የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 3 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 3 ቀን 2011 ዓ.ም

ዶ/ር ዐቢይ በአርሶ አደሮች ማሳ በመገኘት ሰብሎችን መሰብሰብ እያነጋገረ ነው 

የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በዛሬው ዕለት በአርሶ አደሮች ማሳ በመገኘት የደረሱ ሰብሎችን  ሲሰበስቡ ታይተዋል።  ሽልማታቸውን በተቀበሉ ዕለት ምሽት በከተማዋ የተተከሉ ችግኞችን ውሃ ሲያጠጡ ታይተው ነበር።

ዶክተር ዐቢይ ዛሬ የደረሱ ሰብሎችን ሲሰበስቡ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ የሚያጋጥመውን የእህል ብክነት ለመከላከል በትጋት መሥራት እንዳለባቸው መክረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሀገር ለመመገብና ከርሃብና ከተረጂነት ለመላቀቅ ከዘር እስከ መኸር ለሚተጉ የሀገሪቱ አርሶ አደሮች ምስጋና ማቅረባቸውን ዉሏቸውን ባሰፈሩበት ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ  ተመልክቷል።

በማህበራዊ ዘርፍ የሚያደርጉትን ይህንን አይነት በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች መልቀቅ ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ እና ለፖለቲካ ትርፍ የሚያደርጉት ተክለ ሰውነታቸውን ለመገንባት ለታይታ የሚያደርጉት ነው የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚሰጡ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዝቅ ብለው ከማህበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት የዚህ አይነት ተግባራት የሚመሩትን ሕዝብ ምን ያህል አብረውት መሆናቸውን የሚያሳይና ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብም ሆነ ለመላ የሃገሪቱ ዜጎች ሰርተው ለማሰራት ቆርጠው መነሳታቸውን ያመለክታል ሲሉ የሚከራከሩ መኖራቸው ተመልክቷል።

የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬ ውሎው በተለያዮ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ታህሳስ 4 ቀን ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል። የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይም ምክር ቤቱ እንደተወያየ ታውቋል ።

የመንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ረቂቅ አዋጅ ዋና ዓላማ የመንግሥት አካላት በመንግሥት ፕሮጀክቶች ውስጥ ያላቸውን ሓላፊነት በግልፅ በማመላከት ተጠያቂነትን እና ግልፀኝነትን በማስፈን የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ማጎልበት እንደሆነም ተገልጿል።

በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓት ባለመኖሩ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ወጪ እና ጥራት ባለመጠናቀቃቸው፣ የሀገሪቱን ውስን ሃብት ለከፍተኛ ብክነት እየዳረጉ ይገኛሉ ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ወጥ የሆነ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን በህግ ለመደንገግ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ልኳል።

በውጭ ሀገራት ስለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠትና የመፈፀም ስምምነትን ለማፅደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅንም ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ተመልክቷል::

በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ ማጽደቋ የውጭ ባለሃብቶችን ስጋት የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ የውል አፈጻጸሞችን ቀልጣፋ የሚያደርግ መሆኑም በሰብሰባው ታምኖበታል።

ወደ ሀገሪቱ የሚኖረው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የስምምነቱ መጽደቅ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ስምምነቱን ለማፅደቅ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ማቅረቡን ተከትሎ ምክር ቤቱም በረቂቆቹ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ አዟል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረቡትን የተለያዩ ስምምነቶች እና የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል። የኢትዮጵያ ማእድን፣ ነዳጅ እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

ረቂቅ ደንቡ በአሁኑ ወቅት ለማዕድንና ነዳጅ ሃብት መንግሥት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ በሂደት የታዩ ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባሮችን አካቶ እንዲሠራ እና አደረጃጀቱም ይህንኑ በሚያግዝ መልኩ እንዲደራጅ ለማድረግ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ማቅረቡ የተመለከተ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም ተወያይቶ ማስተካከያዎችን በማከል በሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

ባህርዳርን ያስዋባትን ዘንባባ ታሪክ የ95 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ተናገሩ  

