ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውይይት ባለመግባባት ተቋረጠ
በነፃነት ተምሳሌቷ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር በምርጫ ማስፈጸሚያ ሕጉ ዙሪያ ዛሬ ማካሄድ ጀምሮት የነበረው ውይይት ባለመግባባት ተበትኗል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው ውይይት ሊቋረጥ የቻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ ላይ የሰጡት አስተያየት ግብዓት ሆኖ አላገለገለም የሚል ሃሳብና አቋም በመያዛቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች የሆኑ የፓርቲ አመራሮች አመላክተዋል።
” የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ለማስፈጸም በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ከመወያየታችን በፊት በአዋጁ ላይ ያነሳነው ጥያቄ ሊመለስልን ይገባል” የሚል ሃሳብ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ቦርዱን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም የሚል ምላሽ ቢሰጡም ልዮነቱ ከመጥበብ ይልቅ ወደ አለመግባባት ማደጉን ለማወቅ ተችሏል።
ሰብሳቢዋ በዚህ መሠረት እንደ ተቋም የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣትና መተግበር ስለሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ባለድርሻ አካላት በረቂቁ ላይ ሃሳብ እንዲሰጡ ቢጠይቁም ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላት ግን ”ከዚህ በፊት በአዋጁ ረቂቅ ላይ የሰጠነው ሃሳብ ግብዓት ሆኖ ባለማገልገሉ ፣ አሁን በዚህ ደንብ ላይ የምንሰጠው አስተያየት ግብዓት ይሆናል የሚል እምነት የለንም” ሲሉ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋን ሃሳብ አጣጥለዋል።
እንዲህ ባለ የሃሳብ ልዮነት ነገሮች በመክረራቸውና በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን ባለመኖሩ ዛሬ ለግማሽ ቀን ተጠርቶ የነበረው መድረክ ካለስምምነት እንደተበተነ ተሳታፊዎቹ ለኢትዮጵያ ነገ አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቺ በያዙት አቋም ውይይቱን ለማካሄድ አመቺ መሆኑን የተረዱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳና የቦርዱ አባላት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሌላ ጊዜ ለውይይት ተዘጋጅተው እንዲመጡ አሳስበው፤ ያላቸውን ጥያቄ በጽሑፍ ለቦርዱ እንዲያቀርቡም ምክር ለግሰዋል።
በተጨማሪም ረቂቅ ደንቡ ፓርቲዎቹ ተወያዩበትም አልተወያዩበትም መጽደቁ ስለማይቀር ለፖለቲካ ሂደቱ ስኬት ሲባል ቢወያዩበት ይመረጣል ማለታቸውንና ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ማስተላለፋቸውንም የተበተነው ጉባዔ ተሳታፊዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሦስት የመንግሥት ሓላፊነቶች አዲስ ሹመት ሰጡ
የኢፌዲሪጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሦስት የመንግሥት የሥራ ሓላፊነት ቦታዎች ሹመት ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም ከትናንት ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር ላይ ለሦስት የመንግሥት የሥራ ሓላፊነት ቦታዎች ሹመት መሰጠቱን ይፋ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አዲስ ሹመት መሠረት:-
አቶ አህመድ ቱሣ ፤ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣
ዶክተር አለሙ ስሜ ፤ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ
አቶ አወሉ አብዲ ፤ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሓላፊ ሆነው መሾማቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቲም ለማ የለውጥ ቡድን እገዛ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ወሳኝ መንግሥታዊ ሓላፊነቶች ለአንድ ብሔር ባደላ መልኩ ለኦዴፓ ሰዎች አከፋፍለዋል በሚል የሰላ ትችት ሲቀርብባቸው መሰንበቱ አይዘነጋም::
“ቄሮ አምላኪ” ናቸው የሚባሉት አዲሱ አረጋ የኦሮሚያ ም /ርዕሰ መስተዳድር ሆኑ
ነፍጠኛን ሰብረን ጥለነዋል በማለት በተሳሳተና ከእውነታ ባፈነገጠ ትርክት ብዙኃኑን የአማራ ሕዝብ ባበሳጩትና ለዚህም ትልቅ ስህተት ይቅርታ ባልጠየቁት ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለስድስት አመራሮች ዛሬ አዲስ ሹመት መስጠቱ ተሰማ።
በኢሬቻ በዓል ላይ ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው የኖሩትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ወደ ግጭት የሚያመራ አስተያየት በአደባባይ በመስጠት አሳፋሪ ተግባር የፈጸሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ስህተታቸው ሳይፀፀቱ ከ82 ዜጎች በላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ አይነተኛ ሚና የተጫወተው ጃዋር መሐመድን ወግነው “ወንድም ጁሃር ላይ የተወሰደው ዕርምጃ አግባብ አይደለም” በማለት የፌደራል መንግሥቱን አቋም የሚቃረን ሃሳብ መስጠታቸውም ይታወሳል::
ዛሬ በእኚህ ግለሰብ የሚመራው መንግሥት በተመሳሳይ የቄሮ ደጋፊና አምላኪ ናቸው የሚባሉትን የኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ ለስድስት ሰዎች ተጨማሪ አዳዲስ ሹመቶችን ሰጥቷል:: በዚህም መሰረት፦
