የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም

ገነት ዘውዴና ካሱ ኢላላ የህወሓት ታማኝ መሆናቸውን በመቀሌው ስብሰባ አረጋገጡ

በሕወሓት የሚተዳደረው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት “ሕገ መንግሥትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓትን ማዳን” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ከትናንት ሕዳር 23/2012 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ በአምባገነኑ ስርዓት ውስጥ የሕወሓት ታማኝ አሽከር ሆነው በጥቅም የበለፀጉ የቀድሞ ባለሥልጣናት፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል መልዕክት አስተላልፈዋል ።

ዶ/ር ደብረፂዮን በመልዕክታቸው በአሁኑ ወቅት ያለው የሁሉንም ፍላጎት የማያስተናግድ፣ የጠቅላይነት አስተሳሰብ መኖር አገሪቷን ወደ ከፋ ሁከትና መበተን ይወስዳታል ብለዋል። “በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተተበተበ ሃገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ ምክንያት፣ ለአደጋ ተጋላጭነታችንን እያየነው መጥተናል” ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ ለሁሉም መሠረት የሆነው ሠላም መደፍረስ፣ የሕግ የበላይነት የማይከበርበት፣ የአገሪቷ ሕገ መንግሥት በግልፅ የሚጣስበት ሁኔታ አለ ብለዋል።

ዜጎች በአገራቸው እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መሥራት የተቸገሩበትና ለጥቃት የተጋለጡበት ወቅት ላይ መሆኑንም በማከል አገሪቷ በአደገኛና አስፈሪ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ያሉት የሕወሓቱ አመራር፤ በመሆኑም ኢትዮጵያን ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ለማላቀቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የቱን መንገድ መከተል ያሻል የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ከተጨማሪ ጉዳትና ጥፋት ማዳን ይቻላል ብለዋል።

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፤ መድረኩ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የመሰላቸውን ሃሳብ በማንሸራሸር ትግል የሚያደርጉበት እንጂ፣ ሃሳብ ወደ መድረክ እንዳይመጡ የሚታፈኑበት ባለመሆኑ የፖለቲካዊ አጀንዳዎች በሰላምና፣ በሕጋዊ መንገድ በማካሄድ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን የሚያጠናክር አጋዥ የፖለቲካ መድረክ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

“የተለያየ ሃሳብ የሚፈሩ በውይይትና በመድረክ የማያምኑ ደካሞች፣ በዚህ መድረክ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች እንዳይሳተፉ በተለያየ መልኩ ጫና በማድረግ ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸውን አሳይተዋል” ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን ማንነታቸውን በስም ያልጠቀሱ አካላትን “የውጭ ጠላቶቻችን የአገራችንን መዳከም ብቻ ሳይሆን መበታተን የግድ አስፈላጊ ነው ብለው በግላጭ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው” ካሉ በኋላ ካለፈው ስህተት በመማር ቀጣይ የኢትዮጵያ ጉዞ የተቃና እንዲሆን ጠቃሚ ድምዳሜዎች ላይ የሚደረስበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፤ የውይይቱ አሰናጅ  ሕወሓት አለመሆኑን በመጥቀስ ጀምረው፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በተካሄደው የመጀመሪያው ውይይት ወቅት በተዋቀረው ኮሚቴ አማካኝነት 50 የሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደተጋበዙ በመጠቆም እርሳቸውም እዚህ ውይይት ላይ ሲካፈሉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

“ባለፉት 27 ዓመታት የፌደራል ሥርዓቱ በዲሞክራሲ ተደግፎ አላደገም፣ ቋንቋን መግፋት፣ ማንነትን የመግፋት ሁኔታዎች ነበሩ” የሚሉት የሕወሓት ስሪት “ባለፉት 3 ዓመታትም ለውጥ መጥቶ ነበር” የሚለውን አባባል ተቀብለው ለውጡን ተቀብለው የመጡት የሕዝቡ ጥያቄ ትክክል መሆኑን በማመን የሕዝቡን ጥያቄ ወደ መመለስና ሃገር ወደ ማረጋጋት ነው የሄዱት በማለት ተናግረዋል።