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዋሴ አካሉ ከ50 ዓመት በላይ በዘለቀው የሥራ ህይወታቸው በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ  ያገለገሉ ሲሆን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከተማዋን በእጅጉ ያስዋባት ዘንባባ ከአስመራ ከተማ መጥቶ መተከሉን መስክረዋል።

“መሃንዲስ ክፍል፣ እሳት አደጋ፣ የመንግሥት ካዝና መጠበቅ የመሳሰሉትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን ሠርቻለሁ” የሚሉት አዛውንት፤ “እሳት ሲነሳ መኪና የብረት ቆብ እና የብረት ዝናር አለ አጥፍተን እንመለሳለን ማታ የለም ቀን የለም” በማለት የወጣትነት ዘመናቸውን ከማስታወሳችሁ ባሻገር፤ የባህር ዳር የጽዳት እና አትክልት ሓላፊ በመሆንም አንዳገለገሉም ገልጸዋል።

ባህር ዳር  ከተማ በውበቷ ገዝፋ የወጣችበትንና የምትታወቅበትን ዘንባባዎች ለመትከል እና ለመንከባከብ እድል ያገኙት ያገኙትም በጽዳት እና አትክልት ዘርፍ በሚሠሩበት ወቅት መሆኑን ይናገራሉ::

አራቱ በህይወት ባይኖሩም 10 ልጆች አፍርተው የነበሩት አቶ ዋሴ አሁን 95 ዓመትሞልቷቸዋል። ” አሁን ጡረታ ነኝ በ55 ዓመቴ ጡረታ ወጣሁ። ብዙ ነበርን አብረን የምንሠራው። ከእኔ ጋር እነ ሙሼ ጸጋ፣ አበበ አላምረው፣ እነ አዲስ ያየህ. . . ምንኑን እቆጥረዋለሁ። አሁን 10 አይሞሉም በህይወትያሉት። የጽዳት እና አትክልት ሓላፊ ነበርኩ። ፊታውራሪ ሐብተማርያም የባህር ዳር አስተዳዳሪ ነበሩ፣ መጥተው ባህር ዳርን ሲያስተዳድሩ የዘንባባ ችግኙን አስመጡ። “ያሉት አዛውንቱ የባህርዳር ነዋሪ ዘንባባው ከአስመራ ወደ ባህርዳር የመጣበትን ሂደት ሲያብራሩ፤ “በስምንት መኪና ነው ከአሥመራ የመጣው፤ በዚያ ወቅት 50 ሰው በስሬ አሠራ ነበር። ዘንባባው አጂፕ ከሚባለው የባህር ዳር ሰፈር እስከ ኳስ ሜዳ፣ ከኳስ ሜዳ እስከ ጢስ አባይ መንገድ ተተከለ” ይላሉ::

“ኋላ ሲደረጅ ከሥር ውሃ ይጠጣል፤ ማንም ቆሻሻ አይጥልበትም። በስር በስር እየሆነ ውሃ ይጠጣም ነበር። ሌላ ደግሞ በራሱ ቀዬ (መንደር) የሚያፈራ ይሄን ሁሉ በደንብ እይዝ ነበር። ዛሬ ከተማይቱ ከተመ ሆነች፤ ዘንባባዎቹ በ1949 ዓ.ም ከአስመራ ነው የመጡት። ዘንባባውን ያከፋፈልኩበት መዝገብ እስካሁን ድረስ አለ። በወቅቱ የዘንባባዎቹ መተከል ሰዉ እንግዳ ሆኖበት ነበር። አሁን ግን ይኸው የባህር ዳር ከተማ ጌጥ ለመሆን በቅቷል። እኔ ወጣ ብዬ ሳየው ደስ ይለኛል። በተለይ በክረምት ወቅት በጣም ደስ ነው የሚለኝ። እንግዳ ነገር ነው፤ በጣም የሚያስገርም ነው” ሲሉም የውቧ ባህርዳር መገለጫን ምንጭ አስረድተዋል::

