አጭር ማሳሰቢያና አጭር ትውስታ || በእውቀቱ ስዩም

አጭር ማሳሰቢያና አጭር ትውስታ || በእውቀቱ ስዩም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ ቆንጆ ቆንጆ ቃለመጠይቅ አድራጊ ጋዜጠኛ ሴቶች በየሜዳው ማለቴ በየሚድያው ተበራክተዋል !!” It is a trap! “ጎበዝ ተጠንቀቁ ይህ ነገር ለኛ ነው” ብሏል አዝማሪ ወርቄ!!

በቆንጆ ሴት ተጠይቀህ ስለሀገርና ስለፓርቲ ስትቀድ ሳታስበው ልታሰምጣት መፍጨርጨርህ አይቀርም! አንበሳው! ጀግናው! አይበገሬው! መባል ውስጥ ውስጡን ሊያምርህ ይችላል፤ እና ሳታውቀው፤ ክልልን ከክልል፤ ዞንን ከዞን፤ ዝሆንን፤ ከዝሆን የሚያጋጭ ጦሰኛ ቃል ሊያመልጥህ ይችላል!! ስለዚህ አንድ ነገር ከመናገርህ በፊት “ይህ ሀሳቤ ከጭንቅላቴ ነው ወይስ ከቃጭሌ ነው የመነጨው?” ብለህ ራስህን ጠይቅ!

ጥንታዊ ሴቶች ተዋጊ ወንድ ይወዱ ነበር ፤ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ በጊዜው የኑሮ ውጣውረድ በትጥቅ ትግል የታጀበ ነበር፤ ሴቶች በጀግንነት ከወንዶች አንሰው ባያውቁም እንደ እርግዝና አይነት የተፈጥሮ ፀጋዎችም (ወይም እዳዎች) የወንዱን ያህል እንዳይዋጉ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል:: ይህንን ሁኔታ ተዋጊ ወንድ በማጨት ያካክሱታል፤ ጥንታዊት ሴት፤ አድኖ ወይም ቀምቶ ያሳድረኛል፤ ወይም ጩጩዎቼን ከነጣቂ ይታደግልኛል ብላ የምታስበውን ጉልቤ ወንድ ብታፈቅር አይገርምም፤ እና ያኔ ወንዶች ሴቶችን እሚጀነጅኑት ሊፈፅሙት ስለተዘጋጁት ጀብድ በመፎከር ነበር፤

አሁን ዐለም በብዙ መንገድ ቢቀየርም ጂናችን አልተቀየረም፤ ሴቶችን ለማማለል አለመጠን መጎረር፤ መፎከር፤ ልናደርገው ከምንችለው በላይ ቃል መግባት፤ አመላችንም ዘረመላችንም ሆኖ ቀጥሏል፤ እና ይሄን ስለማውቅ አንድ ፖቲከኛ ባንዲት ቆንጆ ሴት ቃለ መጠይቅ ሲደረግ ባየሁ ቁጥር “ እሱ ይሁነን እንግዲህ “ እያልሁ እማልዳለሁ፤

ከላይ ያቀረብኩ እውቀት ከመከራ የተማርኩት ነው፤

በልጅነቴ የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቅሴ አይመቸኝም ነበር:: ለነገሩ የሰውነት ማጎልመሻ ውስጥ ልትገባ የምትችለው ሊጎለምስ የሚችል ሰውነት ሲኖርህ ነው:: ርሳስን ጠርበህ ምሶሶ አታረገውም!! እኩያዎቼ፤ ሩጫ፤ ትግል አክሮባት፤ ሲወዳደሩ እኔ ጉቶ ላይ ቁጭ ብየ በዳኝነት እና በተመልካችነት እንዳገለግል ተፈርዶብኛል፤

አንድ ቀን እኩዮቼ “ ጦጥማ” በተባለው ሰፊ ሜዳ ላይ አክሮባት ይሰራሉ:: ሜዳው ጠርዝ ላይ ፤ ያገልግሎት ዘመኑን የጨረሰ የሎንቺና ጎማ ተጋድሟል:: አንዱ ልጅ እየተንደረደረ ይመጣና በሁለት እግሮቹ ጎማው ፊት ላይ ነጥሮ አየር ላይ ተገለባብጦ እንደ መሬት ላይ ወርዶ እንደ ዘንግ ቀጥ ይላል! ግራና ቀኝ የተኮለኮለው ትመልካች ጭብጨባና ፉጩቱን ያወርድለታል !!

ከሰፈራችን ሴቶች ጋር ተቀላቅየ፤ ይሄንን ትይንት እያየሁ ሳጨበጭብ፤ እንኮየ የተባለች የሰፈራችን ቆንጅየ ልጅ “አንተ አትሞክርም እንዴ?” አለችኝ::

ለምን አልሞክርም የኔ ቀንበጥ? አንች ብለሽኝ!!

ከሜዳው ጫፍ አንስቼ እየተንደረደርሁ መጣሁ:: የተንደረደርኩበትን ርቀት አሁን ሳስበው፤ አክሮባቱን ትቼ፤ አገር አቋራጭ ምናምን ብሞክር ይሻለኝ ነበር! ሮጥ ሮጥ ሮጥ ሮጥ..ጎማው ላይ ልደርስ አንድ ሁለት ርምጃ ሲቀረኝ በውሳኔየ ክፉኛ ተፀፀትሁ:: ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ፀሎት፤ ፀፀት ይዞ አክሮባት አይመከርም!! ጭራሮ የመሰለ እግሬ የጎማውን ጉንጭ ስቶ አፉ ውስጥ ገባ!! ጏደኞቼ ጎማው ላይ ይነጥሩ ነበር:: የኔ ጊዜ ሲሆን፤ ጎማው እኔ ላይ ነጠረ!! ጎማው ከሎንቺናው ተገንጥሎ እየኖረም አመሉን እንደማይረሳ አሳየኝ፤

የድንበርየለሹ የሀኪሞች ማህበር አባላት በቃሬዛ ተሸክመው ከሜዳው ሲያወጡኝ ላጭር ጊዜ በሁሉም አቅጣጫ መተንፈስ አቁሜ ነበር፤ አለመሞቴን የተረዳሁት የተመልካቾችን የሁካታ ሳቅ ስሰማ ነው:: ከሁካታው መሀል ዘለግ ብሎ የሚሰማው ደግሞ የእንኮየ ሳቅ ነበር!

LEAVE A REPLY