የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 28 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 28 ቀን 2011 ዓ.ም

የወያኔ ድራማ የሆነው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አሁንም መከበሩ እያነጋገረ ነው

የወያኔ መንግሥት ለመደለያነት ያስጀመረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለ14ኛ ጊዜ በለውጡ ቡድን ደጋሽነት በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ዜጎችን ጨፍልቆ የሃገሪቱን ሀብት በተደራጀ የማፍያ ቡድኑ ከመዝረፍ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አፍኖ የነበረው ሕወሓት መራሹ መንግሥት በተንኮል አባቱ ጸናሽነት ወልዶ ያሳደገው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዐልን ለይስሙላ በየክልሎቹ ስታዲየሞች እያስከበረ በምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲቀልድ መክረሙ አይዘነጋም::

በመለስ ዜናዊ ድርሰትና ዳይሬክቲንግ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ቀን ጨፍረው ሦስት መቶ ሥልሳ አራት ቀን በአምባገነኑ መንግሥት ሲቀጠቀጡና ሲገደሉበት የነበረው ድራማ ዛሬም መቀጠሉ ብዙ ትርጉም እየተሰጠው ይገኛል:: የለውጡ ቡድን ከኢህአዴግ ጉያ የወጣ በመሆኑ ፈጽሞ ይህንን በዓል ማስቀረት አይችልም የሚሉ ወገኖች የአሁኑ አከባበር (የሁለት ዓመቱ) ትክክለኛ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያስጠብቅ ነው በማለት ይከራከራሉ::

በሌላ በኩል የለውጡ ቡድን ይህንን የመደለያ በዓል ለአስራ አራተኛ ጊዜ ማክበሩ ስህተት ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ካነጋገራቸው ግለሰቦች መረዳት ችለናል:: የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ላይ በ27 ዓመት ውስጥ ከባድና ዘግናኝ የሰብኣዊ ጥቃት እየፈጸመ እንዲህ አይነቱን ሐሰተኛ በዓል ሲያከብር መኖሩን አስታውሰው በዓሉ ፈጽሞ በገሃድ ከሚታየው እውነታ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ መቅረት ባይችል እንኳ የአከባበር ቅርፁ ሊቀየር ይገባዋል ይላሉ::

እነዚህ በአዲስ አበባ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዮ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለይ አሁን ላይ በዓሉን ማክበር ወጥተው በሰላም መግባታቸውን በሚጠራጠሩ ዜጎች ላይ እንደመሳለቅ ይቆጠራል ነው የሚሉት:: ባለፉት አስራ ስምንት ወራት ህወሓት ለሥልጣኑ መደላደል ሲነሰንሰው የሰነበተው መርዝን መሠረት ያደረጉ ብሔር ተኮር ግጭቶችን ተከትሎ በየክልሉ ብዙ ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል::

ብሔር ተኮር ጥቃቶች ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ ሃይማኖታዊ አጀንዳዎችን ደርበው አሁን ድረስ በየቦታው የሰው ነፍስ እንደ ብጣሽ ወረቀት እየጠፋ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በሁሉም ክልልሎች በነጻነት የመኖር መብታቸው የተከበረ ይመስል ቀኑን በአደባባይ ማመስ ተገቢ አይደለም ሲሉ ለኢትዮጵያ ነገ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች የዶክተር ዐቢይ መንግሥት በቅድሚያ አሳሳቢውን መፈናቀልና ግድያ መቆጣጠር አለበት ብለዋል::

ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ በዓሉ ሲከበር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብአዲሳን ጨምሮ፥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች ታይተዋል።

በዕለቱም የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና አኗኗር የሚያሳዩ ትዕይንቶች በተወካዮቹ አማካኝነት ቀርበዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባደረጉት ንግግር ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር በጋራ መፍታት ይገባል ካሉ በኋላ ቀኑ የህዝቦችን ባህል፣ አኗኗርና እሴት ለማሳየትና አንድነታቸውን ለማጠናከር ያግዛል ሲሉ ተደምጠዋል::

