የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልን ለማቋቋም ከጅቡቲ ጋር ከስምምነት ላይ አልተደረሰም
ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ትገነባዋለች የባሕር ኃይሏን በጂቡቲ ለማቋቋም የተደረሰ ስምምነት የለም ተባለ።
የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ ፣ የባሕር ኃይሏን ሦስት አስርት ዓመታት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ጂቡቲ ውስጥ መልሳ ልታቋቁም እንደሆነ በስፋት እየተወራ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ለንባብ የበቃው ካፒታል የተሰኘው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተም የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ፤ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ጂቡቲ ውስጥ እንደምታቋቁምና ዋና የማዘዣ ጽሕፈት ቤቱም በባሕር ዳር ከተማ እንደሚሆን መዘገቡ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን መልሳ የማደራጀት ፍላጎት እንዳለት በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በይፋ መነገሩ ደግሞ የሚወራውን ተናፋሽ መረጃ ዕውነታ እንዲኖረው ያስችላል ተብሏል::
በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር የሆኑት መሐመድ እድሪስ ፋራህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ጉዳዩን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኢል ኦማር ጊሌ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ጂቡቲ ውስጥ ማቋቋምን በሚመለከት ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን አመላክተው ፤ ነገር ግን “እስከ አሁን የተደረሰ ህጋዊ ስምምነት የለም” ሲሉ አስታውቀዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የባሕር ኃይልን ማቋቋምን በተመለከተ በሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ላይ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ብቻ ሳይሆኑ “የባሕር ኃይሉን በማቋቋሙ ሂደት ድጋፍ የምታደርገው ፈረንሳይም” እንደምትኖር ነው አምባሳደሩ ያመላከቱት።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየችበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ፤ የባሕር ኃይል ሳይኖራት ቆይታ ከቅርብ ዓመታት በኋላ መልሳ የማቋቋም ፍላጎት እንዳላት በተለያዩ አጋጣሚዎች ብትገልጽም ፤ ይህ የባሕር ኃይል መቀመጫውን የት እንደሚያደርግና በምን ሁኔታ እንደሚቋቋም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ኢትዮጵያ በፈረንሳይ ድጋፍ ለማቋቋም ያቀደችው የባሕር ኃይል መቀመጫውን በኤርትራዋ የምጽዋ ወደብ እንደሚሆን ‘ዠን አፍሪክ’ ለተሰኘው የፈረንሳይ መጽሔት መግለፃቸው ይታወቃል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ወቅት ኢትዮጵያ ለማቋቋም የምትፈልገውን የባሕር ኃይል ሠራዊት እውን ለማድረግ አገራቸው አስፈላጊን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረው ነበር። ኤርትራ ነጻነቷን እስካገኘችበት እስከ ግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በምጽዋና በአሰብ ወደቦች ላይ ትልቅ የባሕር ኃይል ነበራት።
በአዳማ ሁለት ፖሊስች በነዋሪዎች በዘግናኝ ሁኔታ ተቀጥቅጠው ተገደሉ
በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ “አዱላላ ቦኩ” በተሰኘውቀበሌ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲያዝ የተወሰነበት ተጠርጣሪን ለመያዝ የተሰማሩ ሁለት የፖሊስ አባላት መገደላቸው ተሰማ።
“ፖሊሶች ወደ ቀበሌው ሄደው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲሉ ለምን ይያዛሉ? በሚል ረብሻ ተነስቶ የአካባቢው ሰዎች በፖሊስ አባሎቻችን ላይ ይህን መሰሉን ጉዳት አድርሰዋል” ሲሉ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በአካባቢው ነዋሪዎች የተቃጣው ጥቃት የሁለት የፖሊስ አባላቶችን ህይወት ከመቅጠፉም በላይ አንድ ሲቪል ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ፣ በተጨማሪም ሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ደግሞ ጉዳት ማድረሱን የጠቆሙት ኮማንደሩ ፤ ረቡዕ ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ላይ በተፈጠረው ክስተት ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ የፖሊስ አባላት ሆስፒታል ተኝተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
በተጠቀሰው ቀን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አባላት ሃሰተኛ መስክርነት በመስጠት የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነበር ሕግ አስፈጻሚዎቹ ወደ አዱላላ ቦኩ ቀበሌ የተጓዙት።
“ከዚህ በፊት ሦስቱ ግለሰቦች ‘ሰው ገድሏል’ በማለት በሃሰት መሰከሩ። የክስ መዝገቡ ምረመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በድጋሚ ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ ግን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። የሰጡት ምስክርነት የሃሰት መሆኑ ሲታወቅ ፣ ፍርድ ቤቱ ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ። የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም ፖሊሶች ወደ ስፍራው ከተሰማሩ በኋላ ነው ይህ የሆነው” በማለት ክስተቱን ያስታወሱት አዛዥ ፤ ፖሊሶቹ ወደ ስፍራው ካቀኑ በኋላ ሦስቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋ ሲጥሩ ከአከባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ እንደደረሰባቸው እና በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ይፋ አድርገዋል።
