የአቶ ለማ መገርሳን ቃለመጠይቅ ካዳመጥኩ በኋላ ስለእሳቸው ብዙ ነገሮችን አወጣሁ። አወረድኩ። እውነት ለመናገር ከፍርሃት የተነሳ ቃለመጠይቁን ለማዳመጥ ምጥ ሆኖብኝ በማግስቱ ነው ጨክኜ ማስፈንጠሪያዋን በመንካት የሰማሁት። ወኔ አጠረኝ። ለእሳቸው ውስጤ የሰጠው ቦታ ትልቅ ነውና ከአንደበታቸው የልዩነትና የመነጠል ትርክት ለመስማት ጆሮዬ ሳይቀር ቀፈፈው። እንደምንም አዳመጥኩት። እሳቸውን የመሰለ ብርቱ ሰው፡ የተስፋን መንገድ ያመላከቱ፡ የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ በመረዳት ትክክለኛውን መድሃኒት የቀመሙ ፖለቲከኛ ከአንድ ጫፍ ወደሌላ ጫፍ በዚህ ፍጥነት ለመቀየር እንዴት ይቻለዋል ለሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘሁለትም። የብልጽግና ፓርቲ ፈጥኗል ካሉበት ይልቅ የእሳቸው ከኢትዮጵያ አዳኝነት ወደ አንድ ብሄር ወኪልነት ለመቀየር የወሰደባቸው ጊዜ የብርሃን ያህል መፍጠኑን የተረዱት አይመስለኝም። ለማንኛውም አሁንም ለኦቦ ለማ መገርሳ ያለኝ አክብሮት እንደተጠበቀ ነው። አቶ ለማ የመረጡትን መርጠዋል። ውለታቸውን መርሳትም ሆነ ማራከስ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። ከቃለመጠይቃቸው ላይ እንደተረዳሁት ግን ሁለት መሰረታዊ ስህተቶችን ሰርተዋል።
አቶ ለማ በፓርቲና በህዝብ መሀል ስላለው ግንኙነት ግንዛቤአቸው ላይ ጥያቄ የሚያጭር ሀሳብ አንስተዋል። አንዱ ስህተት እሱ ይመስለኛል። የብልጽግና ፓርቲ አመሰራረትን በተመለከተ ”ቃለመሀላ ከፈጸምንለት ህዝባችን ጋር ሳንማከር” የምትል ነገር በተደጋጋሚ አንስተዋል። ሰሞኑን በዚሁ መንደር ያነበብኩት አንድ ጽሁፍ ላይ ያገኝሁት አባባልን ብዋሰው ጥሩ ነው። ፓርቲ ቀንድ እንጂ ጭራ አይደለም ይላል ጸሀፊው። እውነት ነው። ፓርቲ ተከታዮች እንዲኖሩት፡ ደጋፊዎች እንዲበዙለት ፕሮግራሙን ቀርጾ፡ ማንፌስቶውን አዘጋጅቶ ህዝብ ፊት ይቀርባል እንጂ ህዝብ አማክሮና አወያይቶ የሚወለድ ፓርቲ የለም። ካለም እድርና የጽዋ ማህበር እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አያሰኘውም። ፓርቲ ቀንድ ሆኖ ይቀድማል። ጭራ ሆኖ አይከተልም። ህዝብ የቀረበለትን ፓርቲ አይቶና መርምሮ የመከተል ውሳኔ በእጁ ነው። አቶ ለማ ይህቺን የፖለቲካ ሀሁ እንዴት እንደዘነጉት አላውቅም። ምናልባት አዲሱን ፓርቲ ከህዝብ ልብ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ፈልገው ሊሆን ይችላል። ለህዝብ ታማኝነት የሚገለፀው በዚህ መልኩ ነው የሚል ድምዳሜ ስህተት ብቻ ሳይሆን ጤናማም አይደለም። “እናንተ ምረጡኝ እንጂ የፖለቲካ ፕሮግራሜን ከእናንተ ጋር ተመካክሬ እቀርፃለሁ” ብሎ በምረጡኝ ዘመቻ ህዝብን ሲቀሰቅስ የነበረን ተወዳዳሪ ያስታወሰኝ አነጋገር ነው ከአቶ ለማ የሰማሁት።
