ሪፖርተር || ብሩክ አብዱ
ከሕወሓት በስተቀር ሦስቱ አባል ድርጅቶችና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ የሚመሠርቱት አዲሱ ውህድ (ብልፅግና ፓርቲ) ፕሮግራም፣ በአምስት ዋና ዋና መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል፡፡
የመጀመርያው ክፍል የፓርቲው ጥቅል ዓላማ፣ መለያ እሴቶች፣ የሕዝቦች ክብር፣ ፍትሕና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ያብራራል፡፡
በሁለተኛው ክፍል ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ዓላማ ጠንካራና ቅቡልነት ዘላቂ አገረ መንግሥት መገንባትን ያመለክታል፡፡ በዚህም መሠረት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፣ እንዲሁም በተቋማዊና በሕዝባዊ መሠረት ላይ የቆመ አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባትን ያስረዳል፡፡
በክፍል ሦስት የኢኮኖሚ ፕሮግራሙ ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ዓላማ አለው፡፡ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ግቦች፣ የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ መዋቅር መገንባት፣ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማትና ምርታማነትን መሠረት ያደረገ ማኅበራዊ ፍትሕ ማረጋገጥ፣ ሀብትና ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ መገንባት መሆኑን ያመለክታል፡፡
በክፍል አራት ማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማው ሁለንተናዊ ልማት የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት ማምጣት ነው፡፡ ጥራት፣ ፍትሐዊነትና አግባብነት ያለው የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት፣ መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ሥርዓት መዘርጋት፣ የመኖሪያ ቦታ የማግኘት መብትን የሚያሟላ የቤቶች ልማት ማረጋገጥ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያገናዘበ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ማስፈን፣ የሠራተኞችን መብት ማስከበርና የሥራ ሥነ ምግባር ማሳደግ፣ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን ማጎልበት፣ የወጣቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቃሚነትና ተጠቃሚነት ማስፋት፣ ውጤታማና ተጨባጭ የሥነ ሕዝብ ሥርዓት መዘርጋት፣ ብዝኃነትን ማዕከል ያደረገ የቋንቋ ፖሊሲ፣ አገራዊ ክብርንና አገራዊ መቀራረብን የሚያመጣ የስፖርት ልማት፣ እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶችን ዘመንን እንዲሻገሩ የሚያደርግ ጥበቃ ተዘርዝረዋል፡፡
ክፍል አምስት አገራዊ ክብርን ዋና ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነትን ይመለከታል፡፡ በዚህም መሠረት የውጭ ግንኙነት ግቦች ለትብብርና ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አጋሮችን ማስፋት፣ ለጎረቤት አገሮች ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የመንግሥት ሥልጣን በመጨበጥ የጋራ የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችንን ተግብረን ተጨባጭ አገራዊ ዕድገትን ማስመዝገብ ችለናል።የምናካሂደው ውህደት እያንዳንዱ እህት ድርጅት የነበረውን የዓላማና የተግባር ውህደት በአዲስ መንፈስ ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ ኃይል እንድናሰባስብ በማድረግ በቀጣይ ለላቀ የዓላማ አንድነትና አገራዊ ድል የሚያበቃ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ይሆናል፤›› ሲል የውህድ ፓርቲው ፕሮግራም ያስረዳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በስተቀር ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባልና አጋር ድርጅቶች፣ ኢሕአዴግን የሚተካውን አዲስ ውህድ ፓርቲ ለመቀላቀል ወስነው አፅድቀዋል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሐዋሳውን የግንባሩን ጠቅላላ ጉባዔ ጠቅሶ የግንባሩን ውህደት በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁንና ይኼንኑ ውሳኔ የግንባሩ ምክር ቤት ማፅደቁን ተከትሎ፣ አዲሱን ውህድ ፓርቲ ለመቀላቀል የወሰኑ አባልና አጋር ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲን ለመቀላቀል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
አጋር ፓርቲዎች ከአሁን ቀደም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ድምፅ እንዳይኖራቸው አግልሏል ተብሎ የሚተቸውን ኢሕአዴግ ተክቶ ውህድ ሆኖ የሚመሠረተው ብልፅግና ፓርቲ አባላቱ በግለሰብ ደረጃ አባል የሚሆኑበት ሲሆን፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የተመለከቱትን አሥር መሥፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አባል መሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል በኅብረ ብሔራዊነትና በአገራዊ አንድነት ላይ ፅኑ አቋም ጽንፍ ረገጥ አመለካከትንና ተግባሮችን በፅናት የሚታገል፣ ዜጎችንና ሕዝቦችን በእኩልነት የሚያገለግል፣ የሕዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም፣ ከሙስናና ብልሹ አሠራር ራሱን ያራቀና ሌሎችንም የሚታገል፣ በፓርቲው መመርያ መሠረት ወርኃዊ መዋጮ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ እንዲሁም ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ፣ መሆን አለበት የሚሉት ይገኛሉ፡፡
በዚህ መሠረትም የፓርቲው አባል ለመሆን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የወሰኑ ሲሆን፣ አጋር የሆኑት የቤንሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመቀላቀል ወስነዋል፡፡
የፓርቲው አወቃቀር የፌዴራል አወቃቀሩን እንደሚከተልና በርካታ የሥራ ቋንቋዎች እንደሚኖሩት የሚያትተው የብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ ፓርቲው በቋሚነት የብሔራዊ ጉባዔ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን፣ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት፣ የፓርቲው የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ የፓርቲው የአካባቢ አካላት፣ የሴቶች አደረጃጀት እንዲሁም የወጣቶች አደረጃጀት ይኖሩታል ይላል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካል የሆነው ብሔራዊ ጉባዔ መደበኛ ጉባዔውን በአምስት ዓመት አንዴ ያደርጋል፡፡ ይኼ አደረጃጀት ከኢሕአዴግ አደረጃጀት ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የሚሉ የሥራ ድርሻዎችን ያስቀረ ሲሆን፣ በኢሕአዴግ በሁለት ዓመት ከመንፈቅ ይደረግ የነበረውን ጉባዔ ወደ አምስት ዓመት አራዝሞታል፡፡