የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም

ወላይታ ክልል ለመሆን ታህሳስ 10 ቀንን በገደብ ማስቀመጡን ለዶ/ር ዐቢይ አሳወቀ

የወላይታ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ጋር ትናንት ሕዳር 21/2012 ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው ተወያዮ።

ውይይቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የወጣቶች ክንፍ አመራር አቶ አሸናፊ ከበደ ፤ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ካቀኑት አባላት መካከል አንዱ ናቸው። ውይይቱ በአጠቃላይ የወላይታን ሕዝብ የክልል እንሁን ጥያቄን የተመለከተ እንደነበር ፣ ውይይቱ በዋናነት ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወላይታ ሶዶ በሔዱበት ወቅት “ተወያዩበት፤ ምከሩበት” ባሉት ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንደሆነና በዚሁ መሠረት ውይይት ያደረጉበትን ሃሳብ ይዘው ለውይይት መቅረባቸውን አቶ አሸናፊ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቀደም ሲል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት የሚያስታውሱት አቶ አሸናፊ፤ በወቅቱ የነበሩት አጀንዳዎች ሦስት እንደነበሩ ይናገራሉ ፤ “የወላይታ ሕዝብ ብቻውን ክልል መሆን ነው ወይ?፣ ሌሎችን ይዞ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ክልል መሆን ነው ወይ? አጠቃላይ ሌሎች 55ቱን ይዞ ሠፊ ሕዝብና መሬት፣ ሰፊ የተማረ ሰው ያለበት በመሆኑ አንደ ዋና መቀመጫ እንዲያገለግል በሚል ዙሪያ ነበር የተወያየነው” በማለትም ይተነትናሉ።

በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ አቋማቸውን ማስቀመጣቸውንም ይፋ አድርገዋል። ይህን ተከትሎም ክልል የመሆንን ጥያቄ የወላይታ ሕዝብ ብቻውን የሚወስነው ባለመሆኑ፤ ተጨባጭነቱም ሊረጋገጥ ስለማይችል በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንደማይችል ፤ እንዲሁም አጎራባች ያሉ ዞኖች ጋር አንድ ክልል መሆንንም አንደ አማራጭ የወላይታ ሕዝብ ተወያይቶበት፤ ሌሎች ከመጡ ማቀፍ እንደሚችል ከዚያ ውጭ ግን በሌሎች ዕጣ ፈንታና መብት ውስጥ ገብቶ መወሰን የወላይታ ሕዝብ ሥልጣን አለመሆኑን እንደተነጋገሩበት ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ ውይይት መነሻነት ወላይታ ራሱን ችሎ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ ወላይታ ሶዶን ደግሞ ማዕከል አድርጎ የራሱን ክልል እንዲመሠርት የሁሉም ሕዝብ ድምፅ በመሆኑና ሕገ መንግሥታዊ መብት ስለሆነ ሌሎች አማራጮች እንዳማይሠሩና እንደማያዋጡ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን አቶ አሸናፊ ገልፀዋል።

በትናትናው ዕለት በተደረገው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ከሆነ ጥያቄውን እርሳቸው እንደማይመልሱት በመግለፅ፤ በሕጉ መሠረት እንዲሄድ ከምርጫ ቦርድ ጋር እንደሚነጋገሩ እዚያው ምላሽ በመስጠት ለቀሪ ጉዳዮች በተወካዮች በኩል ሰፋ ያለ ምላሽ እንደሚሰጡ ማሴታወቃቸውንም አያይዘው ተናግረዋል።

“የወላይታ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ራሱን በክልል አደራጅቶ መምራት መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀን ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎች አማራጮችን አይታችኋል ወይ ተማክራችኋል ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅረበውላቸው እንደነበርም አልሸሸጉም:: ሆኖም የቀረቡት አማራጮች ሁሉ የሕዝብ ጥያቄ ባለመሆናቸው፤ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄም ባለመሆናቸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት የወላይታ ሕዝብ የሚጠይቀው የራሱን በሕገ መንግሥት የተቀመጠውን መብት እንጅ የሌሎችን እጣ ፈንታ በሚወስን መልኩ መጠየቅ አይችልም በሚል ውሳኔ ላይ የተደረሰበትን የሕዝብ አቋም አንፀባርቀው መውጣታቸውን አቶ አሸናፊ አብራርተዋል።