የታከለ ኡማ መስተዳደር ለቀላል ባቡር ሥራ 5 ቢሊዮን ብር ለፌደራል መንግሥት አልከፍልም አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የቀላል ባቡሩ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ከአምስት ቢሊየን ብር በላይ የድጎማ ማካካሻ ክፍያ ለፌዴራል መንግሥት አልከፍልም ሲል ወሰነ።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በቀጣይ ለሚኖሩ ድጎማዎች የትራንስፖርት ቢሮ ጥናት ማቅረብ እንዳለበትም ውሳኔ አሳልፏል። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ እንደገለጹት፥ አስተዳደሩ ከዲዛይን እስከ አገልግሎት ዋጋ ትመና አለመሳተፉን አስታውሰው በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ቅሬታ ነበረው ሲሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ለነበረው ኪሳራ ድጎማ ለማድረግ የዋጋ ትመና ሲወጣ  ፤ “ያዋጣል አያዋጣም” ለሚለው ውይይት ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት የቢሮ ሐላፊ የኮርፖሬሽኑ ኪሳራ ትክክል ስለመሆኑ የማጥራት ሥራ እንዳልተሠራም አስረድተዋል። አዲስ አበባ ከተማ እንዲከፍል ሲደረግ በስምምነት ላይ ተደርሶ እንዳልሆነ እና የከተማ አስተዳደሩ መክፈል ያለበት ኮርፖሬሽኑ ለገጠመው ኪሳራ ሳይሆን የእያንዳንዱ ተሳፋሪ ሂሳብ ተሰልቶ ነው በማለት አካሄዱን ተችይተዋል።

የቀላል ባቡር ሥራ ከጀመረበት 2008 ዓ.ም እስክ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ያለውን ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ ማካካሻ ክፍያ ጥያቄ መቅረቡ አይዘነጋም። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ኪሳራ ስላለብን በዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንዲከፍል መጠየቁ ተገቢ እንዳልሆነ ነው ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ያስታወቁት።

የትራንስፖርት ቢሮ የኪሳራ ማካካሻ ድጋፍ የሚደረግበትን ሁኔታ አጥንቶ እንዲያቀርብ በተጠየቀው መሰረት የቀላል ባቡር አገልግሎት መሰጠት ከጀመረበት 2008 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ከድርጅቱ መረጃ በመውሰድ ጥናት ማድረጉ ተነግሯል። በጥናቱ መሰረትም በሦስት ዓመታት በድምሩ 265 ሚሊየን 524 ሺህ 261 ብር ከተሳፋሪዎች ገቢ ተሰብስቧል ነው የተባለው። በአንፃሩ 5 ቢሊየን 338 ሚሊየን 234 ሺህ 688 ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ፤ 5 ቢሊየን 72 ሚሊየን 710 ሺህ 427 ኪሳራ መድረሱንም ጥናቱ አሳይቷል።

ቢሮው ለካቢኔው በላከው ደብዳቤ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በፌዴራል መንግሥት ከተጠየቀው የሦስት ዓመታት 5 ቢሊየን 72 ሚሊየን 710 ሚሊየን 427 ብር የማካካሻ ድጎማ ውስጥ  ፣ 2 ቢሊየን 821 ሚሊየን 207 ሺህ 338 እንዲደጎም የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ቀሪው ገንዘብ ግን የግንባታ ወጪ ወለድ ምጣኔ በመሆኑ ይህም በአገልግሎት ሰጪው ድርጅት ምክንያት የደረሰ ኪሳራ አለመሆኑ ነው የተገለጸው።

ሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ ይህ ወጪ በፌዴራል መንግሥት የሚሸፈን መሆኑን በመገለፁ የከተማ አስተዳደሩ ቀሪውን ኪሰራ መክፈል እንደሌለበትም በደብዳቤው አብራርቶ የነበረ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ይፋ አድርጓል ። የከተማ አስተዳደሩ ከጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት ያለውን ውድቅ ከማድረጉ በተጨማሪ ከዚህ በኋላ ለሚደረገው የድጎማ ማካካሻም የትራንስፖርት ቢሮው ጥናት አድርጎ እንዲያቀርብ ከውሳኔ ላይ መድረሱን ተሰምቷል።

ሁሉም የአገሪቱ ዮንቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ተወሰነ

በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር መመለስ የሚቻለው ፣ ጥበቃዎቹን ማጠናከር ሲቻል መሆኑ በመታመኑና ተቋማቱ የፌደራል ተቋማት በመሆናቸው በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ከውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

