አገራችን ሳተላይት በዚህ ሳምንት ታመጥቃለች || ቴዎድሮስ ዳኘ

አገራችን ሳተላይት በዚህ ሳምንት ታመጥቃለች || ቴዎድሮስ ዳኘ

አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር ሳተላይት ያመጠቀችው የዛሬ 60 ዓመት ነበር። በመጀመሪያዎቹ 13 ያህል ሙከራዎች የተሳኩትና መንኩራኩሩን ጠፈር ላይ ማሳረፍ የተቻለው 4 ጊዜ ብቻ ነው።

በናሳ አስተባባሪነት ኤስፕሎረር 1 የተሰኘው ሳተላይት ለመጀመሪያ ጊዜ ስትመጥቅ፣ ለአሜሪካኖች የረጅሙ የሃያልነት ጉዞ አንድ ርምጃ ነበር። ዛሬ ጠፈርን ተቆጣጥረውታል።

ያን ጊዜ፣ ጃንዋሪ 31/1958 ዓ.ም አሜሪካኖች የመጀመሪያዋን ሳተላይት ሲያመጥቁ፣ ድርጊቱ በሬዲዮና በቴሌቪዥኖች በመላው አገሪቱ በቀጥታ ነበር የተላለፈው። መጠኗ 30 ፓውንድ (15 ኪሎ አካባቢ) የምትመዝነው ይቺው ሳተላይት፣ ለአሜሪካኖች ክብር ነበረች። ለምን? ቴክኖሎጂ ያለውን ጥቅም በሚገባ ስለተረዱ።

ኢትዮጵያውም በታሪኳ የመጀመሪያዋን ሳተላይት በዚህ ሳምንት ታመጥቃለች። ይህ የአገራችንን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የሚወነጨፈው መንኩራኩር፣ ጉዞው ሊሳካም ላይሳካም ይችላል። ርምጃው ግን ትልቅ ነው።

ይህን ትልቅ ክንውን ልናደንቀው፣ ለልጆቻችን ልንነግር፣ ቀኑን ልንመዘግብ፣ ልንደሰትበት፣ ልንኮራበት ይገባል። አሜሪካኖች 15 ጊዜ ሞክረው የተሳካላቸው በአራቱ ብቻ ነው። እንዲያውም የመጀመሪያዎቹ መጠቃዎች አልተሳኩም። ያ ግን ተስፋ አላስቆረጣቸውም። ተስፋ መቁረጥ ደግሞ መሞት ማለት ነው። ሰው በህይወት እያለ እንደ ሞተ መሆን የለበትም።

ጥቂት፣ ኢትዮጵያ ተሻሻለች፣ አደገች ሲባል የሚያማቸው ሰዎች ካሁኑ ማጣጣል ጀምረዋል። ኢትዮጵያ እየኖሩ የኢትዮጵያ ስኬት ለምን እንደሚያማቸው ለማወቅ የሳይካትሪስት ምርመራ ያስፈልጋቸው ይሆናል። አንዱ ችግር “እኛ ያልጋገርነው ይረር” ነው። ሌላው ችግር “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው” .፣ ሁለቱም ደግሞ ከታመመ ጭንቅላት ብቻ የሚመጡ የበሽታ ምልክቶች ናቸው።

አገራችን ሳተላይት በዚህ ሳምንት ታመጥቃለች። ጉዞው ቢሳካም ባይሳካም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ እንደሰታለን። የተሳካ እንዲሆን ደግሞ እንመኛለን። የፊታችን ዓርብ የሚደረገው በታሪካችን የመጀመሪያው የሳተላይት መጠቃ ፣ ለአገራችን አንድ አሻራ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም በነጻነት፣ በሰላም፣ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በብልጽግና ትኑር።

LEAVE A REPLY