ቤት ዘግተው ተነጋግረው መጨረስ የሚገባቸውን ለአደባባይ ማብቃታቸውን በቅንነት መውሰዱን መርጬአለሁ። የህወሀትን አከርካሪ ሰብረው፡ እነስብሃት ነጋን በአዳራሽ ውስጥ በድንጋጤ አስጩኸው ወደ መቀሌ ከሸኙት የለውጥ አመራሮች በፊት መሪነት የሚጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳ በዛሬው ዕለት ቅንድብን ከፍ የሚያደርግ፡ ስሜትን የሳይቤሪያ በረዶ ውስጥ አስገብቶ የሚያኮማትር አቋም ማንጸባረቃቸው የብዙዎችን ቀልብ መግፈፉን እያየሁ ነው። የእኔንም ጨምር። ሆኖም ዓለም የተደፋችብን፡ ሁሉ ነገር ያበቃና ያለቀለት አድርገን እንድንወስድ በአክራሪ ብሄርተኞች እየተደለቀ ያለውን ከበሮ የምሰማበት ጆሮ የለኝም። ገና ነው። የፖለቲካው ጡዘት አንድ ከፍታ መጨመሩን እንጂ ሰማይ ምድሩ በድቅድቅድ ጨለማ የተዋጠብን አድርጌ ለመደምደም ጊዜው በጣም ገና ነው።
በለውጥ ዘመን ከዚህም የከፋ መጠላለፍ ይከሰታል። በእኛ የእድሜ ዘመን ባይገጥመንም በአብዮቱ ፍንዳታና በ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ጊዜ የነበሩት የፖለቲካ ግብግቦች አሁን ከተከሰተው አንጻር ከወሰድን ኢምንት ሆኖ ሊታየን ይችላል። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም አብዮታቸውን ለማጽናት ሰውነታቸው በጥይት እስኪበጣጠስ የደረሱ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል። ቤተምንግስታቸው የጦርነት አውድማ እስኪመስል ከቀልባሾች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው፡ በታንክ ስር መሽገው ነው በመጨረሻም መንግስታቸውን አረጋግተው፡ መለዮአቸውን አውልቀው በኢጣሊያን ሱፎች ብቅ ማለት የጀመሩት። ህወሀትም የአራት ኪሎ አጀማመሯ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ከሁስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ አንስቶ አያሌ ትርምሶችና፡ ግብግቦችን ተሻግራ ነው ወንበሯን ያጸናችው። የ1993ቱ የህወሀት ህንፍሽፍሽን አቶ መለስ ዜናዊ የተሻገሩት ከደብረዘይት አየር ሃይል መሽገው እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። የትኛውም የለውጥ ጉዙ ባሩድ ሳይሸት፡ መጠላለፍ ሳይከሰት፡ በጓዶች መሃል ሽጉጥ መማዘዝ ሳይኖር ጸንቶ አልቀጠለም። ካለፈው ታሪካችን የሚለየው አሁን የዘር ፍጥጫና ጥቃት መኖሩ እንጂ ከለውጥ ጊዜ ግርግር አንጻር ብዙም ችግር አለ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።
አቶ ለማ መገርሳ ለምን በዚህን ጊዜ መደመርን ተጠየፉ? የውህድ ፓርቲው በዝግ ስብሰባዎች ሲደረጉ አቶ ለማ በግልጽና በአደባባይ ልዩነታቸውን አስቀምጠው ከሂደቱ ለምን አልወጡም ነበር? የብልጽግና ፓርቲ የምስረታ ጉዞ ዛሬ ድንገት ዱብ ያለ አይደለም። በኢህአዴግና በኦዲፒ ደረጃ በተደረጉ የአዲሱ ውህድ ፓርቲ የምስረታ ስብሰባዎችና ምክክሮች ወቅት አቶ ለማ መገርሳ ተቃውሞ እንደነበራቸው በጭምጭምታ የሚሰማ ቢሆንም የሀሳብ ልዩነታቸውን አስጠብቀው በመጨረሻም ለብዙሃን ውሳኔ ተገዢ ሆነው በሂደቱ መቀጠል አልያም ልዩነታቸውን ይዘው ከሂደቱ መሰናበት ሲገባቸው እጃቸውን በማውጣት አጽድቀው የተስማሙበትን ውሳኔ ዛሬ በሬዲዮ ቃለመጠይቅ እኔ የለሁበትም ማለታቸው ምን ይፈይድላቸዋል?
