የኢትዮጵያ ሰብዓዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጉብኝት በጅግጅጋ ከተማ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጉብኝት በጅግጅጋ ከተማ

|| ጋዜጣዊ መግለጫ ||

ታህሳስ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በሶማሌ ክልል መስተዳድር ያለው ተነሳሽነት እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን በጅግጅጋ ከተማ የሥራ ጉብኝት የአደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል፡፡

በጉብኝታቸው ከክልሉ መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ከመወያየታቸው በተጨማሪ እስር ቤቶችንና ታሳሪዎችን ጐብኝተዋል፤ እንዲሁም የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዲስ በማሰራት ላይ ያለውን ማረሚያ ቤትም ጐብኝተዋል፡፡ ይኸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው አዲስ ማረሚያ ቤት በተለይ እጅግ ለተጨናነቀው በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ለሚገኘው ፋፈን ማረሚያ ቤት መጣበብ መፍትሔ የሚሰጥና ለታራሚዎች ጤናማ እና ሰብዓዊ አያያዝ የሚረዳ ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡

በጅግጅጋ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ጽ/ቤት ሥር የሚገኘው በተለምዶ ሀቫና በመባል የሚጠራው እስር ቤት የንፅሕና ደረጃ እና የእስረኞች አያያዝ ሊሻሻል ስለሚገባበት ሁኔታ ከኃላፊዎቹ ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷል፤ ኮሚሽኑም አፈጻጸሙን በቅርበት ይከታተላል፡፡

የተወሰኑ ታሳሪዎች በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹትና ለኮሚሽኑም ከቀረቡ አቤቱታዎች በፖሊስ አካላዊ ጥቃትና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንደተፈጸመባቸው ያሳወቁ በመሆኑ ኮሚሽኑ ስልታዊ ክትትሉን የሚቀጥል ሲሆን እስከ አሁን በተገኘው መረጃ መሰረት አልፎ አልፎ የሚከሰት ሃይል የመጠቀም እና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ሊኖር እንደሚችል ከመጠቆም ያለፈ ስልታዊ የሆነ ወይም የተስፋፋ የፖሊስ ድብደባ እየተፈጸመ ነው የሚያሰኝ አይደለም፡፡

ነገር ግን አዲስ መብራቱ የተባለ ወጣት ተማሪ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኃላ ተፈጽሞበታል በተባለው ድብደባ በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል ገብቶ ሕይወቱ ማለፉ የተገለጸ መሆኑ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ክስተት በመሆኑ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በዝርዝር በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡

እንዲሁም ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሕክምና እና መልሶ መጠገን በተመለከተ፣ ከጐረቤት ክልሎች የተፈናቀሉ ሰዎችን መብት አጠባባቅ በተመለከተ፣ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ለረጅም ዓመታት ከኖሩበት የመንግስት ቤቶች ተገድደው የመልቀቅ ችግሮች የገጠማቸውን ሰዎች መብት አጠባበቅ በተመለከተ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ኮሚሽኑ ከመስተዳድሩ ጋር ስለ መፍትሔ አቅጣጫዎች በመወያየት አበረታች ምላሽ የተገኘ ሲሆን አፈጻጸሙንም በቅርበት ይከታተላል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት መሠረት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሰለባ ለነበሩ ሴቶች የክልሉ መስተዳድር የአደረገው የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ የሚመሰገን እርምጃ ሲሆን ለቀሪዎቹም ሰለባዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሰጡት ቃል የሚያበረታታ ነው፡፡

«በተለይ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ዑመር ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት እንዲሁም የጥሰት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መጠገን እና መልሶ መቋቋም የአለቸው በተግባር የሚታይ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት እጅግ የሚያበረታታ እና ለሌሎች የፌዴራል እና የክልል መንግስት ባለሥልጣኖች በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው» በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ የሚታየውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ለማሻሻል አስፈላጊ ከሆኑ እርምጃዎች ውስጥ የፍትሕ አስተዳደር እና የፀጥታ ጥበቃ አካላትን ብቃት መገንባት፣ ለዳኝነት አስተዳደር ልዩ ትኩረት በመስጠት በሙያዊ ብቃት እና ሥነ ምግባር ላይ የተመሰረተ አቅም ማጐልበት፣ የግንዛቤ ማስፋፋት እና ተጐጂዎችን መልሶ መጠገን እና ማቋቋም ይጨምራል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከክልሉ መስተዳድር ለተደረገለት ድጋፍ እና መልካም የሥራ ግንኙነት ምስጋናውን እየገለጸ ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ሁሉ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር አብሮ እንደሚሰራ እና የክትትል ስራውን የሚቀጥል መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

LEAVE A REPLY