“ከዛሬ 63 ዓመት በፊት ነው ዘንባባው እንደመጣ ወዲያውኑ ነበር መትከል የተመጀመረው። አስታውሳለሁ መትከል የተጀመረው ጥቅምት 01/1949 ዓ.ም ነበር። አብሬ በል እንደዚህ ትከል፤ እንደዚህ አድርግ ውሃ ስጥ እል ነበር። ውሃ የሚሰጥ በነጋታው ነው። ይሄን ሁሉ የተከታተልኩት እኔ ነኝ፤ የሚተክሉትን ሃምሳ ሰዎች በሙሉ እኔው ነበርኩ የማስተባብረው። በስር ስር ምግብ እየሰጠን ፤ አሁን ደግሞ ተረካቢዎች ጥሩ ይዘውታል።  ከዚህ እስከ ኳስ ሜዳ ሲያዩት ደስ ሲል። የሚያልፍ የሚያገድመው እንዳንጋጠጠ ነው። የሚመጣው ባለስልጣን ጋዜጠኛ ሁሉ አመስግኖ መርቋት [ባህር ዳርን] ይሄዳል።” ያሉት የ95 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ፤ “በዚያ ወቅት በህልምም በእውንም ይታየኛል። የማስበው ስለከተማዋ ጽዳት ነው፣ ለዚህ ሥራ የተሰጠን ምስክር ወረቀትም ነበረ፤ ሁሉ ነገር ሲያልፍ ይገርማል።” ሲሉ ትዝታቸውን አጋርተዋል::

ዶፒንግን ከሃገሪቱ ስፖርት ለማጥፋት ለፈርማሲ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ

ለፋረማሲ ባለሞያዎችና ባለቤቶች በፀረ-አበረታች ቅመሞች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል፤ ዶፒንግን ከመሰረቱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምርመራና ቁጥጥር ተዘርግቶ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተው፤ የተጀመረው  እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላትን በፀረ-አበረታች  ቅመሞች ዙሪያ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን  እንደታመነበት ገልጸዋል።

አበረታች ቅመሞች የሀገራችንን ስፖርት ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብ ጤና ጠንቅ ጭምር መሆኑን በማስታወስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን በጋራ ሊከላከሉትና ሊቀርፉት  እንደሚገባ ይገባልም ብለዋል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ  ላይ ከ150 በላይ  ባለሙያዎች  መሳተፋቸውን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ አጭር ቀሚስና የተቦዳደሱ ጂንስ ሱሪዎችን መልበስ ከለከለች

በኬንያ ናይሮቢ የምትገኝ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አማኝሴቶች አጫጭር ቀሚሶችን እየለበሳችሁ እየመጣችሁ ተቸግሪያለሁ ስትል ወቀሰች።

በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተነባቢ የሆነው የኬንያ ዴይሊ ኔሽን እንደዘገበው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ “ሴት ምዕመናን እባካችሁ አለባበሳችሁን ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ብታደርጉ” ስትል መማጸኗ ታውቋል።

“ቅዱስ ጴጥሮስ ክላቨር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን” ይህን መልዕክት ያስተላለፈችበት መንገድ ለብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑም እየተነገረ ነው።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን መልዕክት ለምእመናኑ ያስተላለፈችው የቤተ ክርስቲያኒቱ መግቢያ በር ላይ የሰሌዳ ማስታወቂያ በመስቀል ጭምር መሆኑን ያመላከተው ዜና፤ በማስታወቂያው ላይ ሴት ምዕመናን ሊለብሷቸው አይገባም ያለቻቸውን 10 ዓይነት አለባበሶችን በፎቶ ጭምር በማስደገፍ በዝርዝር ማስቀመጧን ገልጿል።

አጭሬ ቀሚስ (ሚኒስከርት)፣ ታፋው ላይ የተቦዳደሰ ጂንስ ሱሪ፣ “ቀይ ሰይጣን” የሚል ጽሑፍ ያለበት ቲሸርት፣ የተገላለጠ፣ ገላን የሚያሳይ ረዥም ቀሚስ ለአብነት ተጠቅሰዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን መመሪያ በሚተላፈሉት ላይ ምን እርምጃ እንደምትወስድ ግን እስካሁን ድረስ የገለጸችው ነገር የለም።

LEAVE A REPLY