የንግድ ሚኒስቴር የተጠና ዕርምጃ በድርጅቶች ላይ ወሰደ
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጉድለት በተገኘባቸው የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ገለፀ።ሚኒስቴሩ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባደረገው የውስጥና የውጪ የድህረ ፈቃድ የፍተሻ እና ቁጥጥር ሥራ ፣ ህግን ተከትለው በማይሠሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱን የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ቡድን አማካኝነት በ3 ሺህ 330 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማጣራት ሥራ ለመሥራት አቅዶ በ 1 ሺህ 868 የንግድ ፋይሎች ላይ የፍተሻ ሥራ መስራቱንና የዕቅዱን 56 ነጥብ 1በመቶ ማከናወኑ ነው የተነገረው። በተመሳሳይ በ480 የንግድ ድርጅቶች ላይ የውጪ ፍተሻ ሥራ ለማድረግ አቅዶ በ 421 የንግድ ድርጅቶች ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉ ታውቋል።
ክትትል ካደረገባቸው 421 ድርጅቶች ውስጥ 127ቱ በተለያየ ደረጃ የአዋጅ ጥሰት የታየባቸው፣ 67 ድርጅቶች ፈቃዳቸው የተሰረዘ፣ 28ቱ በድጋሚ በክትትሉ ወቅት ያልተገኙ እንዲሁም ቀሪዎቹ 199 በህግ አግባብ እየሠሩ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። እንዲሁም በውጪ የፍተሻ ሥራ ክትትል ከተደረገባቸው 421 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ 199ኙ በትክክለኛው የህግ አግባብ እየሠሩ ያሉ፣ 67 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ ፈቃዳቸውን የሰረዙ መሆኑም ተገልጿል።
ሌሎቹ ደግሞ የአስመጪነት ፈቃድ እያላቸው በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሠማሩ ፣ ተመሳሳይ ግብይት ሲያከናውኑ የተገኙ ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ግብይት እና ከዘርፍ ውጪ የሚነግዱ ፣ ከአድራሻ ውጪ የሚነግዱ፣ የመሸጫ ዋጋ በተገቢ ቦታ ያለጠፉ መሆናቸውን የፍተሻው ውጤት ያሳያል ነው የተባለው። ችግሮቹን ተከትሎ ወደ ትክክለኛው የንግድ መስመር ለመግባትና ለመቅረፍ በተለያየ ደረጃ የቃል እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ መሆኑን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::
በምዕራብ ኦሮሚያ ሁለት ባለሥልጣናት በታጣቂዎች ተገደሉ
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የጀልዱ ወረዳ አመራር የሆኑ ሁለት የአካባቢው ባለስልጣናት ከትናንት በስቲያ ማንነታቸው አልታወቀም በተባላቸው ታጣቂዎች መገደላቸው ተሰማ።
የጀልዱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ረጋኔ ከበበ እና የጎጆ ከተማ የፖለቲካ ዘረፍ ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ገረመው በጎጆ ከተማ ማክሰኞ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ በጥይት ተመትተው መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በክልሉ ይህን መሰል በመንግሥት ሓላፊዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፈው ሳምንት እንኳ አንድ የምዕራብ ሸዋ ዞን ባለስልጣን በተመሳሳይ በጥይት ተመትተው መገደላቸው ይታወቃል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያም ማንነታቸው በውል ያልተገለጹ ታጣቂዎች የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሓላፊ የነበሩትን ኮማንደር ጫላ ደጋጋን መግደላቸውምተነግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመንግሥት ሓላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ኢትዮጵያ ነገ ለበርካታ ጊዜያት መዘገቡ አይዘነጋም።
ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ቡድን በሚንቀሳቀስበት በምዕራብ ወለጋ ከመንግሥት ባለስልጣናቱ ባሻገር ሰላማዊ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና የውጪ ዜጎችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ማንነታቸው በውል ባልተገለጹ ታጣቂዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በክልሉ በሚገኙ ባለስልጣናት ላይ ኢላማ እያደረገ የመጣውን ይህን ግድያ ለማስቆም በቅርቡ የተቋቋመው እና ‘ጋዲሳ ሆገንሰ ኦሮሞ’ የሚሰኘው አካል ከመንግሥት ጋር በመሆን መፍትሄ እያፈላለገ እንደሆነ ተናግረዋል። በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ፓርቲዎች ስብስብ መድረክ የሆነው ‘ጋዲሳ ሆግንሰ ኦሮሞ’ የኦሮሞ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ፓርቲዎች አብረው ለመስረት ከስምምነት ደርሰው ከሁለት ወራት በፊት ያቋቋሙት አካል ነው። በ’ጋዲስ ሆግንሰ ኦሮሞ’ ምስረታ ላይ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዳውድ ኢብሳ፣ መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ እና በቀለ ገርባ ፓርቲዎቻቸውን ወክለው ፊርማቸውን ካኖሩ አመራሮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ::
“ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ አካላት ትግላቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን ነው የመንግሥት ፍላጎት :: አለመረዳዳት ነው እንጂ ኦሮሞ ኦሮሞን ገድሎ የሚገኝ ጥቅም የለም፤ ኪሳራ ነው ማለት ነው” ያሉት አቶ ዴሬሳበተለይ በምዕራባዊ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ላጋጠመው ባለስልጣናትን ኢላማ ላደረገው ግድያ ተጠያቂውን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዴሬሳ፤ “ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ባለበት ሁኔታ እከሌ ነው ማለት አይቻልም፤ እርስ በእርስ መጠቋቆም ነው የሚሆነው፤ ይህንን ጥቃት ለማስቆም በአጠቃላይ እንደ መንግሥት ያለን አቋም የጦር መሳሪያ አያስፈልግም የሚል ነው” በማለት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ወደ ሰላማዊው መድረክ እንዲመጡ እንደሚፈለግ አስታውቀዋል።
“ሰላም በሌለበት እና ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አካል ባለበት ሁኔታ ለወንጀሉ ተጠያቂው እገሌ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው” ያሉ ሲሆን፤ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመቆጣጠር እና የህግ የበላይነትን ማስከበር መሰል ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በምዕራቡ የአገሪቱ አካባቢ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ሓላፊነቱን የወሰደ ቡድን ባይኖርም ድርጊቱ በተለይ ኢላማ ከሚያደርጋቸው የመንግሥት ባለስልጣናት አንጻር ምናልባት ፖለቲካዊ ዓላማ ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ኤርትራ ኳታር ባለሥልጣናቷን ለመግደል ማቀዷን ደርሼበታለሁ አለች
ኳታር የተለያዩ ኃይሎችን በመጠቀም የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመግደል ዕቅድ እንዳላት እንደደረሰበት የኤርትራ መንግሥት ገለፀ። ጉዳዮን አስመልክቶ የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ኳታር የተለያዩ የሽብርና የተቃውሞ ተግባራት በኤርትራ ውስጥ እንዲፈጸሙ የማስተባበር ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ደርሼበታለሁ ብሏል።
ይህንን እኩይ ተግባር ሱዳንን እንደ ድልድይ በመጠቀም የኤርትራን ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ ተግባራት በኳታር ደጋፊነት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል አጋልጧል።
ኳታርና ተላላኪዎቿ እብደታቸው እያደገ ነው በማለት የሚጀምረው መግለጫ “ኳታርና ሸሪኮቿ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ወጣቶችን በመቀስቀስ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና ተቃውሞ እንዲያስነሱ ተዘጋጅታለች” ሲል ይወነጅላል።”ሙስሊም የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶችን በመስበክ በኤርትራ ሕዝብ መካከል የብሔር ጥላቻ በመዝራት፣ ሙስሊሞች በሌላው ሕዝብ ላይ እንዲነሱ የሐሰት ወሬ እያሰራጨች ነው” በማለትም ኳትርን በገሀድ አብጠልጥሏል።
በኤርትራ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ቪድዮዎችን በማዘጋጀት ተቃውሞና አድማዎች እንዲካሄዱ በማበረታታትና የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ኳታር ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው የሚለው የኤርትራ መንግሥትበዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ላይ ጥቃት እንዲፈጸምና ውድመት እንዲደርስ እንዲሁም አስፈላጊ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የመንግሥት ባለስልጣናትን ለመግደል ስልጠና እየሰጠች ነው ሲል የተጋረጠበትን ስጋት አመላክቷል::
በምሥራቃዊ ሱዳን በብሔሮች መካከል ግጭት መፍጠርን በሚመለከትም ‘አጃኢብ የሚያሰኝ ዕቅድ’ ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል:: ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የኤርትራ መንግሥት ቱርክ እና ኳታር በኤርትራ ላይ አውዳሚ ተግባራት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።
ቱርክ በዚህ ዓመት ‘የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት’ በሚል የሚታወቀው ቡድን ጽህፈት ቤቱን እንዲከፍት መፍቀድዋን ጠቅሶ ይህም መግለጫው ‘አውዳሚ’ ላለው አላማ እንደሚውል ያስረዳል:: የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት (መጅልስ ሹራ ራቢጣ ዑላማእ ኤሪትሪያ) በሱዳን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለው የቡድኑ አባል የሆኑት መሓመድ ጁማ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የኤርትራ መንግሥት “ይህንን ከንቱ ተግባር በተለያየ መንገድ በመደገፍ በኩል ኳታርና ለእንደዚህ እኩይ አላማ ግዛቱን አሳልፎ በሰጠው የሱዳን ሥርዓት አማካይነት የሚፈጸሙ ናቸው” በማለት መክሰሱም አይዘነጋም። ኤርትራ ከኳታር ጋር የነበራት ጠንካራ ዝምድና በመሻከሩ በሳዑዲ አረቢያ ወደ ሚመራውን የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጥምረት ፊቷን አዙራለች። ከአራት ዓመታት በፊት በየመን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለፈጸመው በሳዑዲ የሚመራውን ኅብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ኤርታራ ማስታወቋ የበለጠ ክፍተቱን አስፍቶታል።
