የታሪክ ምንጣፍ – የወልወል ግጭት – ህዳር 26፣1927 ዓ.ም || አዲስ ዘይቤ

የታሪክ ምንጣፍ – የወልወል ግጭት – ህዳር 26፣1927 ዓ.ም || አዲስ ዘይቤ

ከአድዋ ድል ማግስት ኢትዮጲያ በአራቱም አቅጣጫ በቀኝ ገዢ ሃገራት ተከባ ነበር፤ በሰሜን እና በደቡብ-ምስራቅ በጣሊያን፣ በደቡብ እና በምዕራብ በእንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ በፈረንሳይ ቀኝ ገዢዎች ቀለበት ዉስጥ ወድቃ ነበር፡፡ አድዋ ድልን ተከትሎ ዳግማዊ ሚኒልክ የግዛት ማስፋፋትን ዓላማ ይኖራችዋል የሚል ከፍተኛ ሰጋት ዉስጥ የወደቁት ቀኝ ገዢዎች፣ ይህንኑ እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ በራሳቸዉ አነሳሺነት የድንበር ውል ስምምነት እንዲፈጸም አደረጉ:: ከእነዚህ የዉል ስምምነቶች ዉስጥ በ1900 ዓ.ም በኢትዮጲያ መንግስት እና በወቅቱ የጣሊያን-ሱማሌ ላንድ (የዛሬዋ ሶማሊያ) ቀኝ ገዢ በነበረችዉ ጣሊያን መካከል የተደረገዉ የዉል ስምምነት አንዱ ነበር፡፡ እነዚህ ከወቅቱ ቀኝ ገዚዎች ጋር የተደረጉ የደንበር ውል ስምምነቶች በአብዛኛዉ በመሬት ላይ ወርደው የማካለል ሰራዎች ስላልተከናወኑ እስከዛሬ ድረስ ለሚታዩ የድንበር ግጭቶች እንደዋና ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ::

በሌላ በኩል በአድዋ ጦርነት ከባድ ሽንፈት የገጠመው የጣሊያን መንግሥት ይህን ሽንፈቱን የሚያካክስበት እና ዝናውን እንደገና በዓለም መድረክ የሚያድስበት አጋጣሚ ሲጠባበቅ ኖሯል:: በተለይ እ.ኤ.አ በ1922 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጣዉ የቢኔቶ ሞሶሎኒ መንግሥት ይህን የሽንፈት ታሪክ የሚሽርበት ሰበብ ይፈልግ ነበር፡፡ ታዲያ ይህን የረዠም ጊዜ እቅድ እዉን ለማድረግ የምስራቅ ኢትዮጲያን ድንበር በመጣስ በሐረር ግዛት በኡጋዴን አዉራጃ በምትገኝ ወልወል የምትባል ቦታ በመያዝ የወረራ ደዉል አሰማ፡፡ ለሁለተኛው የጣሊያን ወረራ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በተለምዶ የወልወል ግጭት ተብሎ የሚጠራው የታሪክ ክስተት አንዱ ዋናው ሲሆን ይህ በኢትዮጲያ እና በኢጣሊያን መካከል የተደረገ ጦርነት ልክ የዛሬ 85 ዓመት ህዳር 26፣1927 ዓ.ም ነበር የተደረገርው:: ይህ ግጭት የጣሊያን መንግስት ኢትዮጲያን እንደገና ለመዉረር እና በአድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል የተጠቀማት የመረማመጃ ድልድይ እንደሆነም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ለዉልወል ግጭት መነሻ የሆነዉ የእንግሊዝ እና የኢትዮጲያ መንግሥታት ባደረጉት የድንበር ወል ስምምነት መሰረት ከሁለቱም ሀገራት የተወጣጡ ኮሚሽነሮች ስምምነቱን ወደተግባር ለማዉረድ ወደ አካባቢዉ ባቀኑ ወቅት ነበር፡፡ የኢትዮጲያ ተወካዮች ባካባቢዉ በደረሱ ወቅት የኢጣሊያን ወታደሮች ቀድመዉ በድንበር ዉል ስምምነት ከተቀመጠዉ የኢትጶጲያን ድንበር አልፈዉ የዉሃ ኩሬዎች በብዛት ወደሚገኝባት የበረሃዋ ገነት ወልወልን ተቆጣጥረዉ ጠበቋቸዉ፡፡ በሁኔታዉ ግር የተሰኙት የኮሚቴው አጃቢ ወታደሮች ወደፊት ለመሄድ ያደረጉት ጥረት በጣሊያን ወታደሮች በመከልከላቸዉ ለ14 ቀናት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተው በመጨረሻ ኅዳር 26፣1927 ወደ ጦርነት አምርተዋል፡፡ኮሚቴዉን አጅበዉ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ፊታዉራሪ አለማየሁ እና የኦጋዴን ተወላጁ ደጃዝማች ኡመር ሰመትር ይገኙበታል፡፡ በዉጊያዉም በኢትዮጲያ በኩል ፊትአዉራሪ አለማየሁን ጨምሮ 106 ሰዎች ሲሞቱ በጣሊያን በኩል 21 የሚሆኑ ወታደሮች ሞተዋል፡፡ የፋሲስት መንግስት መሪ የነበረዉ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ይህን ግጭት ምክንያት በማድረግ የረዥም ጊዜ እቅዱን እዉን ለማድረግ ኢትዮጲያ በሶስት አቅጣጫ ዳግም ወረራ ፈጸመ፡፡

ወልወል በምስራቅ ኢትዮጲያ፣ በሱማሌ ብሔራዊ ክልል ዶሎ ዞን የምትገኝ መንደር ነች፡፡

LEAVE A REPLY