ብልፅግና ፓርቲን የሸሹት ኦቦ ለማ መገርሳ አሜሪካ ገብተዋል
የብልፅግና ፓርቲ ምስረታና የመደመር ፍልስፍናን የተቃወሙት ኦቦ ለማ መገርሳ አሜሪካ ገቡ:: ሰሞነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆኑት የለውጡ ወላጅ ለማ መገርሳ በኢህአዴግ መክሰምና ውህደት ዙሪያ የተለየ አቋም መያዛቸው በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ድንጋጤን ከመፍጠሩ ባሻገር ተስፋ የተደረገበት የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ዳግም ወደ መከፋፈልና የጨለማ ዘመን ይመልስ ይሆን የሚል ስጋትን ማሳደሩ አይዘነጋም::
የብልፅግና ፓርቲን ምስረታ ጊዜው አይደለም በሚል የተቹትና አካሄዱን ከመተቸት ባሻገር በዕምነት ረገድ የሸሹት ለማ መገርሳ የመከላከያ ሚኒስትር መሆናቸውና የለውጡን ቡድን ጸንሰውና ወልደው ያሳደጉ መሆናቸው እሳቸውን ተከትሎ ሌሎች የፓርቲው አባላት በተለይም የኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚዎች የአቋም ልዮነት ያደርጋሉ ተብሎ ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም ብልሁ ለማ መገርሳ በወሳኙ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ኢሕአዴግ ወደ ውህደት አምርቶ ብልፅግና ፓርቲን እንዲመሠርት ድምጻቸውን በመስጠት የሕወሓትን ዓላማና ፍላጎት በማጨናገፍ ዳግመኛ ታሪክ ሠርተዋል::
የእሳቸውን ውህደት መቃወም ተስፋ ያደረጉ የኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚዎችንም በዚህ መንገድ ባልተጠበቀ ሰዐት ጉድ እንዳደረጉ ያስታወሱት ምንጮቻችን ለማ መገርሳ ፓርቲው ወደ ውህደት ከመጣ በኋላ ልዮነታቸውን ገሀድ ማውጣታቸው በሳልና አስተዋይ መሆናቸውን ከማሳየቱ ባሻገር የሰለጠነ የፖለቲካ መንገድ የተከተሉ መሆናቸውን እንዳሳዮም ጭምር ይናገራሉ::
በዚህን መሰሉ አነጋጋሪ ሂደት ውስጥ ያለፉት ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተቃቅረዋል ተብለው የታሙት ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ በአሁኑ ወቅት ወደ አሜሪካ ተጉዞ በአሜሪካ ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በመከላከያ ሚኒስትሩና በለውጡ ቡድን ጠንሳሽ የተመራው ልዑክ በዛሬው ዕለት ዋሽንግተን ዲ.ሲ መግባቱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋም በትዊተር ገፃቸውአረጋግጠዋል። ጉብኝቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካን የሁለትዮሽ የመከላከያ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
ዐቢይና ለማ ከ5 ወር በፊት ግጭት ውስጥ መግባታቸውን እንደሚያውቁ የቱለማው አባ ገዳ ተናገሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ግንኙነት መሻከር የጀመረውና ልዮነታቸው መስፋት ከጀመረ መሰንበቱንና በሁለቱ ግለሰቦች መሀል አለመግባባት መኖሩን ከሰሙ አምስት ወራት መቆጠራቸውን የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ገለፁ ።
“እነዚህ የአባ ገዳ ልጆች በፊት ምን ያህል ይቀራረቡ እንደነበርና እየተራራቁ እንዳሉ የሰማነው ከአምስት ወር በፊት ነው” የሚሉት አባ ገዳ ጎበና ይህ ለኦሮሞ ህዝብ ጥሩ እንዳልሆነ ፣ ትግሉንም ወደ ኋላ እንደሚመልስ ስጋታቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች መካከል ንፋስ መግባቱን ሲሰሙ ከኦሮሞ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎችና አባ ገዳዎችም አንድ ላይ ሆነው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይንም ሆነ መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማን በተናጠል አልያም አንድ ላይ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን የቱለማው አባ ገዳ አስታውቀዋል። ያለፈው አልፏል አሁንም ወደፊት የሚቀር ብዙ ስለሆነ ሁለቱንም ማግኘት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል።
በአመራሮቹ ዘንድ የእናንተ አካሄድና ተሰሚነት ምን ያህል ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አባ ገዳ ጎበና “ለኦሮሞ ህዝብ እንዳላቸው ቅርበት የሚቀበሉትም የማይቀበሉትም አለ። አባ ገዳዎችን የሚፈልጉበት፣ የሚጠቀሙበትና የሚናቁበት ቦታ እንዳለ ለማንም ግልፅ ነው” ብለዋል። በማያያዝም ‘እንኳንስ አብሮ የሚሰራ ሰው እግር እና እግር እንኳ ይጋጫል’ የሚሉት አባ ገዳ ጎበና ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።
የዶ/ር ዐቢይና የለማ መገርሳ ልዮነት ከ5 ወር በላይ ስለመቆየቱና በአባ ገዳዎች ዕርቅ ስለመሞከሩ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው አባ ገዳ ሰንበቶ ምንም ያሉት ነገር አለመኖሩ ይታወቃል::
ተክለ ብርሃን አምባዬን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ ተቋራጮች ታክስ በመሰወር ተከሰሱ
የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ ተቋራጮችን በግብር ስወራ ክስ መስርቶባቸዋል:: ጉዳያቸውም በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንተኛና አስረኛ ወንጀል ችሎቶች መታየት ጀምሯል::
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የደረጃ አንድ ተቋራጮች ዋነኛውና በካፒታሉ የፈረጠመው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከ2005 እስከ 2008 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መከፈል የነበረበት እንዲሁም ከተለያዮ ፕሮጀክቶች የተገኘ 70.3 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር ባለመክፈሉ ክስ እንደተመሠረተበት ለማወቅ ችለናል::
ግዢ ባልተፈጸመባቸው ሐሰተኛ ደረሰኞች በመጠቀም የንግድ ግብሩ የተሰወረ ሲሆን ደረሰኞቹንም የቆረጡት ድርጅቶች በአካል የሌሉ መሆናቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል:: ከተለያዮ አገልግሎቶች የተሰበሰበ ሦስት ሚሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ በተመሳሳይ ለመንግሥት ሳይከፍሉ ቀርተዋል ሲልም በስምንተኛ የጉምሩክ ችሎት ላይ አስረድቷል::
ከአንድ ዓመት በላይ የገቢዎች ሚኒስቴር ፌደራል ፖሊስና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ33 በላይ ደረጃ አንድ ተቋራጮችን በተለይም የምርመራ ኦዲት ሪፖርትን መሰረት ያደረገ የምርመራ ሥራ ሲያካሂዱ መቆየታቸው ይታወሳል::
አብዲ ዒሌና በ47 ተከሳሾች ላይ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጠ
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመርን (ዓብዲ ኢሌ) ጨምሮ በ47 ተከሳሾች ላይ የዓቃቤ ህግን ምስክሮችን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ፤ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሃመድ ኡመርን ጨምሮ የ47 ተከሳሾችን ጉዳይ ሲመለከት ውሏል። ችሎቱ ጉዳዮን ከመረመረ በኋላ በተከሳሾች ላይ የአቃቤ ህግን የመጀመሪያ ዙር የምስክር ቃል ለመስማት ከጥር 14 እስከ 22 ቀን 2012ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት በዋለው ችሎት እስከ አሁን ያልተያዙ 10 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲሁም 3 ተከሳሾች በፖሊስ ተይዘው በዛሬው ችሎት እንዲቀርቡ ቀደም ባለ ችልቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ሆኖምበጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው 10ሩም ሆኑ ሶስቱ ተከሳሾች በዛሬው ችሎት አለመቅረባቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል። በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ከተባሉት 3 ተከሳሾች ውስጥ ሁለቱ ከሀገር ውጭ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ አንደኛው ተከሳሽ ግን በቁጥጥር ስር ውሎ ለፌዴራል ፖሊስ መሰጠቱም ተብራርቷል።
ፍርድ ቤቱ ከሀገር ውጭ ናቸው የተባሉት ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲቀርቡና ለፌዴራል ፖሊስ ተላልፎ የተሰጠው ተከሳሽም በቀጣይ ችሎት እንዲቀርብ በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል።በማያያዝ በዚህ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው በፖሊስ መጥሪያና በጋዜጣ ጥሪ ያልቀረቡ አስር ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት መወሰኑንም ታዝበናል።
በ300 ሚሊዮን ብር የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ይገነባሉ ተባለ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 12 ገጠራማ እና ከዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች ርቀው የሚገኙ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን እንዲሁም በስድስት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ::
ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ በአማራ በደቡብ በአፋር በትግራይ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎች ይከናወናሉ:: ከብሔራዊ የኃይል ማሰራጫዎች ርቀዉ የሚኖሩ 68 ሺኅ ለሚሆኑ ዜጎች ኃይል የማቅረብ አቅም ይኖራቸዋል::
ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በአገልግሎቱ ወጪ የሚገነባ ሲሆን በአጠቃላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግት ፕሮጀክትም ነው ተብሏል:: ግንባታውን ለማካሄድ የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፉ ሦስት የቻይና እና አንድ የስፔን ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈጽሟል::
