ፍቅሬን በግልጥ፤ ባደባባይ
ደስታየን ፤በድንጋይ ሰሌዳ ላይ
መናዘዜ
ቅሬታየን በደብዛዛ ርሳስ
መከራየን በለሆሳስ
ጭንቄን በምስጢር መያዜ
ካዘናጋሽ
አንድ ቁምነገር ላውጋሽ!
ተከፍቼ
ግና ፊቴ ላይ፤ የብርሀን ዱቄት ነፍቼ
ምድር አትችለውን ችየ፤ ሆዴን ከጠረፍ አስፍቼ
ከሾህ አክሊሌ በላይ: ያበባ ዘውዴን ደፍቼ
በሸንጎ ጅንን ብየ ፤በእልፍኜ ብስለመለም
ህመምን አለማወጅ ፤አልታመምኩም ማለት አደለም፤