ሌላው ስህተታቸው የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት አሁን ዱብ ያደረጉብን አስተሳሰባቸው ይጠቅማል ብለው መወሰናቸው ነው። የኦሮሞ ጥያቄ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ይለያል ብሎ የሚነሳ ፖለቲከኛ እዚያው መንደር ውስጥ የሚቀር፡ ወንዝ የማይሻገር እንደሚሆን ከህወሀት የማይማር ፓለቲከኛ ብቻ ነው። አቶ መለስ ዜናዊ በአስተሳሰብ የትግራይን ምድር ሳይሻገሩ 21 ዓመት የኢትዮጵያ መሪ ሆነው ይህቺን ምድር ሲሰናበቱ ሌጋሲያቸው በተወሰኑ የትግራይ ተወላጆች ልብ ውስጥ ብቻ ቀርቷል። መንደርተኛ አስተሳሰባቸው፡ በዓመታት ቆይታ፡ በዕድሜ መጨመር እንኳን የሚለወጥ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊ መሪ ሳይሆኑ፡ የኢትዮጵያን ችግር ሳይፈቱ፡ ይበልጥኑ አወሳስበውና መርዝ ተክለው ከነጥቁር ታሪካቸው ታሪክ ሆነው ቀርተዋል። አቶ ለማን በልባችን ማህደር በመልካም ጎናቸው እንድናስቀምጣቸው ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ የመለስን መንገድ አለመምረጣቸው ነበር። ጥያቄአችን አንድ ዓይነት፡ ችግራችን ተመሳሳይ፡ መፍትሄውም በጋራ የሚገኝ ነው በሚል እነስብሃት ነጋን አከርካሪ ሰብረው ከመቀሌ የሸኙት አቶ ለማና ጓዶቻቸው የኢትዮጵያውያን ችግር በጋራ የምንፈታው ነው ብለው ይዘው የተነሱት የተቀደሰ የፖለቲካ ውሳኔ እንደነበረ አንዘነጋውም።
ዛሬ ላይ አቶ ለማ የተነሳሁለት፡ የምሞትለት ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ነው ማለታቸው እጅግ አስደንጋጭ፡ በጣምም የተሳሳተ፡ ፈጽሞ መሬት ላይ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከመፍትሄ ይልቅ ችግር ሆኖ የሚያስጨንቅ ውሳኔ ነው። አቶ ለማ የኦነግን የአርባ ዓመት የከሰረ የፖለቲካ አካሄድ በቅጡ የተረዱት መስሎን ነበር። ከኦነግ ሸልፍ ላይ አዋራ ጠጥቶ ከዚያው ከሸልፍ መውረድ ያቃተውን የፖለቲካ ትርክት የሚመስል አካሄድ በዚህን ወቅት መምረጣቸው እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። ” ጽንፈኝነት ማንንም አይጠቅምም። ማዶና ማዶ ሆኖ ማቅራራት በየትኛውም አለም ላይ ውጤት ያስገኘበት ጊዜ የለም። ” የሚለውን የአቶ ለማ ንግግር መቼም የምረሳው አይደለም። የኢትዮጵያን ችግር በጋራ እንፍታ፡ ብቸኛ መንገዱም እሱ ነው በሚለው ፈዋሽ ንግግራቸው የወደድናቸው አቶ ለማ ”በቅድሚያ የኦሮሞን ችግር መፍታት ነው ያለብን” ብለው መታጠፋቸው ለእሳቸው ምን ያህል ርቀት እንደሚወስዳቸው የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው። ለኢትዮጵያ ግን ፈጽሞ መድሃኒት አይሆንም። የተለየ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የለም። ሁላችንም ተጎድተናል። ሁላችንም ዘንድ የፍትህ ጥያቄ አለ። የዲሞክራሲ ጥያቄ አለ። የነጻነት ጥያቄም እንዲሁ። ዘመኑን የሚመጥነው የፖለቲካ መስመር ይህን መሰረታዊ የኢትዮጵያ ችግር ተረድቶ መፍትሄ የሚሰጥ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ የብሄር ውክልና ይዞ ስለአንድ ብሄር እታገላለሁ የሚለው አስተሳሰብ እንደመለስ ዜናዊ ለመቃብር ላይ ጽሁፍ እንኳን የማይበቃ ታሪክ ትቶ ማለፍ ብቻ ነው።