ፖሊሶቹ በወቅቱ የጦር መሳሪያ ታጥቀው እንዳሉ ነው አሳዛኙና አሰቃቂው ጥቃት የተፈጸመባቸው። “የወጣንበት የራሳችን ማህብረሰብ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ተግባር በመፈጸሙ በጣም ነው ያሳዘነን” ያሉት ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ፤ በፖሊስ ባልደረቦቹ ላይ ለተፈጸመው ወንጀል እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ እንደሌለ አስታውሰው
በአሁኑ ሰዓት ወንጀሉ የተፈጸመበት አካባቢ ሰላም መሆኑን እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ ምረመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል::
የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ እየመከሩ ናቸው
የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ዙሪያ ምክክር እያደረገ ነው ተባለ። የምክክር መድረኩ “ሁሉም ለሰላም ዘብ ይቁም” በሚል መሪ ቃል ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።
ከዘጠኙም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና አባ ገዳዎች በምክክር መድረኩ ላይ እየተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል። መድረኩን የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመተባበር አዘጋጅተውታል።
በዛሬው ዕለት መካሄድ የጀመረው የምክክር መድረኩ በሃገር እና በሕዝቦች ሰላም ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሚካሄድ ሲሆን ፤ መድረኩ በቆይታው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሃገር ሽማግሌዎች ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለው ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ሰላምን ለማስፈን እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገልፀዋል።
የአዴፓ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ እንቅስቃሴ ዙሪያ በጥልቀት እየመከሩ ነው
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የክልል አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ህገ ደንብ ዙሪያ እየመከሩ ይገኛሉ። በውይይቱ ላይ በአማራ ክልል የሚገኙ የአዴፓ የዞን አመራሮችና የባህር ዳር ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተማ አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው።
የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፈ ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ በውህድ ፓርቲው ፕሮግራም፣ በመተዳደሪያ ህገ ደንቡና የድርጅቱ አወቃቀር፣ በንቅናቄው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን እቅድ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በፓርቲው ዙሪያ በሚነሱ የተለያዩ የግልጸኝነት ጥያቄዎች ዙሪያም ምክክር ተደርጓል።
ለውህድ ፓርቲው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት የተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ከህዳር 25 እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ፤ በዚህ መሰረትም የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን፣ የከተማና የገጠር ወጣትና ሴቶችን፣ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን፣ ምኹራንና የሲቪክ ማኅበራት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ይደረጋል። በድርጅቱ ላይ የሚነሱ ማናቸውንም ጥያቄዎችና ሀሳቦች ምላሽ በመስጠት ለድርጅቱ የሚጠቅሙ ምክረ ሀሳቦችን ማግኘት ይቻልበታል ተብሎ ተገምቷል።
28 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ኮኬይን በአዲስ አበባ ተያዘ
ከ28 ሚሊየን 386 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ እንደሚያወጣ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣው አደንዥ ዕፅ ትናንት በጉምሩክ ኢንተለጀንስ ሠራተኞች እንዲሁሜ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች አማካኝነት በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በዓለም ዐቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ነው በቁጥጥር ስር ውሏል።
ኖምዛሞ ግላዲየስ ቦዛ የተባለች የደቡብ አፍሪካ ዜጋ መነሻዋን ከደቡብ አፍሪካ በማድረግ ፤ መዳረሻዋን ወደ ህንድ ኒው ደልሂ በማድረግ 7 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ኮኬይን ስታዘዋውር ተይዛለች። በተጨማሪ አንቲቃ ሱሌይማን ቂዚ አባሶባ የተባለች የአዘርባጃን ዜጋ፤ ጠዋት ላይ ከሞስኮ አዲስ አበባ ገብታ ሆቴል አርፋ ፣ ተመልሳ ወደ ባንኮክ 4 ኪሎ ግራም ኮኬይን ይዛ ልትወጣ ስትል በቁጥጥር ስር መዋሏ ታውቋል።