1. አቶ አዲሱ አረጋ፦ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ
2. ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፦ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ
አስተባባሪ
3. አቶ ካሳሁን ጎፌ፦ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ
4. አቶ ፍቃዱ ተሰማ፦ የድርጅት ጽህፈት ቤት ኃላፊ
5. አቶ ሳዳት ነሻ፦ በድርጅት ጽህፈት ቤት የከተማ ፖለቲካ ዘርፍ አደረጃጀት ኃላፊ
6. አቶ አበራ ወርቁ፦ በድርጅት ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ አደረጃጀት ኃላፊ በመሆን መሾማቸው ታውቋል።
አንዋር መስጅድ ዙሪያ ያሉ ሱቆች እንዳይፈርሱ የፕላን ማሻሻያ መደረጉን ታከለ ኡማ ገለፁ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች ከአዲስ አበባ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኡለማዎች እና የቦርድ አባላት ጋር ውይይት አደረጉ፡፡ ከዚህ ቀደም በህዝበ ሙስሊሙ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከእምነቱ ተከታዮች እና ከከተማ አስተዳደሩ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ በደረሰባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መምከራቸው ተሰምቷል፡፡
የምክር ቤቱ የቦርድ አባላት የይዞታ ጥያቄዎችን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ሌሎች የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ዙሪያ ከከተማ አስተዳደሩ ሥራ ሓላፊዎች ጋር በማንሳት በመፍትኄ ሃሳቦች ዙሪያ በጥልቀት መክረዋል፡፡
በመንገድ ግንባታ ምክንያት ሊነሱ የነበሩ የታላቁ አንዋር መስጅድ አካል የሆኑ ሱቆች እንዳይነሱ የከተማ አስተዳደሩ የፕላን ማሻሻያ እንዳደረገ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በውይይቱ ወቅት መግለፃቸው በውይይቱ ላይ የነበሩትን ኡለማዎች በእጅጉ እንዳስደሰተ ነው የተነገረው::
ወደፊት የከተማ አስተዳደሩ እና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የጋራ በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመሥራት ከስምምነት መድረሳቸውን ካገኘነው መረጃ ማረጋገጥ ችለናል፡፡
ኳታር በኤርትራ መንግሥት የቀረበባት ክስ ሐሰት ነው ስትል አጣጣለች
ኤርትራ ትናንት ኳታር ከፍተኛ ባለስልጣኖቼን ለመግደል ዕቅድ አላት በማለት ያቀረበቸውን ክስና ያወጣችውን መግለጫ የኳታር መንግሥት ውድቅ አድርጎታል። በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል ለወጣው ክስ አዘል መግለጫ ኳታር በሰጠችው ምላሽ “ሐሰት ነው” በማለት ክሱን ሙሉ ለሙሉ አጣጥላዋለች።
ኳታር ተቃዋሚ ቡድኖችን በመደገፍ በኤርትራ መንግሥት ላይ አመጽና ተቃውሞን ለመቀስቀስ መጣሯን በክሱ ላይ አመልክቶ ነበር ፤ ይሁንና ኳታር ባወጣችው መግለጫ የኤርትራ መንግሥት ከጠቀሳቸው የትኛውም አንጃ ሆነ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት በመግለጽ “ይህንንም የኤርትራ መንግሥት በደንብ ያውቀዋል” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የሚታወቁትን ሌሎች ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መንገዶችን ከመጠቀም ይልቅ” በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በወጣው መግለጫ ግራ መጋባቱን ጠቁሞ ፤ ከዚህ ቀደም ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበረውና ለዚህም የተለያዩ ተግባራት ሲያከናወኑ መቆየታቸውን፤ ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር ያላትን ያለመግባባት ለመፍታት ኳታር ያደረገቸውን ጥረት በምሳሌነት የሚቀርብ ነው ሲል ይከራከራል።
የኤርትራ መንግሥት በመግለጫው “ኳታር የኤርትራ መንግሥት በእስላማዊ ተቃዋሚዎች መካከል ጽንፈኛ ሐይማኖታዊ አመለካከቶችን በማስረጽ አመጽ በመቀስቀስ፣ በወገኖቻቸው ላይ እንዲነሱ” ፍላጎት አላት ሲል ወንጅሏል።በቅርቡ የወደብ ከተማዋን ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በምሥራቃዊ ሱዳን፣ በነዋሪዎች መካከል ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን በማንሳት ኤርትራ በመግለጫዋ ኳታርን “ፖርት ሱዳን ውስጥ የጎሳ ግጭቶች እንዲከሰቱ” በማድረግ ወቀሳ መሰንዘሩ ይታወሳል።
የኤርትራን ክስ ተከትሎም የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር “ከክስና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመጠቀም ይልቅ እውነታዎችንና የችግሮቹን ስር መሰረት መለስ ብሎ እንዲመረምር” አሳስቧልዠ።
በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያጋጠመው ቀውስ እስከተፈጠረበት ጊዜ ድረስ ኤርትራ ከኳታር ጋር ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም በሳዑዲ አረቢያ በሚመሩት አገራትና በኳታር መካከል አለመግባባቱ ሲፈጠር ኤርትራ ወዳጅነቷን ከሳዑዲና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጎን በመቆም የመን ውስጥ የሚካሄደውን ዘመቻ ደግፋለች። ይህን ተከትሎ አገራቱ የመን ውስጥ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ለማገዝ ኤርትራ ከወደብ ከተማዋ አሰብ ወጣ ብሎ የሚገኝ ወታደረዊ ሰፈርን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሠራዊት እንዲጠቀምበት መፍቀዷ ይታወቃል።