ወላይታ ክልል እሆንበታለሁ ያለውን ቀነ ገደብም ታህሳስ 10/2013 ዓ.ም አድርጎ አስቀምጧል። ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ተወካዩ፤ “በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንቀፅ 47/42 በተቀመጠውና በሌሎች አንቀፆች የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የምርጫ ቦርድ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል ይላል” ሲሉ አንቀፅ መዘው ተከራክረዋል። በመሆኑም ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያደራጁ ታህሳስ 10 አንድ ዓመት ይሞላል፤ ከዚህ በኋላ ጥያቄው መመለስ ካልተቻለ ሕዝቡ ቀኑን ጠብቆ የራሱን ሉዓላዊ ሥልጣን ይጠቀማል ሲሉም አሰጠንቅቀዋል። ይሁን እንጅ በሲዳማ የተፈጠረውን ስህተት ለመድገም እንዳማይፈለግም አመላክተዋል።

“ሰላማዊ በሆኑ መንገዶች በሙሉ ታህሳስ 10 ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄድበት ቀን ካልታወቀ፤ የራሱን ውሳኔ አሳውቆ አቋሙን ገልፆ ፤ቀጣይ ሰላማዊ ትግሎች በሌሎች መንገዶች ይሄዳሉ” ያሉት ተወካዮ ፤ በዚህ ሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ሓላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታልም ብለዋል::

ኢትዮጵያ የባንክና የኢንሹራንስ ተቋማትን ለውጭ ሃገር ባለሀብቶች ክፍት አታደርግም ተባለ

ኢትዮጵያ የባንክና የኢንሹራንስ ተቋማትን ለውጪ ባለሃብቶች ተሳትፎ ክፍት እንደማታደርግ ሮይተርስ ጉዳዩን በሚመለከት የተዘጋጀን ረቂቅ ሕግን ዋቢ አድረጎ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ቢሆንም የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፎች ግን አሁንም ዜጎቿ ብቻ የሚሳተፉባቸው መስኮች ሆነው እንዲቆዩ ልታደርግ መሆኑን የዜና ተቋሙ ተመለከትኩት ባለው ረቂቅ ሕግ ላይ ሰፍሯል ሲል አስታውቋል።

የተለያዩ የውጪ ባለሃብቶችና ተቋማት ኢትዮጵያ ክፍት ታደርጋቸዋለች ተብለው የሚጠበቁ ተቋማትን ለመግዛትና በመንግሥት እጅ ስር ብቻ ተይዘው በነበሩ ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት እየገለጹ ነው ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማሳደግ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩ ዘርፎች ላይ የውጪ ባለሃብቶች ክፍት እንደሚሆኑ መገለፁ ይታወሳል። ተዘጋጅቷል በተባለለትረቂቅ የኢንቨስትመንት ሕግ ላይ እንዳመለከተው የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ አነስተኛ የቁጠባና የብድር የገንዘብ ተቋማት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ የተተዉ ዘርፎች ይሆናሉ።

ባለፈው ሐምሌ የአገሪቱ ምክር ቤት አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የባንኮችን አክሲዮን ለመግዛት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሕግ ሲያወጣ፤ በበርካቶች ዘንድ ቀስ በቀስ ዘርፉ ለውጪ ባለሃብቶችም ክፍት ሊደረግ ይችላል የሚል ተስፋን ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም::

