በቅርብ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ተሰጥጦት በብሔራዊ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ህጋዊ ይሁንታ ያገኘው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ባለልጣናት እራሱን ከሶማሊያ ከገነጠለው የጁባላንድ ባለስልጣናት ጋር ኬንያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ለስብሰባ መቀመጣቸው ተሰማ።
በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው አዲስ ስታንዳርድ የኤሎትሮኒክ መጽሔትን ዋቢ ያደረጉ የሶማሊያ ድህረገጾች እንዳስነበቡት ከሆነ በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ የግንባሩ መሪነቱን ያገኙት አብዱራህማን መሀዲ የተመራው የኦብነግ ልኡካን ቡድን ባለፈው እሁድ ኬንያ ሲገባ የናይሮቢ መንግስት ባለስልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውለታል።
እኤአ በ2001 በተቋቋመው እና በሰባት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዙሪያ በሚሰራው መንግስታዊ ያልሆነው የስምጥ ሸለቆ የጥናት ማእከል በተባለው ተቋም መንገድ ጠራጊነት ናይሮቢ ላይ ከሚዲያዎች እይታ ውጪ ለምክር የተቀመጡት የኦብነግ እና የጁባላንድ ባለስልጣናት በምን ጉዳይ እንደሚመክሩ እና ምን አይነት ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ለጊዜው አልታወቀም። አንዳንድ ገለልተኛ ያልሆኑ ነገር ግን ለጉዳዩ ቅርበትነት ያላቸው ምንጮች በበኩላቸው የናይሮቢው ስብሰባ በቀጠናው ሊደረግ ስለሚገባ ሰላም እና ትብብር ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ባለፈው ነሐሴ ወር ውስጥ አወዛጋቢ የሆነ የፕሬዛዳንታዊ ምርጫ ያካሄደችው እና በኦጋዴን ተወልደው አሁን ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት መሀመድ አህመድ እስላም (አህመድ ማዴቤን) የሚመሯት ጁባ ላንድ በወቅቱ የኢትዮጵያ አውሮፕላን ወደ ኪስማዩ አውሮፕላን ጣቢያ ከማረፍ ማገዷ፣ ምርጫውን በምትቃወመው ሶማሊያ (መቋደሾ) እና ኢትዮጵያ በአንድ በኩል መቆም፣ ምርጫውን በምትደግፈው ኬንያ በተቃራኒ ጎራ መሰለፍ የፕዲፕሎማቲክ ክፍተት ፈጥሮ እንደነበር ዜና ዘገባዎቹ አውስተዋል።
የጁባላንድ ፕ/ቱ ማዲቤ በቅርብ ይፋ እንዳደረጉት ኢትዮጵያ ባለፈው ነሐሴ ወር ወደ ኪስማዪ በአውሮፕላን ልካው የነበረው ኮማንዶ ሰራዊት “በእኔ እና በአስተዳደሬ ላይ ግልበጣ ለማድረግ የተወጠነ ነበር” ብለዋል። ከዚህ አኳያ ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ሰራዊታቸውን ከጁባ ላንድ እንዲያስወጡ ብርቱ የሆነ ግፊት ቢኖርም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቁርጥ ካለ ውሳኔ ላይ አለተደረሰም።
ኢሕአዲግን እና ሻቢያን ከደርግ ጋር ለማደራደር ሞክረው በመጨረሻው ሰአት ላይ ሁለቱ አማጺያኖች አ/አ እና አስመራ ላይ መንግስት እንዲመሰረቱ ይሁንታ የሰጡት የቀድሞው በአፍሪካ የአሜሪካ ጉዳዮች ም/ሀላፊ የነበሩት ሀርማን ኮኸን በቅርቡ በትዊተር መልክታቸው ላይ “ኢትዮጵያ ሰራዊቷን ከሶማሊያ ካወጣች አልሽባብን ግባልን ብሎ የመፍቀድ ያህል ስለሚሆን ጥንቃቄ ያሻዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እንደ ሶማሊያ መገናኛ ብዙሃናት እምነት የጁባላንድን ምርጫ እና የማዲቤን መመረጥን ቀደም ሲል የደገፈው ኦብነግ ናይሮቢ ላይ ከጁባ ላንድ ተወካዬች ጋር የሚያደርገው ውይይት በኬኒያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ውጥረቶችን እንዳያባብስ ተሰግቷል።
የጁባላንድ ባለስልጣናት ” የአፍሪካ ህብረት እውቅና ያልሰጠው”፣ በጌዶ የሚገኘው እና በቅርቡ የጁባላንድ ም/ል/ፕ/ት የሆኑት መሐመድ ሳይድ አዳን የቁም እስረኛ አድርጓቸዋል የተባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ለተመድ እና ለአፍሪካ ህብረት ደብዳቤ ጽፈዋል ሲሉ አስነብበዋል።