ከአምስት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ የኤሌኬትሪክ አገልግልትን ለማዳረስ የተያዘው ግብ አካል የሆነው ፕሮጀክት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ በዘርፉ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና በአገር ውስጥ ያለውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት ይረዳል ተብሎ ታሜኖበታል::
ከሦስት ክልሎች በስተቀር ኤች አይ ቪ በኢትዮጵያ በወረርሽኝ መልክ መስፋፋቱ ተረጋገጠ
በኢትዮጵያ ውስጥ የተዘነጋውና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው ኤች አይ ቪ ኤድስ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢና የትውልዱ ፈተና መሆኑ ታውቋል:: ይህን ተከትሎ በሽታው በዚህ ወቅት ከሦስት ክልሎች ውጪ ኤችአይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት አረጋግጧል።
ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ቤንሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች በአስከፊው ኤችአይቪ ወረርሽኝ ውስጥ ተዘፍቀዋል ነው የተባለው – በተሰበሰበው ዳታ መሠረት። በአንጻሩ የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ቫይረሱ በወረሽኝ መልክ የያልተንሰራፋባቸውና የተሻሉ ሆነው ተመዝግበዋል።
በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሕግ መሠረት ፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከአንድ በመቶ በላይ በበሽታው ከተያዘ እንደ ወረርሽኝ ስለሚቆጠር እነዚህ ክልሎች ወረርሽኝ ውስጥ መሆናቸው ተረጋግጧል። ሆኖም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የስርጭት መጠን ሲታይ ወረርሽኝ ላይ ነው ማለት እንደማይቻል ብሔራዊ ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያ ገልጿል። ቢሮው ቫይረሱን በተመለከተ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት ይታያል ብሏል።
በየዓመቱ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ይያዛሉ ያለው ጽህፈት ቤቱ፤ ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች እየሞቱ መሆናቸውን ጠቁሞ ፤ ይህ አሃዝ ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ ቢሆንም ፤ ጎን ለጎን እንደ ሀገር መዘናጋትና ቸልተኝነትን በመፍጠሩ በዚህ ምክንያት ኤችአይቪ እስከመኖሩም የረሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲበዙ ማድረጉንም አጋልጧል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ፣ በልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች፣ በአበባ ልማት ላይ፣ በስኳር ፋብሪካ የአገዳ ቆረጣ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች መዘናጋቱ በስፋት ከሚታይባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።
የጉዳዮን አሳሳቢነትና የቫይረሱን ሥርጭት በወረሽኝ መልክ መስፋፋት በመገንዘብ መንግሥት ቀደም ሲል ለውጥ ካመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ አደረጃጀቶች፣ የመገናኛ ብዙኃንና ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ መቆጣጠሪያ ጽ/ቤቱ አስታውቋል። የአገር አቀፍ ኤድስ ምክር ቤት ጉባዔ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱ አይዘነጋም።ከዚህ የተነሳ በክልሎች ምክር ቤቱ እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ይገኛል::
ኤች አይ ቪ በአገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዶ በቁጥር 0.91 አካባቢ ነው ያለው ቢሮው ፤ የኤች አይቪ ስርጭት በክልል ደረጃ ሲታይ ግን ከአገር አቀፉ የስርጭት መጠን ከፍ ያለ የተመዘገበባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት የጋምቤላ ክልል 4.8 በመቶ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 3.4፣ የትግራይና የአማራ ክልል በበኩላቸው 1.2 የስርጭት ምጣኔ እንዳላቸውና ኤች አይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኝ የጠቆመው መረጃ የድሬዳዋ፣ የሐረር፣ የአፋርና የቤንሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች ኤች አይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብሏል። ዝቅተኛ የስርጭት ምጣኔ ያለባቸው ክልሎች ደግሞ ሶማሌ (0.01) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (0.04) መሆናቸውንም ጠቁሟል።