ሮይተርስ አረጋግጫለሁ ያለው ረቂቅ የኢንቨስትመንት ሕግ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት ሳምንታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እየጨመረ የሚሄድና ወጣት ሕዝብ ያላት ሲሆን ኢኮኖሚዋም ከአስር ዓመታት በላይ በሁለት አሃዞች ሲያድግ ቆይቷል። ነገር ግን በአገሪቱ የሚስተዋለው ብሔርን መሰረት ያደረገ ውጥረትና ግጭት ኢኮኖሚው ላይ ስጋትን ከፍተኛ የሰጋት ጥላን ጥሏል ማለት ይቻላል።

ኤርትራዊው ድምጻዊ ተክለ ነጋሲ (ወዲ ማማ) በአዲስ አበባ ከባድ ድብደባ ተፈጸመበት

“ወዲ ማማ” በሚል የቅጽል ስም የሚታወቀው ኤርትራዊው ሙዚቀኛ ተክለ ነጋሲ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በማይታወቁ ሰዎች ጥቃት እንደተፈጸመበት ተናገረ።

ድምጻዊው ጥቃቱ የተፈጸመበት ከትናንት በስቲያ እሁድ ከሰዓት በኋላ ነው:: በተጠቀሰው ቀን ገርጂ በሚገኘው አንበሳ ጋራዥ አካባቢ ፣ በእግሩ በሚጓዝበት ወቅት እስካሁን ድረስ ማንነታቸውን በማያውቀው አምስት ሰዎች ጥቃቱ እንደተፈጸመበት አስታውቋል:: ድምጻዊ ተክለ ጥቃቱን ካደረሱበት ሰዎች ጋር ምንም አይነት ንግግር እንዳልነበረና አላማቸው ጉዳት ማድረስ ብቻ እንደሆነምገልጿል። “ምንም አይነት ንግግር አልተናገሩኝም፤ በቀጥታ ወደ ድብደባ ነበር የገቡት” በማለትም ክሰተቱን አብራርቷል።

ኤርትራዊው ድምጻዊው ተክለ ነጋሲ ሱዳን ውስጥ በነበረበት ጊዜ በደረሰበት የመኪና አደጋ እግሩ ተሰብሮ እንደነበር ፣እግሩ ላይም ብረት እንዳለው ጠቁሞ ጥቃቱን የፈጸሙበት ሰዎች በተደጋጋሚ በአደጋው ጉዳት የደረሰበት እግሩን ይመቱት እንደነበርም አስታውሷል።

ከዚህ በመነሳት ደብዳቢዎቹ ከባድ አደጋን ለማድረስ ዕቅድ እንደነበራቸው፣ ጥቃቱም የታቀደ ከመሆኑ ባሻገር “በደንብ የሚያውቁኝ መሆን አለባቸው” የሚል ግምት እንዲይዝ ያስገደደው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል። ድምጻዊ ተክለበተፈጸመበት ድብደባ ሳቢያ በቀኝ እጁ፣ በአፍንጫው፣ በጭንቅላቱና የግራ ኩላሊቱ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትም አስረድቷል።

ኤርትራዊው ተክለ (ወዲ ማማ) የትግርኛና የትግረ ቋንቋዎች ዘፈኖችን ግሩም አድርጎ በመጫወት ይታወቃል። የገርጂ ፖሊስ ጣቢያ ባልደረባ የሆኑት ምክትል ሳጅን ዮሴፍ ተስፋዬ፣ አርቲስቱ በትናንትናው ዕለት ስለደረሰበት አደጋ ሪፖርት እንዳደረገ አመላክተው “ትናንት በደረሰን መረጃ መሰረት አምስት ሰዎች መሆናቸውና አካላዊ ጥቃት አድርሰው ምንም ነገር ሳይወስዱበት በመሰወራቸው ጥቃቱ ከዝርፊያ ጋር የሚያያዝ ነው የሚል ግምት እንዳይኖረን አድርጓል” ሲሉ ጉዳዮን በማስመልከት ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል። “ተጎጂው (ድምጻዊ ወዲ ማማ) አለባበሳቸው ወይም መልካቸውን ማስታወስ የሚችል ከሆነ ተከታትለን ልንደርስባቸው እንችላለን” በማለትም በጠራራ ፀሐይ ድብደባ የፈጸሙት ሰዎች የመያዝ ተስፋ የጠበበ እንደሆነም ይፋ አድርገዋል::