ውህድ ፓርቲው ጉዞውን ቀጥሏል። ዶ/ር አብይ የሚያስፈልጋቸውን ድምጽ አግኝተው አዲሱን ፓርቲ ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ አሸጋግረውታል። የአቶ ለማ ባለቀ ሰዓት፡ የተበላበት ሰሀን ከተሰበሰብ በኋላ ምግቡ አልጣፈጠኝም የሚል አስተያየት መስጠትና አቋም መያዝ ምን ትርጉም አለው? የለውጡ የጀርባ አጥንት አቶ ለማ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ከየአቅጣጫው ጦር ሲሰበቅበት በጽናት መክተው ከገደል አፋፍ የተጠጋውን የኢትዮጵያን ህልውና የታደጉት አቶ ለማና ጓዶቻቸው ናቸው። ቲም ለማ በሚል የተጠራውን የለውጥ አመራር ለድል አብቅተው የ27 ዓመቱን የህወሀት አስከፊ ምዕራፍ የዘጉት እሳቸውና ጥቂት ገለሰቦች ናቸው። ዛሬ አብረዋቸው ለውጡን ከዳር ያደረሱትና ህወሀትን ከመቀሌ የሸኙት አመራሮች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚሰራ አዲስ መስመር ሲዘረጉ አቶ ለማን ምን ነጠላቸው?
በእርግጥ በአቶ ለማ ተስፋ ለመቁረጥ የሚያስችል ወኔ የለኝም። ለአክራሪዎች ትርክትና ለህወሀት ዲስኩር የሚመች አቋም ቢያንጸባርቁም ሰርፕራይዝ የሚያደርግ የማንጠብቀው፡ የማንገምተው የተሻለ ነገር ለማድረግ አስበው ነው በሚል ውሳኔአቸውን በበጎነቱ ለመቀበል ውስኜለሁ። ማን ያውቃል? ጽንፈኝነት ከበረከተበት፡ የጎረምሳ ጩኸት በደመቀበት፡ መንጋውን በአንድ ፊሽካ መንዳት የለመደ ወፍ ዘራሽ አክቲቪስትና ፖለቲከኛ እንደእንጉዳይ በፈላበት የፖለቲካው አውድ በሌላ አቅጣጫ መጥተው፡ ልቡ የሸፈተውን ለጽንፈኞች ጆሮውን የሰጠውን አብዛኛውን የወጣቱን የህበረተሰብ ክፍል ወደ ለውጡ መስመር ለመጎተት የዘየዱት ብልሃት ይሆናል የሚል ቅንጣቢ ተስፋ በውስጤ ማሳደሩን መርጬአለሁ።
በተረፈ የእሳቸውን ውሳኔ ለጽንፈኛ ትርክታቸው ፍግ አድርገው ለመጠቀም ያሰፈሰፉ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች ዛሬ ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። አጋጣሚው ለህወሀትም ያልታሰበ አዱኛ ከእጁ እንዲገባ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። አሁን ካለው ውጥረት የበለጠ በቀጣዮቹ ቀናት ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። ዶ/ር አብይን ከኦሮሞ ክበብ ለማምውጣት ቀን ከሌሊት የሚታትሩት እነዚህ ጽልመተኞች ከወዲሁ ጡንቻቸውን እያፍታቱ፡ ለሌላ ዙር ቀውስ ደጋፊዎቻቸውን ሊማግዱ መጠራራት ጀምረዋል። አቶ ለማን የኦሮሞ ብሄራዊ ጀግና፡ ዶ/ር አብይን በተቃራኒው የኦሮሞ ህዝብ ጠላት አድርጎ ለማሳየት ቀደም ብለው የጀመሩትን ዘመቻ በብዙ እጥፍ ጨምረው ከሰሞኑ እንደሱቅ በደረቴ በተከፈቱ ግልገል ሚዲያዎች ሳይቀር በብዛት እንደሚመጡ ይጠበቃል። ውህድ ፓርቲውን ከጉዞው ለማደናቀፍ ያስችለናል ያሉትን እያንዳንዷን እድል ለመጠቀም የተዘጋጁት ህወሀቶችና ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች የአቶ ለማን የዛሬ አቋም ከሰማይ ትልቅ ሲሳይ እንደወረደላቸው አድርገው የሚቁጥሩት በመሆኑ ለኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ምጥ የሚበረታበት መሆኑ የማይቀር ነው።