በዚህ መሠረት በአንድ ቀን ግምታዊ ዋጋው ከ28 ሚሊየን 386 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ፤ በድምሩ 11 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ካደረገው መረጃ መረዳት ችለናል::
በኬንያ በኩል ከሃገር ሊወጣ የነበረ የአኩሪ አተርና የማሾ ምርት በፀጥታ ኃይሎች ተያዘ
ለውጥ የሚመስለው ለውጥ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በስፋት እየተካሄዱ ናቸው:: በተለይም የመሣሪያ እና የሃገር ውስጥና የውጭ ገንዘቦች ዝውውር በሃገሪቱ ውስጥ መንግሥትና ሕግ አስከባሪ ኃይል የለም እስኪባል ድረስ በመላ ሃገሪቱ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው በእጅጉ ስር መስደዱ ታውቋል::
የኢትዮጵያ ነገ የዜና ምንጮች እንደገለፁልን ከሆነ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በህገወጥ መንድ ወደ ኬንያ ሊወጣ የነበረ የአኩሪ አተርና ማሾ ምርት በሃገር ወዳዶች ጥቆማ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ህገ ወጥ ምርቱ የገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባካሄደው የህገ-ወጥ ንግድ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ነው ከሃገር ሊወጣ ሲል የተደረሰበት።
ለጊዜው ከየት እንደወጣና ወዴት ሊላክ እንደነበር ያልታወቀውና በኬንያ በኩል ለማውጣት የተምከረው 1 ሺህ 350 ኩንታል አኩሪ አተር እና 1 ሺህ 295 ኩንታል የማሾ ምርት በቁጥጥር ስር ውሎ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሽያጭ እንዲቀርብ መደረጉን ታማኝ ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል።
የፈረንሣይ ልማት ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሬሚይ ሪዮክስ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረግ ጀመሩ ። ዳይሬክተሩ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታም ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ተነግሯል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራሞች አተገባበር እና ሂደት ዙሪያ ምክክር ያደርጋሉ። በተጨማሪም ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር ሁለት ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙም ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል:: ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ወር ላይም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የ100 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጎ ነበር።
ከገንዘቡ ውስጥ 85 ሚሊየን ዩሮ በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ሲሆን፣ 15 ሚሊየን ዩሮው ደግሞ በዓለም ዐቀፍ የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮግራም በኩል የተደረገ ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተገልፆ ነበር።
ከነሕይወቷ የተቀበረችው ጨቅላ ሙሉ በሙሉ ማገገሟ ተሰማ
ከነ ሕይወቷ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ተቀብራ የተገኘችው ጨቅላ ሙሉ በሙሉ ማገገሟ ታወቀ። ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ጨቅላዋ ከእነ ህይወቷ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ተቀብራ ከተገኘች በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደችው። ጨቅላዋ ሆስፒታል ስትደርስ በደሟ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ባክቴሪያ በመኖሩ ህይወቷ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ እንደነበረ ሐኪሟ አስታውሰዋል።
የህጻናት ዶክተሩ ራቪ ካህና ጨቅላዋ በአሁኑ ሰዓት የክብደት መጠኗ እና አተነፋፈሷ መስተካከሉን አመላክተው ፤የወላጆቿ ማንነት እስካሁን እንዳልታወቀና የጤናዋ ሁኔታ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ሲደርስ ለማደጎ ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረዋል። አበሂናንዳን ሲንጋህ የተባሉ የፖሊስ ሓላፊ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ጨቅላዋ የተገኘችው አንድ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተወለደች የሞተች ሌላ ጨቅላን ለመቅበር እየቆፈሩ ሳሉ የህጻን የለቅሶ ድምጽ ከሰሙ በኋላ መህኑን ጠቁመው፤ ጨቅላዋ 90 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ መቀበሯንም አብራርተዋል።
ሐኪሞች ጨቅላዋ ግዜዋ ሳይደርስ በ30ኛው ሳምንት እንደተወለደች እና ወደ ሆስፒታል ስትመጣ 1.1 ኪ.ግ ብቻ እንደምትመዝን እና ከሁለት ሳምንታት የህክምና ክትትል በኋላ ጨቅላዋ በአሁኑ ሰዓት 2.7 ኪ.ግ እንደምትመዝን እና ፈሳሽ ነገር እየወሰደች እንደሆነም ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተዋል።
ጨቅላዋ በሸክላው ውስጥ ከሦስት እስከ አራት ለሚሆኑ ቀናት ተቀብራ ሳትቆይ እንዳልቀረች ሐኪሙ ዶ/ር ካሃን ግምታቸውን አስቀምጠው “ህጻናት ሲወለዱ በውስጣቸው ስብ ይዘው ነው። ይህም በአደጋ ግዜ ህይወታቸውን ለማቆየት ይረዳቸዋል” ብለዋል።
በአንጻሩ ሌሎች ባለሙያዎች ከዶ/ር ካሃን በተለየ መልኩ ጨቅላዋ በዛ ሁኔታ ውስጥ ተቀብራ የቆየችው ግፋ ቢል ከሶስት እስከ አራት ሰዓታት ብቻ ነው በማለት ይከራከራሉ:: ጨቅላዋ የተቀበረችበት ሸክላ ክፍተት ስለነበረው እና አፈሩ በኃይል ስላልተደለደለ አየር ይደርሳት ነበር ነው የተባለው።