“ከተማሪዎች ጋር በተደጋጋሚ በተደረገ ውይይት የቀረበው ቅሬታ የግቢው የጥበቃ አካላት ላይ መሆኑን በማንሳታቸው ፣ በተጨማሪም ተማሪዎች የፌደራል ፖሊስ በገለልተኝነት እያገለገሉን ነው” በማለታቸው እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ እና በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን የየዩኒቨርስቲዎቹ አስተዳደሮች በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አረጋግጠዋል። በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የፔዳጎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረው አዲ ዋቆ የሞተው በወልዲያ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ እንደሆነም ተነግሯል።

ጓደኞቹ እንደተናገሩት ከሆነ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት አዲናን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው የጥበቃ አካላት ድብደባ ደርሶባቸው እንደነበር ገልጸው  ፤ ከዚህ ድብደባ በኋላ አዲ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር። ትናንት የጎንደር ዩኒቨርስቲ በፌስቡክ ገፁ ማሾ ዑመር የተባለ የእንስሳት ህክምና ተማሪ ማታ ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ቢወሰድም ሊተርፍ አልቻለም ብሏል። ጉዳቱን በማድረስ የተጠረጠሩት ከሟቹ ዶርም ፊት ለፊት የሚገኙ ተማሪዎች ናቸው ያለው ዩኒቨርስቲው፣ ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የምርመራ ውጤቱም እንደ ተጠናቀቀ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።

በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ዛቻ እንደሚደርስባቸው፣ የማስፈራሪያ ወረቀቶችም እንደሚለጠፉ መረጃ እንዳላቸው ለቢቢሲ የገለፁት አቶ ደቻሳ ጉርሙ ፤ ለዚህም መፍትሔው የግቢዎቹ ጥበቃ እንዲጠናከር ማድረግ በመሆኑ በፌደራል ፖሊስ ይጠበቁ የመባሉን ምክንያት አብራርተዋል።

ተቋማቱን ወደ ሰላማዊ መማር ማስተማር ለመመለስ የዩኒቨርስቲዎቹ አስተዳደሮች የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ያሉት ሓላፊው ዩኒቨርስቲዎች የፌደራል ተቋማት ስለሆኑ ጥበቃዎቻቸውንና ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለማጠናከር “በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ እያመቻቸን ነው” ሲሉ ይፋ አድርገዋል። ጠንከር ያለ የጥበቃ ሁኔታ እንዲኖር ፤ በሚቀጥለው አንድ ሳምንት ውስጥ ፌደራል ፖሊስ ይገባል ተብሎም ይጠበቃል።

በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ባለው የደህንነት ሁኔታ፣ ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ለቅቀው የሄዱ ተማሪዎችን አስመልክቶ ከየክልሎቹ ጋር በመነጋገር፣ ትራንስፖርት አመቻችተው ለመመለስ ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሠሩም እንደሆነ አቶ ደቻሳ አብራርተዋል።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በአንጻራዊነት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አለ የሚሉት አቶ ደቻሳ፣ ክፍተት ሆኖ የሚታየው ለቅቀው የሄዱ ተማሪዎች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማካካሻ ትምህርት በመስጠት ያመለጣቸውን ለማስተማር ወደ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ስርዓት እንዲገቡ ከክልሎች ጋር እየሠሩም እንደሚገኙ አረጋግጠዋል::

ጌዲዮ በደቡብ ክልል ውስጥ መቆየት አልፈልግም አለች

የሲዳማ ክልልነት በሕዝበ ውሳኔነት መፅደቁን ተከትሎ፤ በደቡብ ክልል የተለያዩ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ተጠናክረው እየቀረቡ ናቸው::   የክልልነት ጥያቄዎቹ አዲስ ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም የተነሱና ምላሽ ሳያገኙ በመንከባለል ዛሬ ላይ የደረሱ ናቸው።

ከሁሉም ጥያቄዎች የሚለየው የጌዲዮ ዞን ጥያቄ እንደሆነ የሚገልፁት የአካባቢው ምሁራንና ተወላጆች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ዞኑ በደቡብ ክልል ውስጥ መቀጠል አይችልም ሲሉ ይተነትናሉ። የጌዲዮ ዞን በይፋ የክልል እንሁን ጥያቄውን ለዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው ሕዳር 11፣ 2011 ዓ.ም መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል።