ከአቶ ለማ ቃለመጠይቅ ሌሎች ስህተቶችንም መንቀስ ይቻላል። ለጊዜው የጠቀስኳቸው በቂ ናቸው። አቶ ለማ አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ የመስራት እድላቸው ሰፊ ነው የሚል እምነት አለኝ። በአዲስ መስመር መጻፍ የጀመሩት የፖለቲካ ትርክትን እንደነኦነግ የልዩነትና የመነጠል ባያደርጉት ለእሳቸውም፡ ለኦሮሞ ህዝብም የሚበጅ ይሆናል። ጊዜ ወስደው መክረውና ከራሳቸው ተስማምተው ጥለው የወጡትን የአንድነት ቤት መልሰው ይገቡበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ህወህቶችና ጥቂት ጽንፈኛ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች የአቶ ለማን ውሳኔ ለጀመሩት የትርምስና ቀውስ መስመር ቤንዚን አድርገው ሊጠቀሙበት እያፋሸኩ ነው። አቶ ለማ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በባለፈው ጽሁፌ ጠቆም አድርጌለሁ። ዛሬም የምለውና የምመኝላቸው አቶ ለማ በእነዚህ የሞት ነጋዴዎች ጩኸት እንዳይጠለፉ የሚያደርግ ጥንካሬን እንዲላበሱ ነው። በተረፈ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ከዶ/ር አብይ ጎን መቆም ያለበት ጊዜ ነው የሚል እምነት አለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከዛሬ የሰነበቱበትን ጭንቀት አሁን በግልጽ የተረዳን ይመስለኛል። ህግና ስርዓትን ለማስከበር አቅም ያጠራቸው ለምን እንደሆነ ምክንያትና ሰበቡን በጨረፍታም ቢሆን የተረዳንላቸው ክስተት ነው የሰሞኑ። ዶ/ር አብይ ሰፊ ህልም እንዳላቸው፡ ኢትዮጵያን ከማማ ላይ አውጥተው ሊያስቀምጧት ከልብ ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያረጋግጥ ለመሆኑ ከዚህ ሁሉ የውስጥ ሽኩቻ በኋላ በአሸናፊነት የብልጽግናን ፓርቲ እውን ማድረጋቸው ትልቅ ማሳያ ነው።
በእርግጥም ብልጽግና ፓርቲ በትላንትናው ዕለት ወሳኙን ምዕራፍ አከናውኗል። ከእንግዲህ ኢህአዴግ የሚባለው ስም የለም። ከነኮተቱ ተሸኝቷል። ሶስቱ አባል ፓርቲዎችና አምስቱ አጋሮች በሊቀመናብርቶታቸው በኩል በፊርማቸው ብልጽግናን ፓርቲ እውን አድርገውታል። ፓርቲዎቹ በተናጠል የሚኖራቸው ህልውና ከስሟል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖር እምነቱና ብሄሩ ሳይገድበው ብልጽግናን መቀላቀል መቻሉ ትልቅ ድል ነው። እነዶ/ር አብይ ተራማጅ አስተሳሰባቸውን መሬት ላይ ለማውረድ የገቡበት ፈተና ከባድ ቢሆንም በመጨረሻም ተግባራዊ የሚያደርጉበትን የመጀመሪያ ምዕራፍ አጠናቀዋል። ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የበለጸገች ለማድረግ የሚያስችሉ አፋጣኝ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርነቀል ለውጦችን በማስመዝገብ ስሙን በተግባር መተርጎም ይጠበቅበታል። ፈተናዎች መብዛታቸው አይቀርም። አባጣና ጎርባጣው በየቦታው ተገትሯል። እሾህና አሜኬላው በየኪሎሜትሩ ተደንቅረዋል። እስከዛሬ ከተመጣበት የበለጠ የወደፊቱ መንገድ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም። ወጀቡ ከወዲሁ ተነስቷል። ማዕበሉ አስፈሪ ሊመስል ይችላል። ብልጽግና ፓርቲን አምጠው የወለዱት አመራሮች ከማንም በላይ የወደፊቱን ፈተና የማሽተት አቅም እንዳላቸው ይታመናል። ይህን በመረዳትም ከወዲሁ ወገብን ጠበቅ ማድረግ እንዳለባቸው አውቀውት የገቡበት ግዙፍ ሀገራዊ ሃላፊነት ነው።