የሎስ አንጀለስ ዝግጅት ስነፅሁፍ ምሽት ተጠናቅቆ የፎቶ ማንሳት ስነስራአት ነበር፤ “ አብሮ ተነሺዎቼ” በውቄ ፈገግ በል እንጂ” እያሉ ይጎተጉቱኝ ጀመር:: እኔ ደሞ ፈገግ የማለት ተነሳሽነት ኬት ላምጣ ?
ከትኬት ሽያጭ የተሰበሰበው ገንዘብ ያዳራሹን ወጭ እንኩዋን እንደማይሸፍን እያሰብኩ አጥብቄ እየተከዝኩ ነበር፤ እንዲያውም ሆቴሌ ገብቼ ያይኔ ጭገር እስኪረግፍ ድረስ እስካለቅስ ቸኩያለሁ! በዚህ መሀል፤ አንዲት ልጅ “አንዴ ለብቻህ እፈልግሃለሁ” ብላ ነጥላ ወሰደችኝ፤ ቀይ ናት! ሙሉቀን መለሰ” ከወደዱ ላይቀር ይወዳሉ ቀይ/ እንዳላማ ሰንደቅ ከሩቅ የሚታይ” / ብሎ የዘፈነው ለእንዲህ አይነትዋ ሳይሆን አይቀርም! (አሁን ሳስበው ግን ሙሌ መሌ የዘፈነለት “አላማ ሰንደቅ ” የፖላንድ ይሆን? ) ::
እና ቀዮ ኪሴ ውስጥ የሆነ ነገር አስገባችና ጥላኝ ሄደች፤ ገልመጥ ገልመጥ አልኩና ከኪሴ የገባልኝን እስከወገቡ ብቻ መዘዝ አድርጌ ስሾፈው መቶ ዶላር ነው:: ፤ተባረኪ! አግኝተሽ አትጭ! ባታገኝም አትጭ! አቤት ደግነት! አቤት ደም ግባት! አንችን ነበር በተክሊል ማግባት! ውዴ ሆይ! እንሆ ክረምት አለፈ! ፀደይ ደረሰ! ትካዜየ ተደመሰሰ ! ፈገግታየ ተመለሰ!!
ወድያው የሆኑ ዲያስፖራዎች ከበቡኝና ስለሀገሪቱ እጣ-ፋንታ ምናምን ያወሩኝ ጀመር፤ እኔም በታላቅ ትጋት መተንተን ጀመርኩ፤ በመሃል የሆነ ሰውየ መጣ፤ ሰውየው ሃብታም ዲያስፖራ ነው፤ ስሙን አቶ ለገሰ ልበለው! የሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ የሁለት ነዳጅ ማደያ ባለቤት እንደሆነ ሰምቻለሁ፤ ለቸርች ማሰርያ ብዙ ዶላር ለግሷል! ጎፈንድሚና ጨረታ ላይ የሚቀድመው የለም! OMNንንም ሆነ “ባልደራስ”ን በገንዘብ ይደግፋል፤ “ ፖለቲከኞች ሀብታም እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤ ሌላው ቢቀር ለሀብታቸው ሲሉ አገሪቱን ይጠብቋታል ! ” ይላል አሉ፤ ሳብ አረገና በኪሴ ውስጥ የሆነ ነገር ሼጎጥ አረገልኝ፤ ልቤ በደስታ ተነካ! ሰውየው መላጣ ነው፤ ግን መላጣ ነው ብሎ ለማሰብ ራሱ ከበደኝ! ከ “ፀጉር ቀንበር ነፃ የወጣ ሰው “ነው ብየ ገለፅኩት፤
ከዚያማ ምን ይሆናል፤ በዙርያየ የከበቡኝ ዲያስፖራዎች ስለሀገራችን መጭ እጣ – ምሪንዳ ሲተነትኑ እኔ እምሰማ መስየ የለሁም፤ ቀልቤ ኪሴ ላይ ተተክሎ ቀረ ! ልጆቹ ቶሎ ለቀውኝ ኪሴ ውስጥ የሚርመሰመሰውን ፀጋ እስክቆጥር ቸኮልኩ፤ በመጨረሻ ብቻየን ቀርቼ ኪሴ ውስጥ እምገባበትን እድል አገኘሁ፤ ኮሽ !ኮሽ! ኢች ነገር ቼክ ናት እንዴ? ? ሳወጣው” በእውቄ በሙያየ የንግድ ሰው ብሆንም እያዋዙ እሚያስተምሩ የፍልስፍና ግጥሞችን እፅፋለሁ፤፤ እስቲ ይህንን አንብብና አስተያየት ለግሰኝ፤” የሚል ፅሁፍ አፈጠጠብኝ፤ ነገሩ ቼክ አለመሆኑን ሳውቅ ሼክ ማረግ ጀመርኩ! ይሄ መላጣ! ይሄ እንኩዋን ፀጉር ኮፍያ የማይረጋለት ተልባ ራስ ! ደሞኮ እኔ ልብ የለኝም! ባለ ሃያአንድ ገፅ ግጥሙን ጀመርኩለት!
“የወንድ ልጅ ኑሮ ፤ አቤት መታከቱ
በጠዋት ተነስቶ ፤ሱሪ ውስጥ መግባቱ…
እያለ ይቀጥላል…