የዞኑ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ የጥያቄውን ተገቢነት በማመን ቡድን አዋቅሮ ጉዳዩን አሳልፎ ሰጥቷል። ይህንን ቡድን የዞኑ ምክር ቤት ሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ እንዲያስተባብረው ተደርጎ፣ የብሔረሰቡ ተወላጅ ምሁራን ተካተውበት የጥያቄውን ተገቢነት መርምሮ እንዲያቀርብ ሥራ ተሰጥቶትም ነበር::

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የብሔረሰቦች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በጌዲዮ ዞን ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ውስጥ የባህል ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ታደሰ ፤ ከሕዳሩ ውሳኔ በኋላ ሚያዚያ ላይ በድጋሚ የዞኑ ምክር ቤት መሰብሰቡን አስታውሰው ሚያዚያ 16፣ 2011 ዓ.ም በተጠራው ጉባዔ የተሰጠው ሥራ ምን ደረሰ በማለት ጉዳዩን መልሶ መገምገሙን ተናግረዋል። ሆኖም በነበረው የአስፈጻሚው አካል ምክንያት ጉዳዩን ወደ ፊት መግፋት እንዳልተቻለ ቋሚ ኮሚቴው በወቅቱ ሪፖርቱን ማቅረቡን ያስታውሳሉ።

ሥራ አስፈጻሚው በድጋሚ ይህንን ውክልና ወስዶ እስከ ግንቦት 15፣ 2011 ዓ.ም ድረስ የሚሰራው ሥራ ሰርቶ፣ በአስቸኳይ ለክልል ምክር ቤት ጥያቄው እንዲቀርብ ወስኖ በስብሰባው ትዕዛዝ ማስተላለፉን እንዲሁም ፤ የዞኑ ምክር ቤት በክልል እንዲደራጅ፣ የራሱን አስተዳደር መመስረት እንዳለበት ውሳኔውን ቢያሳውቅም ይህ ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ ለክልሉ አለመቅረቡን አረጋግጠዋል። “ከደህዴን የሥራ አስፈጻሚ አካላት ባለው ግፊት የተነሳ የዞኑ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ይህንን ተልዕኮውን መወጣት አልቻለም” ይላሉ።

የጌዲዮ ሕዝብ በተደጋጋሚ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ለቢቢሲ የገለጹት በዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ታደሰ ኪጤ “ጥያቄው ግን ሲታፈን” መኖሩን ይናገራሉ። አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው ይህ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለዞኑ ምክር ቤት በይፋ መቅረብ የጀመረው በ2010 ዓ.ም ከዞኑ ውጪ በሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ላይ የደረሰው መፈናቀልና ሞት በክልሉ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ባለመቻሉ መሆኑን ይገልጻሉ። በወቅቱ በምክር ቤቱ አባላት ላይ “ስንበደል ቀጥታ የፌደራል መንግሥቱ አባል ብንሆን ኖሮ ጥያቄያችንን ያለ ስማ በለው በቀጥታ ማቅረብ እንችላለን” የሚል ስሜት እንደነበራቸውም አልሸሸጉም።

በ2010 ዓ.ም ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲዮ ማኅበረሰብ አባላት መፈናቀልና ያገኘው ትኩረት ማነስ ለጥያቄው ወደ ፊት መምጣት ሌላ ሰበብ መሆኑን ያብራራሉ። “መፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነት ሳይረጋገጥ፣ የተፈናቀሉት ለተራዘመ መከራ መጋለጣቸው ሌላው ምክንያት ነው” በማለት አቶ ጸጋዬ ይናገራሉ።

የጌዲዮ ሕዝብ  ባሌ የሚባል የራሱ የሆነ ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ነው። የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ያለው ሕዝብም ነው የሚሉ አሉ። ነገር ግን ሕዝቡ ከለመደው የአስተዳደር ሥርዓት ውጪ የሆነ ነገር ሲመጣበት ከምንሊክ መስፋፋት ጀምሮ እምቢተኝነቱን መግለፁን ምሁራኑ ይናገራሉ። የጌዲዮ ሕዝብ ባህላዊ የሆነ የመሬት ሥሪት፣ ደረባ የሚባል ፣ ያለው ሕዝብ ነው የሚሉት እነዚህ የጌዲዮ ተወላጆች፣ በ1880ዎቹ መጨረሻ የምንሊክ ጦር ወደ በስፍራው መስፋፋት የጌዲዮን የመሬት ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ነጥቋል በማለትም ይከራከራሉ።

