የአበል ገዳይ – “የሆድ ጉዳይ ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉ ነው።
አየለ ጫሚሶ የ1997 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ቦታ ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ግን አልተሳካለትም። ቢሳካለት ኖሮ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ሳስበው ይዘገንነኛል። ሰውዬው የሞራል እንጥፍጣፊ የለውም። “ጅብ” የሚለውም አይገልፀውም።
አንድ ቀን ምን ሆነ? የታሰሩ የቅንጅት መሪዎች ስለሚፈቱበት ሁኔታ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር ለመነጋገር ኦስትሪያ ኤምባሲ ቀጠሮ ነበረን። አውሮፓ ህብረትንና አሜሪካንን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች ነበሩ። በውይይቱ መጨረሻ ላይ ጫሚሶ ድንገት ተነስቶ የገንዘብ ዕጥረት እንዳለበትና አምባሳደርቹቿ እንዲረዱት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ኩራቱን ጥሎ – ያለሀፍረት ጠየቀ። እኛ በተቀመጥንበት መደበቂያ ቀዳዳ አጣን። እሱ ግን ብዙ ዶላሮችና የመቶ ብር ረብጣዎች በመሰብሰብ ኪሱን ሞላ።
ለተመሳሳይ ጉዳይ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽ/ቤት ጫሚሶ ከእኛ ጋር አብሮን ተገኝቶ የተናገረውን መልሼ መናገር ያሳፍረኛል። ሰውዬው ጭራሽ ይሉኝታ የሌለው አጋሰስ ነው። በወቅቱ በነበረው የደህንነት ኃይል እየታገዘ በቅንጅት አባላት በተለይ በእኔ ላይ ያልፈፀመው ደባ አልነበረም። አቶ ተመስገን ዘውዴ ጋርም ከመጨቃጨቅ አልፎ ዱላ እስከመማዘዝ ይደርስ ነበር። አቶ ተመስገን ከስድባቸው ሁሉ ጫሚሶን በተደጋጋሚ “ሽንፊላ” የሚሉት ነገር ሳልወድ በግድ ያስቀኝ ነበር።
* * *
ትዕግስቱ አወሉ ወደ ፖለቲካ ከገባ ጀምሮ የፓርቲ ንብረት በመሸጥና ቢሮ በማከራዬት የራሱን የገቢ ምንጭ በመፍጠር የሚታወቅ ሰው ነው። በተለይ በ2007 ምርጫ ዋዜማ ከደህንነት ኃይሉና ከ”ምርጫ ቦርድ” ተብዬው ጋር በመመሳጠር አንድነት ፓርቲን ከተቆጣጠረ በኋላ እጅግ በውድ ዋጋ ተገዝት ከውጭ ገብት የነበረ አዲስ; ዘመናዊና ግዙፍ የማተሚያ ማሽን ሸጦ መብላቱን ሳስበው ዛሬም ንዴት ይወረኛል።
* * *
ስለመስፍን ሽፈራው ብዙም በቅርብ የማውቀው ነገር የለም። ከቅርብ ርቀት እንደምሰማው ግን ሰውዬው በጣም funny ነው። ከእሱ በቀር ሌላ አባል የሌለው ፓርቲ አለኝ እያለ በየመድረኩ ሲጎለት ማዬት በአግራሞት ያስፈግጋል።
* * *
አቶ/መቶ አለቃ? ቶለሳ ተስፋዬ በመንግሥት የደህንነት ኃይል እየታገዙ እነ ፕ/ር መረራ ጉዲናን በጉልበት አባርሮ ኦብኮን የነጠቀ ወሮበላ ነው። አቶ/መት አለቃ? በደህንነት ኃይሉ እገዛ የኦብኮን ቢሮ በጉልበት ከተቆጣጠሩ በኋላ ገዳም ሰፈር በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ሳይቀር ሽጉጥ ሲመዝ እንደነበር የዚያ ሰፈር ልጆች በሀፍረት ሲያወሩ እሰማ ነበር።
* * *
ሌሎችም እንቆቅልሽ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ።
በተለይ ደግሞ ራሳቸውን የአገው ሸንጎና የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነን ብለው የሚጠሩት ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም; ዓላማና ግባቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ አይመስሉም። ከዚህ አንፃር የኃይል አሰላለፍ ምርጫቸው የህወሓት ቡችሎች መሆናቸውን በግልፅ ያሳብቃል።
* * *
እንግዲህ ህወሓት እነዚህንና መሰሎቻቸውን ይዞ ነው የመቀሌውን ግንባር ለመፍጠር ደፋ ቀና ሲል የከረመው። “ሲያልቅ አያምር” ይላል ያገሬ ሰው። እንጅማ እነ አየለ ጫሚሶ ከርሳቸውን ከመሙላት ያለፈ ፖለቲካዊ ፋይዳና ሚና ሊኖራቸው እንደማይችል ከህወሓት በላይ በቅርብ የሚያውቃቸው ያለ አይመስለኝም።
* * *
ታዲያ ምን ይረቡናል ብለው ነው ህወሓቶች ለመጦሪያና ለህክምና ወጭ የሚሆናቸውን (ከኢትዮጵያ ህዜብ የዘረፉትን) ገንዘብ ለነጫሚሶ አበል በመክፈል የሚያባክኑት?