እ.አ.አ. በ 1995 አዲስ አበባ እያለሁ፣ ከ12 የምዕራብ አውሮፓ አምባሳደሮች ጋር ወደ ዝዋይ ሀይቅ ተጓዝን። በዝዋይ ሀይቅ ላይ አምስት ደሴቶች አሉ። ወደ ውስጥ ራቅ ብላ አርሲ ድንበር አጠገብ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የተሸፈነችው ደሴት ላይ የፅዮን ማርያም ገዳም ትገኛለች።
ነዎሪዎቹ ትግርኛ -መሰል ቋንቋ ይናገራሉ። “መሰል” ያልኩት ከትግርኛው ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ጉራጊኛም በዛይ ቋንቋ ውስጥ ስለተዋሃዱ ነው።
ሰዎቹ ከአንድ ሺ አመት በፊት (ከ990 እስክ 1030 አ.ም.) የዮዲት ጉዲት ጦር ፅዮን ማርያም አክሱምን ለማውደም ሲዘምት፣ ጥቂት ሰዎች የፅዮን ማርያም ታቦትን ተሸክመው ወደ ጣና ሀይቅ ደሴት ሸሹ። የአከባቢው ህዝብም ታቦቱን ይዘው የመጡትን እንግዶች በአንዱ ደሴት ባለው የኡራ ኪዳናምህረት ገዳም (ጎብኝቼዋለሁ) ደብቀው አኖርዋቸው።
አሁንም ዮዲት ወሬው ደርሷት ጦርዋን ወደ ጣና ሀይቅ ሲታዘምት፣ እነዛ ከትግራይ የመጡ ሰዎች አብረው ከአማራው ህዝብ ጋር በመሆን ታቦቱን ይዘው ወደ መንዝ (ሸዋ) ሸሹ።
ትንሽ እንደቆዩም፣ የዮዲት ጦር ሚስጥሩን ሰምቶ ኑሮ ወደ ሰሜን ሸዋ አመራ። ታቦት ጠባቂዎቹም ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ አሁን ደግሞ ከሸዋ የተወጣጡ ምእመናን አንድ ላይ ሁነው ታቦቱን ተሸክመው ፍጹም ራቅ ወዳለ ቦታ ብለው ወደ ዝዋይ አመሩ።
ታቦቱም በቀላሉ ሊደረስበት ወደ ማይቻል፣ ቱሉ ጉዶ ደሴት ወስደው ጽዮን ማርያም ገዳምን ሰይመው ታቦቱን ደበቁት።
በግምት ከ70 አመት በኋላ ታቦቱ ወደ መጣበት አክሱም ሲመለስ፣ እዛው ተዋልደው የኖሩት ሰዎች ግን ከትግራይ ይዘውት የመጡትን ትግርኛ ከአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ጉራግኛ ጋር አዋህደው ከጊዜ ብዛት “ዛይ” የሚባል ቋንቋ ተናጋሪ ሆኑ። እነሱም ዛሬ የዛይ ብሄረሰብ ተብለው ይታወቃሉ። ሀይማኖታቸውም ጥንታዊው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነው።
የዛይ ብሄረሰብ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ተዋህዶና ተዛምዶ የኖረ ለመሆኑ አንዱ ቋሚ ማስረጃ ነው።
ይህን ሀቅ የሚቀበል ትውልድ፣ ላለፉት 28 አመታት ትውልድን ሲበክል የኖረውን፣ አገር አፍራሹን የዘር ፖለቲካ እንደ በሽታ ተከላክሎ ማጥፋት አለበት።
በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሰርቶ የሚኖረውን ዜጋ “መጤ” እያሉ፣ ወይም የተለያዩ ስሞችን እየለጠፉ ከኖረበት ቀዬ ሸሽቶ እንዲጠፋ ማድረግ ሀገራችንን ለእርስ በርስ እልቂት የሚዳርግ መሆኑ ልዩ እውቀትን አይሻም።
የአብይ ይሁን ማንኛውም መጪ መንግስት ዘር ወይም ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች የሚያካሂዱ ኃይሎችን በከፍተኛ ወንጀል (treason) እየከሰሰ ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል። ይህን የማያደርግ መንግስት፣ የወንጀሉ ተባባሪ (accomplice) ስለሆነ፣ ህዝብ ድጋፍ ሊነሳው ይገባል።