የገበሬዎቹ አመጽ የተካሄደው ‘ምችሌ’ ላይ መሆኑን የሚጠቅሱት እነዚህ ግለሰቦች የምችሌ የአርሶ አደሮች አመጽ በጌዲዮ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ያብራራሉ። ፕሮፌሰር ታደሰ በበኩላቸው ከዚህ ጦርነት በኋላ የኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ከጌዲዮ አካባቢ ሕዝቦችን በማንሳት ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢ ማስፈሩን ይጠቁማል ።

በደርግ ጊዜ ቢሆንም ይላሉ ፕሮፌሰር፣ ከ1971 ዓ.ም እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ የነበረው አመጽ ዋና ምክንያት የራሱን ምርት ገበያ በሚወስንለት ዋጋ መሸጥ እንዲችል የጠየቀ፣ በራሴ ጉዳይ ራሴ ልወስን የሚል እንደነበረ ያብራራሉ። ይህ አመጽ ከይርጋ ጨፌ ራቅ ብላ በምትገኘው ‘ራጎ ቅሻ’ ላይ መካሄዱንም ያስታውሳሉ። ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በኢህአዴግ አስተዳደር ወቅት ቀጥሎ የፍትሀዊነት ተጠቃሚነት ጥያቄ፣ የእኩልነት የዲሞክራሲ ጥያቄ እስከዛሬ ድረስ መቀጠሉን ፕሮፌሰር ታደሰም ሆኑ አቶ ጸጋዬ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ታደሰ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያ ዓመታት፣ የጌዲዮ ሕዝብ ከሲዳማ እና ከምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ሕዝቦች ጋር በአንድነት ይኖር ነበር በማለት፣ በአካባቢው በተለይ በኦሮሚያ ጉጂ ዞንና በጌዲዮ መካከል በ1988 በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ የተወሰኑ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ እንዲጠቃለል መደረጉን ይገልጻሉ። በወቅቱ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊውን መንገድ መከተሉ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው በመጠቆም፣ በአባያ አካባቢ የሚኖሩ የጌዲቾ ማህበረሰብ፣ በወቅቱ ከጌዲዮ ጋር አንድ ወረዳ የነበሩ ቢሆንም ወደ ኦሮሚያ መካለላቸውን በማስረጃነት አቅርበዋል።

ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ በመሰረተው ክልል 8 ውስጥ የኮሬ ማኀበረሰብም ሆነ ቡርጂ ከጌዲዮ ጋር ነበሩ የሚሉት ፕሮፌሰር እነዚህም ወደ ኦሮሚያ መካለላቸውን አመላክተው ፤ ጎረቤታሞቹ በአሁን ሰአት ከጌዲዮ መራቃቸውን በመናገር እንደ ጌዲቾ ያሉ በባህልም በቋንቋ የሚዛመዱት ሕዝቦች ጋር የጌዲዮ ሕዝብ ተራርቋል ይላሉ።

ጌዲዮ በዞን ሲካለል ጌዲቼ፣ ኮሬ እንዲሁም በቡርጂ በኢህአዴግ አስተዳደር የመጀመሪያ አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት ከእኛ ጋር ነበሩ የሚሉት ፕሮፌሰር ታደሰ በአሁኑ ወቅት የጌዲዮ ዞን ከሲዳማና ከኦሮሚያ ጋር እንደሚዋሰን ከገለጹ በኋላበአሁኑ ወቅት በምስራቅና በምዕራብ ጉጂ የሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ተበታትነው የሚኖሩ ጌዲዮዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

የጌዲዮ ሕዝብ ፍላጎት ክልል የመሆን ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ታደሰም ሆኑ አቶ ጸጋዬ፣ ከኦሮሚያም ጋር ሆነ ከሲዳማ ክልል ጋር የመቀላቀል ፍላጎት እስካሁን ድረስ ከሕዝቡ አለመነሳቱን ይገልጻሉ። የጌዲዮ ሕዝብ ከሲዳማም ሆነ ከኦሮሚያ ሕዝቦች ጋር የኩሽ ሕዝቦች በመሆናቸው የሚጋሩት ነገር ቢኖርም የጌዲዮ ሕዝብ የራሱ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ማንነት እንዳለው አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።