በሕገ ወጥ ላኪዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ተከትሎ የሰሊጥ ዋጋ ቀነሰ

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ያሳየው የሰሊጥ ዋጋ በአገር ውስጥ ገበያ በግማሽ ቀንሷል:: ከዚህ ቀደም ሰሊጥ የመግዣ ዋጋው የናረውየግብይት ሰንሰለቱን መንግሥት የመቆጣጠር አቅሙ ደካማ በመሆኑ ነው ተብሏል::

ላኪ ድርጅቶች የሰሊጥ ምርትን ከአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ በላይ በመግዛት ለዓለም አቀፉ ገበያ ባነሰ ዋጋ የሚያቀርቡበት ከስርዓት የወጣ ግብይት ለዋጋ ጭማሪው  ምክንያት መሆኑን ተከትሎ  የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  ስርዓት በመዘርጋቱ  የዋጋ ልዮነቱ እንደተስተካከለ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር አስታውቋል::

የሰሊጥ ዋጋ ጭማሪው በላኪዎች ያልተገባ የዋጋ ድርድር የተፈጠረ በመሆኑ የአሁኑ የሰሊጥ የዋጋ ማስተካከያ ቅናሽን የሚያመለክት ሳይሆን ከዓለም ዐቀፉ ገበያ የሰሊጥ ዋጋ መሸጫ ጋር የሚናበብ እንዲሆን አስችሎታል ሲሉ የላኪዎቹ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አሰፋ ዮሐንስ ይናገራሉ::

ላኪዎች ከአገር ውስጥ የሚገዙትን ሰሊጥ ከዓለም ዐቀፉ ገበያ በቶን 200 እና 300 ዶላር ዋጋ ከፍ አድርገው በመግዛት ለዓለም አቀፉ ገበያ በዝቅተኛ ዋጋ ሲያቀርቡ ቆይተዋል:: የመንግሥትን የመቆጣጠር አቅም ማነስ በመጠቀም ከሚልኩት ምርት በኪሳራ መልክ የሚያገኙትን ዶላር ለሌልች ሸቀጦች ማስገቢያ አድርገው ስለሚጠቀሙበት እስካሁን ድረስ ይህንን መንገድ ሲከተሉ ነበር:: አሁን ላይ ከዓለም ዐቀፉ ገበያ ጋር የተደረገው ማስተካከያ አገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ተረጋግጧል::

ከአዋሽ ቁልቢ የሚወስደው መንገድ ዕዳሳት ሊደረግለት ነው

በኦሮሚያ ክልል ከአዋሽ መኢሶ እንዲሁም ከአዋሽ ቁልቢ ድሬደዋ ያሉት ሁለት መንገዶች እንደሚታደሱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ::

መንገዶቹ ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆኑ በመሆናቸው መልሶ የመገንባት እንዲሁም የተሻሉ መስመሮችን መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል:: በዚህም መሠረት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተቋራጮች የመንገድ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችላቸው የጨረታ ማስታወቂያ ላይ እንዲሳተፉ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጥሪ አቅርቧል::

የመንገዱ መሠራት በቀዳሚነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን የሚያሳልጥ ከመሆኑ ባሻገር በመስመሩ ላይ የሚደርሱትን አደጋዎች ለመቀነስትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል::

ባለሥልጣኑ በያዝነው በጀት ዓመት 91 የመንገድ ፕሮጀክትችን በ150 ቢሊዮን ብር ለመሥራት አቅዶ መነሳቱን አስቀድሞ በገለጸው መሠረት ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በአገሪቱ ረጅም ድልድይ የሆነው የአባይ ድልድይ ሥራ እንደማካትም መጥቀሱ ይታወሳል::በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ትስስርን የሚያዳብሩ ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተነግሯል::

