፍታትና በኹከቱ ውስጥ ተሳታፊ በነበሩ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ከመሄድ አኳያ ምን እየተሠራ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ከቋሚ ኮሚቴው ቀርበዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጠቡት ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በሀገሪቱ ውስጥ ለተዘራው የፖለቲካና የሃይማኖት መጥፎ ዜና ሰለባዎች መሆናቸውን ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት ግን ተቋማቸው ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ካሉት 45 ዪኒቨርሲቲዎች በአሁኑ ወቅት ችግሩ የተከሰተባቸው ከ25 እንደማይበልጡ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ በመደረጉ አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል ሲሉም አስታውቀዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሃይማኖትና ሌሎች የፖለቲካ አጀንዳዎች ማቀንቀኛ ቦታ መሆን እንደሌለባቸው ቢታመንም የጥፋት አጀንዳ ባላቸው ውጫዊ አካላት ሰለባ እየሆኑ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ተቋማቱ ባሉበት አካባቢ የሚገኙ በየደረጃው ያሉ አመራሮችም ጣልቃ ገብነታቸው የከፋ ከመሆኑ ባሻገር በጊዜ ሂደቱ በመጨመሩ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማከናወን ተቸግረዋል ሲሉ የችግሩ ጥልቀት የት ድረስ እንደዘለቀ አመላክተዋል ።
ተማሪዎችን ለግጭት የሚያነሳሱ አካላት ተለይተው ለፍትህ አካላት ሲተላለፉ ፣በህግ በኩል የሚወሰደው የእርምት እርምጃ በቂና አስተማሪ አለመሆኑን እንዲሁም፤ የፍትህ አካሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የጥፋት አጀንዳ ተሸክመው የገቡ ተማሪዎች እንዳሉ ተለይተው ሲቀርቡለት የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል።
አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ሚዛናዊነት ይጎድላቸዋል የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ሚዲያ ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ጠብቆ ነገሮችን ከአገርና ህዝብ ደህንነት አኳያ በመመዘን ይሠራል እንጂ፣ ችግሮች እንዲባባሱና በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል ማድረግ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ማጥፋት በመሆኑ እንደነዚህ አይነት ሚዲያዎች ከወዲሁ አካሄዳቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል ብለዋል::
ማብራሪያውን ያዳመጠው ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ተቋማቱን ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ የሃይማኖትና የፖለቲካ አጀንዳ ማራገፊያ ለማድረግ የሚሞክሩ ውጫዊና ውስጣዊ አካላትን ተከታትሎ በመለየት የማያዳግምና አስተማሪ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ሁለቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል አስጠንቅቋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን የጥበቃ ኃይል ማጠናከር ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ የገለፀውቋሚ ኮሚቴው የተቋማቱን አመራሮች ምደባን ማስተካከልና የመምህራኖችን ስነ-ምግባር መፈተሸ እንዲሁም የውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተከታትሎ መፍታት ትኩረት ሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውንም አስታውቋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ ያስገነባውን ዘመናዊ የመረጃ ቋት በይፋ አስመረቀ
የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ ያስገነባውን የመረጃ ቋት ባዛሬው ዕለት አስመርቋል። የመረጃ ቋቱ መገንባት የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን በዘመናዊ የመረጃ ማዕከል በማደራጀት ወጪዋን በራሷ ገቢ የምትሸፍን ሀገር የመፍጠር ራዕይን ለማሳካት ያለመ ነው ተብሎለታል።
በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር የአቅም ግንባታና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ምህረት ምንአስብ፤ መረጃዎችን በአንድ ቦታ (ቋት) በማሰባሰብና በተስማሚ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማደራጀት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የመረጃ አቅርቦትና የመረጃ ልውውጥ ጥራት ያለው፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ነው ሲሉ ገልጸዋል። አሠራሩ ግብር ከፋዮችን ከውጣ ውረድና እንግልት በመታደግ ግብራቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲከፍሉ ያስችላልም ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለግብር ከፋዮች ምቹ የሆነ የግብር መክፈያ ስርዓት መዘርጋት የሚጠበቅበት በመሆኑ አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች መካከል የመረጃ ቋቱ ግንባታ አንዱ ማሳያ ነው የሚሉት ዲኤታዋቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የመረጃ ቋት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ይናገራሉ። በመሆኑም የመረጃ ቋትን በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት ዓላማን በማንገብ በዘርፉ ልምድና ብቃት ያላቸው ድርጅቶችን በጨረታው በማሳተፍ የመረጃ ቋቱ መገንባቱን ጭምር አረጋግጠዋል።
የመረጃ ቋቱ የእሳት አደጋን የሚከላከል፣ በጣት አሻራ የተደገፈ፣ የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት፣ ብልሽቶችን የሚጠቁም፣ የቅዝቃዜና የሙቀት መጠን የሚለካ፣ የውሃና ፍሳሽ መቆጣጠሪያ መሳሪያ የተገጠመለት መሆኑ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ የተገለፀ ሲሆን ፤ መሥሪያ ቤቱ ግብር ከፋዮች በዘመናዊና በተቀላጠፈ መንገድ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ለማስቻል ከቴክኖሎጂ ጋር እራሱን እያዘመነ የሚሄድ ዕቅድ ነድፎ እየሠራ መሆኑም ታውቋል::