ለዚህም በማስረጃነት የሚያነሱት በአጼ ምንሊክ ወደ ጌዲዮ አካባቢ ሲመጡ እንኳ ከኦሮሚያም ሆነ ከሲዳማም ሕዝብ ጋር አልነበርንም፤ ህዝቡ ራሱን ችሎ ይኖር እንደነበር በወቅቱ የነበሩ መረጃዎችን በማጣቀስ ያብራራሉ። ከአንድ ትንሽ ቦታ ከፍተኛ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርበው ጌዲዮ ብቻ ነው በማለት፣ ዞኑ ለፌደራል መንግሥቱም ሆነ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም እንዳለ ያብራራሉ። ኦሮሚያም ሆነ ሲዳማ ቡና ቢያቀርቡም ክልሎቹ ሰፊ ናቸው የሚሉት ፕሮፌሰር፣ ከትንሽ ስፍራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የጌዲዮ ዞን የክልልነት ጥያቄው ታፍኖ ከርሟል ይላሉ።

“የራሳችን ኢኮኖሚ አቅም አለን ፤ የራሳችን ሕዝብ ባህል ቋንቋ ታሪክ አለን ሲሉ” ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ ::ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር የጌዲዮ ሕዝብ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው የሚያደርገው ጥያቄና ትግል “ካድሬዎችና አንዳንድ አካላት ለማፈን የሚሞክሩ ቢኖሩም ሲዳማ ክልልነቱን በሕዝበ ውሳኔ ሲያረጋግጥ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ክልል መሆን ነበረብን” በማለትም መብታቸው መረገጡን አስረድተዋሌ።

በደቡብ ክልል በአሁኑ ሰዓት ከ50 በላይ ብሔሮች ቢኖሩም አሁን ሲዳማ ክልል ሲሆን በመልከ አምድሩ አቀማመጥ የተነሳ ከቀሪዎቹ የክልሉ ሕዝቦች ጋር መገናኘት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ ከደቡብ ጋር አንድ ክልል ብሎ ጌዲዮን መጥራት ፈታኝ እንደሆነ አመላክተዋል። አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው የጌዲዮ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄን ተገቢነት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል መመስረት ይችላሉ የሚለውን አንቀፅ በመጥቀስ “ሕገመንግሥቱን ካየን ሰጪና ከልካይ ያለበት አይደለም” በማለት በግልፅ ይከራከራሉ።

በቀጣዮ ወር የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል የተባለው ሐሰት ነው ተባለ

ዋሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ከሚታየው ነዳጅ ተኮር የሆኑ እንቅስቃሴዎች አኳያ የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ነው በሚል ተፈርቶ የነበረ ቢሆንም ፤ የታህሳስ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት የሚቀጥል መሆኑን የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።የአውሮፕላን ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው ጭማሪ ማሳየቱን ግን ሚኒስቴሩ ገልጿል ።

በመሆኑም የአውሮፕላን ነዳጅ በህዳር ወር ሲሸጥበት ከነበረው በሊትር 24 ብር ከ87 ሳንቲም ፣ በዓለም ወቅታዊ ዋጋ መሰረት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 3 ብር ከ37 ሳንቲም በጨመር በሊትር 28 ብር 24 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን አረጋግጠናል።

ሌሎች የነዳጅ ምርቶች ዋጋ  ግን በታህሳስ ወርም በነበረበት እንዲቀጥል የተወሰነ በመሆኑ ሰሞኑን በመዲናዋ አዲስ አበባ ሲናፈስ የነበረው ከረቡዕ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል የሚለው ወሬ ሐሰት እንደሆነ ኢትዮጵያ ነገ ማረጋገጥ ችሏል።

ይሁን እንጂ አዲስ ጭማሪ በቅርብ ጊዜ ሊኖር እንደማይችል የነገሩን የዜና ምንጮቻችን በዓለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ ማስተካከያ ሊደረግ የሚችልበት አጋጣሚ ሊከሰት የሚችልበት ዕድልመ መኖሩን ጠቁመውናል።

LEAVE A REPLY