የዲላ ሪፈራል ሆስፒታል በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ  የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ነው

የዲላ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን የህክምና መስጫ ቦታ ችግር ለመቅረፍ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለፀ፡፡ ሆስፒታሉ የጌዴኦ ዞንን ጨምሮ ለሲዳማ ዞን አጎራባች ወረዳዎች፣ ለአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጂና ቦረና ዞኖች ለሚኖሩ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ሆስፒታሉ የህክምና መስጫ ቦታ ችግር እንደገጠመው የጠቆሙት የሪፈራል ሆስፒታሉ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የቦርድ ሰባሳቢ ዶክተር ዮናስ ሰንደባ ፤ ችግሩን ለመቅረፍ፣ የአገልግሎት ጥራትና ብቃቱን ለማሳደግ 894 ሚሊየን ብር በሚሆን ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡ የግንባታው አፈጻጸምም 84 ነጥብ 6 በመቶ እንደደረሰና በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የዲላ ሪፈራል ሆስፒታል በመማር ማስተማሩ ሂደት ዋና ዋና የሚባሉ የጤና ፕሮግራሞችን የሚሰጥ ሲሆን በሀገሪቱ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን በማስመረቅ ረገድ የጎላ ድርሻ እያበረከተ ነው ተብሏል፡፡ ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው የመደበኛ የሕክምና አገልግሎቶች በተጨማሪ የአይን ህክምና ማዕከል በመገንባት ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ፣ በዞኑና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡

የዲላ ሪፈራል ሆስፒታል የአጥንት ስብራት ህክምናን ጨምሮ በደቡብ ክልል ሁለት ቦታ ብቻ የሚሰጠውን መድኃኒት የተላመደ የቲቢ ህክምናና የፆታ ጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶች ነፃ ህክምና እየሰጠ ሲሆን ፤ ሌሎች ዘመናዊ ህክምናዎችን ለመስጠት በያዝነው ዓመት የሲቲ ስካን ማሽን አስገብቶ አገልግሎት ለመጀመርና የካርድ ክፍል አገልግሎትን በኮምፒውተር የታገዘ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኩላሊት እጥበት እና የፌዝዮቴራፒ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የሪፈራል ሆስፒታሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶተር ሰላማዊት አየለ ከወዲሁ አብስረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በኬንያ ደህነነታቸው እንዲጠበቅላቸው እንደሚሠሩ ኡኹሩ ኬኔያታ አስታወቁ

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያውያን በኬንያ እንደ ሀገራቸው ሠርተው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥት እንደሚሠራ ገለፁ፡፡

ኡሁሩ ኬንያታ ከኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በዲጎድያ ማኅበረሰብ ንጉስ አብዲሌ የተመራውን የልዑካን ቡድን በብሄራዊ ቤተመንግሥት ተቀብለው አነጋግረው በተለያዮ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ባለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኬንያ የመጡ ኢትዮጵያውያን ሠላማዊ ኑሮ እየኖሩ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከኬንያውያን ጋር አንድ በመሆን ሀብት አፍርተው ፣ ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውንና እንዲህ ዓይነቱ ጤናማ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጎረቤቶቻችን ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖር እንሠራለን ሲሉ መናገራቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

ከኬንያ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ለሚያደርገው ጥረት ፕሬዚዳንቱ አመስግነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመደመር መጽሐፍ ናይሮቢ በመመረቁ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡

በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው÷ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኬንያውያን እና መንግስታቸው ለሚያሳዩት ፍቅር እና ክብር አመስግነው የኬንያውያን አንድነት እና ዕድገት ለማረጋገጥ የተዘጋጀው የህብረት ሰነድ ይፋ በመሆኑም ለፕሬዚዳንቱን የ ደስታ መልክት አስተላልፈዋል፡፡

LEAVE A REPLY