በህጋዊ አሰራርና፡ በስርዓትና ደንብ ከሆነ የአቶ ለማ የዛሬው እጥፋት ብዙም የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። አዲሱ ውህድ ፓርቲ በእሳቸውም እጅ ማውጣት ጭምር በአብላጫ ድምጽ እውን የሆነ የማይቀለበስ እርምጃ ነው። የአቶ ለማ በለውጡ ከነበራቸው ግዙፍ ሚና አንጻር የዛሬው ውሳኔአቸው አስደንጋጭ ቢሆንም የብልጽግና ፓርቲን ህጋዊ ሰውነት የሚነካው ፈጽሞ አይሆንም። ጉዞው ይቀጥላል። ሂደቱ አይቋረጥም። አብረው እንደጀመሩት አብረው ቢጨርሱት የተሻለ ይሆን ነበር። ህወሀትን ወደመቃብሩ ሲሸኙት በጋራ መስዋዕትነት የከፈሉት አቶ ለማ የህወሀትን ግብዓተ መሬትም አብረው መፈጸም ቢችሉ ታሪካዊ ይሆን ነበር። ብልጽግና ፓርቲ ወደኋላ የማይመለስ ጉዞ ላይ ነው። ከፊት የኢትዮጵያ ብልጽግና ይጠብቀዋል። ከጨለማው ማዶ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ትታየዋለችና ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ዓይነት ምድራዊ ምክንያት አይኖረውም። ከኋላ ያለው የኢትዮጵያ ምፅዓት ነው። ከኋላ ያለው በህወህት የተቆፈረው ጥልቅ የመቃብር ጉድጓድ ነው። ውህዱ ፓርቲ እንደቡግንጅ እዚህና እዚያ እየፈነዱ ያስቸገሩትን በጥበብና በብልሃት ተሻግሮ ኢትዮጵያን ከማማ ላይ ያስቀምጣታል የሚለው ተስፋዬ አሁንም የጸና ነው።
አቶ ለማ ውሳኔአቸው አሁን ባለው አስፈሪ ድባብ ላይ ተጨማሪ ቀውስ እንዳይፈጥር ከማንም በላይ ሃላፊነት አለባቸው። በእሳቸው ላይ ተንጠልጥለው የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት ላሰፈሰፉ ሃይሎች መሳሪያ እንዳይሆኑ ትልቅ አደራ ተጥሎባቸዋል። አሁንም በእሳቸው ተስፋ አልቆርጥም። የዛሬውን አቋማቸው በውህድ ፓርቲው ሂደት ላይ ለውጥ የማያመጣ መሆኑን እያወቁ ውጥረቱን የሚያባባስ መግለጫ ለአደባባይ በማብቃታቸው ባዝንባቸውም በሚቀጥሉት ቀናት በእሳቸው መነሻነት የሞት ድግስ ለሚያሰናዱ ሃይሎች ግልጽ መልዕክት በማስተላለፍ ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ስል እማጸናቸዋለሁ። ልዩነትዎን አከብራለሁ። መብትዎ መሆኑን እቀበላለሁ። ስለኢትዮጵያ ክፉ ያስባሉ ብዬ ለሰከንዶችም የምጠራጠርዎት አይደሉም። በሱስዎ ውስጥ አሁንም ትልቋ ኢትዮጵያ ትታየኛለች። እንዳስጀመሩን ያስጨርሱናል የሚል እምነት አሁንም እንደብረት ጠንክሮ በውስጤ ተቀምጧል። የለፉበትን፡ መስዋዕት የከፈሉበትን ለውጥ መንገድ ላይ አዝረክርከው ይተውታል ብዬ ለማመን ፈጽሞ አልችልም። በታሪክ መዝግብ ላይ በወርቃማ ብዕር የሚጻፍልዎትን መልካም ስም ጠብቀው መጪው ትውልድ የሚኮራበትን ሀገር ለማስረከብ መንገዱን ጀምረዋልና በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይመስለኝም። እንደበፊቱ አሁንም አምንብዎታለሁ።
ኢትዮጵያን ፈጣሪ እግዚያብሄር ይጠብቃት!!!!