“ይሁን እንጅ ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠው መብት እየተጣሰ ነው፣ ዜጎች እየተንቀሳቀሱ መሥራት አልቻሉም፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል በመሆኑም ውይይቱ ሕገ መንግሥቱ ይከበር” የሚል አንድምታ አለው ሲሉም የአጥፊው ቡድን ተቆርቋሪነታቸውን አሳይተዋል።

“አሁን ያለው አስተዳደርም የሕዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ‘መደመር’ እሳቤ ነው ያመጡት” የሚሉት አቶ ተስፋዬየኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲን ሕገ ወጥ ነው በማለት አብጠልጥለዋል:: ይሄ ፓርቲ ሕጋዊ ካልሆነ ማን ነው ሃገሪቱን እየመራ ያለው? ሕዝቡ በማያውቀው ፓርቲ እየተመራ ነው?” በማለትም ስርዓቱን በአደባባይ ወንጅለዋል።

ከስልጣኑ ተገፍቶ መቀሌ የከተመው ቡድን በጠራው ዲስኩር ላይ በወያኔ ዘመን ሲጠሯቸው አቤት በማለት የአምባገነኑን መንግሥት ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ የኖሩት ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ ካሱ ኢላላ፣ የበረከት ስምዖን ቀኝ እጅ የነበረውና በአማራ ሕዝብ ላይ ሲቀልድ የኖረው ወንደሰን ከበደ መቀሌ ድረስ በመጓዝ የጨቋኙ ሕወሓት ታማኝ አሽከር መሆናቸውን አገር ለማፈራረስ በሚዶልተው ጉባዔ ላይ በመታደም አረጋግጠዋል::

ለዓመታት ከወያኔ ቀለብ እየተሰፈረላቸው እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገርላቸው በተቃዋሚ ፓርቲ ስም ሲነግዱ የኖሩት አየለ ጫሚሶ ትዕግስቱ አወልን ጨምሮ የተለያዮ ሕወሓት ጠፍጥፎ የሠራቸው ግለሰቦችም መቀሌ ገብተው የክፉ ቀን ወዳጅነታቸውን አሳይተዋል::

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ባንኮች የተሳተፉበት የግምጃ ቤት ሰነድ ለሽያጭ ቀረበ

የንግድ ባንኮች ተሳታፊ የሆኑበት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ታውቋል።

ለሽያጭ የቀረበው ሰነድ ጠቅላላ ዋጋ 500 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 250 ሚሊዮን ብሩ የ28 ቀን፣ ቀሪው 250 ሚሊዮን ብር ደግሞ የ91 ቀን መሆኑንም የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ሁል ጊዜም ረቡዕ ዕለት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤በጨረታው የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ እንዲሁም ሌሎች የልማት ድርጅቶች ተሣታፊዎች ነበሩ ተብሏል።

በዛሬው ዕለት የተከናወነውን ሽያጭ ለየት የሚያደርገው በይፋ ውድድር የሚካሄድበት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ባንኮች የሚሳተፉበትና የወለድ መጠኑም በገበያ የሚወሰን መሆኑ ነው። በሌላ በኩል መንግሥት የካፒታል ገበያ በይፋ፣ በስፋት ለማካሄድ እያደረገ ያለው የዝግጅት አካል እንደሆነም ነው የተነገረው።እንዲህ ዓይነቱ አሠራር መንግሥት ለተለያዩ ዓላማዎች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ቀጥታ ከብሄራዊ ባንክ ከመበደር ይልቅ ከገበያው ላይ  እንዲበደር ያስችለዋል በሚል ታምኖበታል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ይህ መንግሥት ከብሄራዊ ባንክ ሲበደር ለአላስፈላጊ የገንዘብ ህትመት በመዳረግ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያባብስ ጠቁመው የአሁኑ አካሄድ ግን ይህን በመቅረፍ ግሽበትን ለመከላከል እንደሚያግዝ መስክረዋል።

መንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭን በአዲስ መልክ የጀመረው በቅርቡ የግል የንግድ ባንኮች ላይ ሲተገብረው የቆየውን የ27 በመቶ የአስገዳጅ የቦንድ ግዢ ማንሳቱን ተከትሎ ሲሆን ፤አሁን ላይ የተጀመረው የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የ28 ቀን፣ የ91 ቀን፣ የ182 ቀን እና የ364 ቀን  ሰነዶች መሆናቸው ተረጋግጧል።

የደቡብ ክልል አመራሮች ውህደቱን በተመለከተ እየተወያዮ ነው

የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲው ውህደት አስፈላጊነት እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ እየተወያዩ መሆናቸው ታውቋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በቅርቡ ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።

በዚህ መሠረት ለፓርቲው አባላት በፓርቲው አጠቃላይ አላማዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ተነግሯል። በዛሬው ዕለትም የደቡብ ክልል የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ አላማዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ እየመከሩ ነው።

የምክክር መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፥ አዲስ ራዕይና እሳቤ ይዞ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተቋቋመው ብልጽግና ፓርቲ ትልቅ ድልና ተስፋ መሆኑን አስረድተዋል።ለዚህም አላማውን በአግባቡ ተረድተው ተግባራዊ የሚያደርጉ አባላትና አመራሮች ያስፈልጉታል ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ፓርቲው በዴሞክራሲ፣ በፍትህና በኢኮኖሚ መስክ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና የተገኙ ገድሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በሀገሪቱ የተሻለ የብልጽግና ደረጃን ለማምጣት የተቋቋመ ነው ካሉ በኋላ ፤ የፓርቲው አባላት፣አመራሮችና መላው ህዝብ የዚህን ውህድ ፓርቲ አላማዎችና ሀገራዊ ግቦች በመረዳት፣ በፓርቲው ዙሪያ የሚነዙ የተዛቡ መረጃዎችን በመዋጋት ለፓርቲው ስኬት ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በውይይት መድረኩ የደኢህዴን ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ የመነሻ ሰነድ አቅርበው ውይይት እንደተደረገበትም ለማወቅ ተችሏል።

የደህንነት ቀበቶ መመሪያ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

አዲሱ የደህንነት ቀበቶ መመሪያ ከጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአሽከርካሪውና በሁሉም ተሳፋሪዎች ላይ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ተባለ።

አዲሱ መመሪያ በመንግሥትና በግል ለሠራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ እስከ 150 ኪሎ ሜትር በሚጓዙ ሚኒባሶች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም ከ5 እስከ 8 መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ልዩ ባሶችና ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

በተጨማሪም የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ ከ12 እስከ 15 ሰው የሚጭኑና በከተማ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የብዙኃን አገልግሎት የሚሰጡ የከተማ አውቶብሶች ለአሽከርካሪውና ፊት ወንበር ላይ ለሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ መጠቀም እንደሚኖርባቸው በመግለጫው ላይ ሰምተናል።ለግል አገልግሎት የሚጠቀሙ አውቶሞቢሎች የሕጻናት ደህንነት መጠበቂያ ቦርድ ያለው ማካተት ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።

በአስመጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አዲስ የመንግሥት፣ የግል፣ የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎች በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በሚወጣው መስፈርት መሠረት ለአሽከርካሪውና ለተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ የተገጠመላቸው መሆን አለበት። በብዙሃን ትራንስፖርት ቆመው የሚጓዙ እና አጭር ርቀት የሚጓዙ ቀበቶ እንዲያስሩ የሚያስገድደው ህግ አሁን በአዲሱ መመሪያ አስገዳጅነት እንደማይኖረው ይፋ ተደርጓል። በባለሁለትና በባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ በግዳጅ ስራ ላይ በተሰማሩ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆንም ታውቋል።

LEAVE A REPLY