የኢጋድ ሃገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው
በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያ በመግባት ላይ ናቸው።
እስካሁን ምሽቱ 12 ድረስ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።
የሃገራቱ መሪዎች አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢጋድ አባል ሃገራት መሪዎች አዲስ አበባ የገቡት ነገ የሚካሄደውን 13ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የመሪዎች ስብሰባን ለመካፈል መሆኑ ታውቋል።
ኢትዮጵያ 21ኛዋ የዮኔስኮ ኮሚቴ አባል ሆና ተመረጠች
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) የዓለምአቀፍ የቅርስ ኮሚቴ አባል ሆና ተመረጠች። በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደገለፀው ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት የዓለም አቀፍ የቅርስ ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧ ታውቋል።
ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ወቅት የዩኔስኮ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድና የዓለም አቀፍ ቅርስ ኮሚቴ አባል ሆና እንደምታገለግልም ነው ኤምባሲው ገልፆ ፤ ኢትዮጵያ የዩኔስኮ የዓለም አቀፍ የቅርስ ኮሚቴ አባል እንድትሆን ለመረጡ ሀገራትም ምስጋናውን አድርሷል።
የዩኔስኮ የዓለምአቀፍ የቅርስ ኮሚቴ የ21 ሀገራት ተወካዮችን በውስጡ የያዘ ሲሆን ፤ የኮሚቴው አባል ሀገራትም በዩኔስኮ ጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጡ ናቸው።
ኮሚቴው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ስምምነቶች በሥራ ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሓላፊነት አለው :: ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የቅርስ ፈንድ አስፈላጊነትን የሚያብራራ እና በሀገራት ጥያቄ ላይ ተመስርቶ የገንዘብ ድጋፍ የሚያመቻች መሆኑም ታውቋል። ኮሚቴው ቅርሶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) መዝገብ ላይ እንዲሰፍሩ እና ቅርሶቹ አደጋ ላይ ሲወድቁም እንዲሰረዙ የማድረግ ሙሉ ስልዕጣን አለው ።
የንግድ ሚኒስቴር የተጠና ዕርምጃ በድርጅቶች ላይ ወሰደ
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጉድለት በተገኘባቸው የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ገለፀ።ሚኒስቴሩ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባደረገው የውስጥና የውጪ የድህረ ፈቃድ የፍተሻ እና ቁጥጥር ሥራ ፣ ህግን ተከትለው በማይሠሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱን የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ቡድን አማካኝነት በ3 ሺህ 330 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማጣራት ሥራ ለመሥራት አቅዶ በ 1 ሺህ 868 የንግድ ፋይሎች ላይ የፍተሻ ሥራ መስራቱንና የዕቅዱን 56 ነጥብ 1በመቶ ማከናወኑ ነው የተነገረው። በተመሳሳይ በ480 የንግድ ድርጅቶች ላይ የውጪ ፍተሻ ሥራ ለማድረግ አቅዶ በ 421 የንግድ ድርጅቶች ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉ ታውቋል።
ክትትል ካደረገባቸው 421 ድርጅቶች ውስጥ 127ቱ በተለያየ ደረጃ የአዋጅ ጥሰት የታየባቸው፣ 67 ድርጅቶች ፈቃዳቸው የተሰረዘ፣ 28ቱ በድጋሚ በክትትሉ ወቅት ያልተገኙ እንዲሁም ቀሪዎቹ 199 በህግ አግባብ እየሠሩ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። እንዲሁም በውጪ የፍተሻ ሥራ ክትትል ከተደረገባቸው 421 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ 199ኙ በትክክለኛው የህግ አግባብ እየሠሩ ያሉ፣ 67 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ ፈቃዳቸውን የሰረዙ መሆኑም ተገልጿል።
ሌሎቹ ደግሞ የአስመጪነት ፈቃድ እያላቸው በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሠማሩ ፣ ተመሳሳይ ግብይት ሲያከናውኑ የተገኙ ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ግብይት እና ከዘርፍ ውጪ የሚነግዱ ፣ ከአድራሻ ውጪ የሚነግዱ፣ የመሸጫ ዋጋ በተገቢ ቦታ ያለጠፉ መሆናቸውን የፍተሻው ውጤት ያሳያል ነው የተባለው። ችግሮቹን ተከትሎ ወደ ትክክለኛው የንግድ መስመር ለመግባትና ለመቅረፍ በተለያየ ደረጃ የቃል እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ መሆኑን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::