የግብጽ ፕ/ት አል ሲሲ ለጠ/ሚር አብይ የፓርላማ ንግግር ምላሽ መስጠታቸው ተነገረ
“በአባይ ግድብ ግንባታ ጦርነት መፍትኄ አይደለም” ፕ/ት አል ሲሲ
የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታ አል-ሲሲ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ላለው ግድብ አለመግባባት ቢኖርም ጦርነት መፍትሄ አይሆንም ሲሉ ገለፁ።
ፕሬዝዳንቱ በግብጿ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው ሻርመ ኤል ሼህ ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በግድቡ ዙሪያ በቀጣይ ወር የአሜሪካ ተወካዮች በሚገኙበት በዋሽንግተኑ ስብሰባ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ነው ትኩረት መሰጠት ያለበት ሲሉ ተናግረዋል።
“ያሉን ውስን ሃብቶች በጦርነት እና በግጭት መባከን የለባቸውም፤ ህዝቡን እና ሃገራችንን ለማልማት ልንጠቀምበት ይገባል፣ ጦርነት መልስ አይሆንም” የሚለው የአል-ሲሲ ንግግር፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፓርላማ ላይ ለተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተያየት ምላሽ ይመስላል እየተባለ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 11 ቀን 2012ዓ. ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ “የማንንም ፍላጎት ለመጉዳት የጀመርነው ፕሮጀክት አይደለም” ከማለታቸው በተጨማሪ፤ “ቁጭ ብለን እናወራለን፤ ማንም ይህንን ግንባታ ማስቆም አይችልም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
በወቅቱ ከግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሰነዘሩ የጦርነት እንከፍታለን መልዕክቶችን አስመልክተው ሲናገሩም፤ ” ጦርነት ማንንም አይጠቅምም ብለን እናምናለን፣ ጦርነትም ከሆነ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ አላት፤ በሚሊዮን ማሰለፍ እንችላለን” ማለታቸውም የሚታወስ ነው።
ዛሬ በሻርም ኤል ሼክ ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት የግብፁ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ዋናው ነገር በመጪው ወር በአሜሪካ ዋሽንግተን በሚደረገው ንግግር ዘላቂ መፍትሄ ላይ መድረስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“ስለ ራሳችን ኃያልነት ብዙ ማለት አንፈልግም። ግን ሚሊዮኖችን ትመለምላለህ ወይስ ግድብ ትገነባለህ?” ሲሉ የጠየቁት አል ሲሲ፤ “ሚሊዮኖችን በሚቀጥፍ ግጭትና ጦርነት ሃብታችን ሊፈስ አይገባውም። ይልቁንም ያን ገንዘብ ለህዝብና ለአገር ልማት እናውላለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ አሞላል ሂደትን በተመለከተ ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይቶች ውጤት አልባ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው
የሕወሓት ቁልፍ ሰው የነበሩት ቴዎድሮስ አድሃኖምና ምክትል ጠ/ሚትር ደመቀ መኮንን ጄኔቭ ላይ ተወያዮ
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያን ቀደም ሲል በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት እንዲሁም በአምባገነኑ ሕወሓት ውስጥ ቁልፍ ቦታ የነበራቸው ቴዎድሮስ አድሃኖምና የለውጡ ቡድን ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው የሚነገርላቸው ደመቀ መኮንን ጄኔቫ በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት ነው ተገናኝተው የተወያዮት።
በውይይቱ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን፣ በቅድመ ጤና አጠባበቅ፣ በተመጣጠነ ምግብ፣ በህክምና መሳሪያዎች እና ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዙሪያ መነጋገራቸው ታውቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ልማት ለሚጫወተው አጋዥ ሚና አድናቆታቸውን በመግለፅ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው፤ የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክር ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ፓርላማው በዛሬ ውሎው የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ታክስ እንዲጨመረ ወሰነ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንቨስትመንትና የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባውም የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅን እና የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ልኳል:: የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንዲሁም የሀገሪቱን የተፈጥሮ፣ የባህል እና ሌሎች ሀብቶችን ጥቅም ላይ ማዋልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት ለማስቻል የተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል።
የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ በዚህ መልኩ መሻሻሉ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ጠቃሚ ነው ካሉ በኋላ ረቂቅ አዋጁ ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጋጩ ነገሮች እንዳይኖሩት ቋሚ ኮሚቴው በጥልቀት ቢያየው የሚል ሀሳብም አቅርበዋል። በኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ ባለሀብቶች በሚያለሙበት ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ላይ መሥራት እንደላባቸው የሚደነግግ አንቀጽ ቢካተት መልካም ነው ማለታቸውንም ታዝበናል።
የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ደምጽ መርቷል። ምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ስለማዛወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ላይም ምክክር አድርጓል።
የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ፤ የአዋጁ ዋና ዓላማ የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ማጎልበትና የካፒታል አቅርቦትን እንዲሁም የመንግሥት የፋይናንስ አቅርቦትን ለማጎልበት ነው ካሉ በኋላ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ ከ20 ዓመታት በላይ በማስቆጠሩ የህግ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በመቀጠልም ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ፤ ረቂቅ አዋጁ መንግስት ተገቢውን ታክስ መሰብሰብ እንዲችል የሚያግዝ፣ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ አስተዋፅኦ የሚያደረግ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤና በሚጎዱ እና የማኀበራዊ ችግር በሚያስከትሉ በተጨማሪም መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ታክስ መጣል በማስፈለጉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኤክሳይዝ ታክሱ በትክክል የቅንጦት እቃ ተብለው በተለዩ፣ በኅብረተሰብ ጤና እና በአካባቢ ደህንነት ላይ ችግር የሚያስከትሉ የነዳጅ ምርቶች፣ ተሽከርካሪዎችና የፕላስቲክ እቃዎች የሚጣል መሆኑንም አስረድተዋል። የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ መሰረት ዝቅተኛው እስከ 10 በመቶ ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ እስከ 500 በመቶ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህም መሰረት 10 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ከሚጣልባቸው ውስጥ የፎቶ ግራፍ እና የቪዲዮ ካሜራዎች፣ የቲቪ መቀበያ እና መሰል የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይገኙበታል። ከ400 እስከ 500 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ከሚጣልባቸው ውስጥ በአብዛኛው በአውሮፓውያኑ ከ2012 በፊት ማለትም 7 ዓመትና ከዚያ በላይ በሆናቸው ተሽከርካሪዎች መሆናቸውም ተነግሯል።
የትራክተር ምርቶችም እንደ አገልግሎት ዘመናቸው ማለትም 4 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆናቸው ላይ ከ100 እስከ 400 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣል መሆኑም በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል። በሀገር ውስጥ ተገጣጥመው ለገበያ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ደግሞ 30 በመቶ መሆኑም ተደንግጓል።
ረቂቅ አዋጁ የአልኮል መጠጦች፣ የትምባሆ ምርቶች፣ ጣፋጭና ጨዋማ ምግቦች፣ ስባማ ምግቦች ላይ እንዲሁም የተሰፉ ልብሶች ላይ የታሸጉ እና ጋዝ ያላቸው ውሃዎች ላይ ታክስ እንዲጣል የሚያዝ መሆኑም ታውቋል።
የምክር ቤቱ አባላት ከታክሱ ዓላማ አንጻር እንደ ስኳር፣ ዘይት እና ጨው ላይ ታክስ መጣሉ ከዝህብ ጥቅም ጋር እንዳይጋጭ መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የግብርና መሳሪያ የሆኑ ትራክተሮች ላይ ከአገልግሎት ዘመናቸው አንጻር ጉዳት ቢያደርሱም እንኳ ምርቶቺ ሊበረታቱ ሲገባ ታክስ መጣሉ አግባብነት አንደሌለውም አንስተዋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ በነበረው መደበኛ ስብሰባው የኤክሳይዝ ረቂቅ አዋጅ ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦ እቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት ለሚገኙ ዜጎች ለመደጎም እንደሚያስቸል አምኖበታል። በመጨረሻም የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ታውቋል::
ኢትዮጵያ 90 ሺኅ ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራች ነው ተባለ
የዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ እና ምላሽ የስደተኞችን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ትርጉም ባለው ደረጃ ሊያጎለብት እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ። “ዓለምአቀፍ የስደተኞች ፎረም” ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስደተኞች የሚደረገው ድጋፍ እና ምላሽ ትርጉም አዘል መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ለስደተኞች የምትሰጠው ድጋፍ እና ምላሽ ዓለምአቀፍ የስደተኞች ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የተሻለ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችሏት የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነች እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡
በመሠረታዊ አገልግሎት እና በማኀበራዊ ደህንነት ጥበቃ፣ በአቅም ግንባታ፣ በክህሎት ስልጠና እና በኢኮኖሚ ትስስር ዙሪያ ኢትዮጵያ በተግባር የሚቆጠሩ ድጋፎችን ለስደተኞች ለመስጠት መዘጋጀቷን ይፋ ማድረጋቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
በዚህም ለ90 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እና ስደተኞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር፣ እንዲሁም ለ20 ሺህ ስደተኞች እና ኢትዮጵያዊያን ጥራት እና ተቀባይነት ያለው የክህሎት ስልጠና ለመስጠት ታቅዷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘላቂነትነት ያለው እና ገበያ ተኮር የሆነ የኃይል አቅርቦት መፍትሄን ስደተኞችን ጨምሮ ለ3 ሚሊየን ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ መተቃዱንም አስታውቀዋል፡፡
ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላንን ማምረት አቁሚያለሁ አለ
ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ለጊዜው የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርቱን ሊያቋርጥ መሆኑን ይፋ አደረገ። በዘጠኝ ወራት ባጋጠሙት ሁለት የመከስከስ አደጋዎች አውሮፕላኑ ከበረራ ታግዶ የቆየ ቢሆንም የማምረት አገልግሎቱን ግን ሳያቋርጥ መቆየቱ ይታወሳል።
አውሮፕላኑ በኢትዮጵያና በኢንዶኔዢያ በገጠመው የመከስከስ አደጋ ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ቦይንግ አውሮፕላኑ ተመልሶ በዚህ ዓመት መጨረሻ እንዲበር አደርጋለሁ የሚል ግምት የነበረው ቢሆንም፣ የአሜሪካ አቪየሽን ተቆጣጣሪ ግን አውሮፕላኑ እንዲህ በፍጥነት ተመልሶ አየር ላይ እንዲወጣ ፈቃድ እንደማይሰጠው ገልጿል።
መቀመጫውን በሲያትል ከተማ ያደረገው ቦይንግ፣ በአሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ምርቱን ወደ ውጪ የሚልክ ኩባንያ ሆኖ ለዓመታት መዝለቅ ችሏል::
ኩባንያው ጉዳዮን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከ737 ማክስ ጋር ተያይዞ ሠራተኞችን እንደማይቀንስ ገልጾ፣ ነገር ግን ምርት ማቆሙ የዕቃ አቅራቢ ድርጅቶችንም ሆነ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲል አስረድቷል።
የአውሮፕላኑ አምራች “737 ማክስ ደህንነቱ የተረጋገጠ ሆኖ ወደ በረራ እንዲመለስ ማድረግ ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ተርታ ነው” ከማለቱም ባሻገር፤ ” 737 ማክስ ዳግም ወደ በረራ እንዲገባ ለማድረግ የሚሰጠው ፈቃድ፣ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎች፣ ጠንካራ መሆናቸውን እንዲሁም ተቆጣጣሪ አካላት፣ ደንበኞቻችን እና መንገደኞች ዳግም በ737 ማክስ ላይ ያላቸው እምነት መመለስ እንዳለበት እናምናለን” ሲል የሚጠበቅበትን ከባድ የቤት ሥራ አመላክቷል::
ባለፈው ሳምንት አሜሪካው የአቪየሽን ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት አውሮፕላኑ በኢንዶኔዢያ ከተከሰከሰ በኋላ ተጨማሪ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ያውቅ እንደነበር ምክር ቤት ተገኝቶ ቃሉን ሰጥቷል።
የፌደራሉ አቪየሽን ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ዲዛይኑ ላይ ለውጥ እስካልተደረገለት ድረስ በርካታ የአውሮፕላን አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተናግረው እንደነበርም ያመላክታል። ይህ ሁሉ ሆኖ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን እስኪከሰከስ ድረስ አውሮፕላኑ ከበረራ ሳይታገድ ቆይቷል።
ቦይንግ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት ነው የተባለውን የአውሮፕላኑን ሥርዓት ዳግመኛ ዲዛይን እያደረገው ነው።
737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ በመታገዱ ብቻ 9 ቢሊየን ዶላር ያስወጣው ሲሆን የአክሲዮን ድርሻው በ4 በመቶ ቀንሶበታል:: ቦይንግ 400፣ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን አምርቶ ለደንበኞቹ ለማከፋፈል ተዘጋጅቶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቀማሉ።
የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የምክክርና የግምገማ መድረክ ተዘጋጀ
24ኛው የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ማጥፋት ፕሮግራም አፈጻጸም ዓመታዊ ግምገማ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። ከጤና ሚኒስቴር፣ ከጋምቤላ ክልል፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ አመራሮችና እና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው ኅብረተሰብ ተወካዮች በግምገማ መድረኩ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦሞድ ኡጁሉ፤ ባለፉት ዓመታት የጊኒ ዎርም በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር የተሠሩት ሥራዎች በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ትብብር ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። በቀጣይም በእርሻ ቦታዎችና በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ሠራተኞችና ማኀበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጊኒ ዎርም በሽታ በሰዎች ላይ አለመከሰቱን ጠቁመው ይህም ትልቅ የምስራች መሆኑን እና ስኬቱ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች እና ሥራው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ተቋማት ያላሰለሰ ጥረት መሆኑን አብራርተዋል።
የጊኒ ዎርም በሽታን በዘላቂነት ለማስወገድም ለበሽታው ተጋላጭ መንደሮች ላይ ድመቶችንና ውሾችን በማሰር ጥብቅ ክትትል ማድረግ ፣ ያቆሩ የውሃ ቦታዎችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ማከም እና የተቀናጀ አሠራርን ማዳበር እንደሚገባና እና ኅብረተሰቡም ተሳትፎውን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መክረዋል።
የጊኒ ዎርም ማጥፊያ ፕሮግራም የአራት ሀገሮች የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነ ብርሃን በግምገማ መድረኩ ላይ በሽታውን ከሀገራችን ለማጥፋት ለማኅበረሰቡ ንጹህ ውሃ እንዲቀርብ ማድረግ ወሳኝ መሆኑተናግረዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የግምገማ መድረክ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የቀጣይ የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ በጥልቀት ውይይት ይደረጋል።