ሰሞኑን ከምእራብ አውሮፓ፣ ጣሊያን፣ የወጣው ዘገባ እንደሚገልጸው በተመገብነው ቁጥር የፊታችን ጡንቻዎችን የሚያፍታታው እና ፈገግታችንም ከሚጨምረው ከቃሪያ እና ከበርበሬ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ለተለያዩ የልብ ህመሞች የመጠቃታቸው እድል በጣም ትንሽ ነው ብልውታል።
ላለፈው ስምንት አመት የቃሪያ እና የበርበሬ የምግብ ግብአትን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙ ሀያ ሶስት ሺህ ፍቃደኞች ላይ በተደረገ ጥናት ቃሪያን/በርበሬን በሳምንት ውስጥ ለአራት ጊዜ የተጠቀሙት ሰዎች የልብ መታወክ ችግራቸው 40%የቀነሰ ሲሆን ፣የአንጎል የደም ሥሮች ደም የማዘዋወር ሥራቸውን ሲያቋርጡ ወይም በአንጎል ውስጥ ደም ሲፈስ የሚከሰት ድንገተኛና አደገኛ የሕመም ሁኔታ የሆነው (ስትሮክ) በ61% እንዲቀንስ ተአምረኛው ቃሪያ አውንታዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል ። ጥናቱ በዚህ ብቻ አላበቃም ቃሪያ ወይም በርበሬ የተጠቀሙ አዘወትረው ካልተጠቀሙት ጋር ሲነጻጸር ተጠቃሚዎቹ ለሞት የመጋለጣቸው እድላቸው 23% መቀነሱን እና አጠቃላይ ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ በሽታዎች በቃሪያ እና በበርበሬ ዘር የተነሳ 34% የመቀነስ እድል አላቸው ሲሉ በቃሪያ ላይ ስፊ ጥናት ያደረጉት ተመራማሪዎቹ ዜናውን አብስረዋል።
በፖሊዚይ ከተማ በሚገኘው የኒዬርሙድ የምርምር ማእከል ውስጥ የሚገኙት የምርምሩ ዋና አስተባባሪ የሆኑት ማሪሉራ ቦናሲዬ እንደገለጹት”አንድ ሰው ጤናማ የሜድትራኒይንን አካባቢ ምግብ ቢበላ ሌላኛው ብዙ ጥራት የጎደለው ምግብን ቢጠቀም በቃሪያ፣በርበሬ፣ሚጥሚጣ፣ቄጦ ውስጥ ያለው ንጥረ ነገርን ከተጠቀመ(ች) ለበሽታ የመጋለጡ ዝንባሌ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው “ብለዋል።
ሰኞ እለት በአሜሪካ የልብ ምርመራ ኮሌጅ የጥናት መጽሔት (Journal of the American College of Cardiology) የወጣው የቃሪያ አስገራሚ ጠቀሜታን እንደሚያትተው ዘገባ ከሆነ በቃሪያ ውስጥ የሚገኘው ካፕሲሱን (capsaicin) የተባለው ንጥረ ነገር የልብ ስራን ያቀላጥፋል፣ የማቃጠል እና የካንሰር ሴሎችን የመራባት ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሏል። አንዳንድ ተመራማሪዎች በበኩላቸው የቃሪያ በጤንነታችን ውስጥ ቀጥተኛ ተጽእኖ ፈጣሪነት ብዙ ሊጠናበት ይገባል ሲሉ ምክር አዘል አስተያየት ሰንዝረዋል ።
የምግብ ጥናት ባለሙያው ዶ/ር ኢያን ጆንሰን በበኩላቸው “በርበሬን ከማይጠቀሙ ይልቅ የቃሪያ እና የበርበሬ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ ጤናማዎች ናቸው ማለቱ ይቀላል” ብለውታል። በእንግሊዝ የልብ ተቋም የምግብ አጥኚ የሆኑት ትሬሲ ፓርክር “ይህ ጥናት በቃሪያ እና በበርበሬ አፍቃሪዎች ዘንድ ትልቅ ትኩስ ዜና ነው” ሲሉ ዜናውን በበጎ ጎኑ ተቀብለውታል።
አጭር ማስታዎሻ:- ቃሪያም ሆነ በርበሬ የአብዛኛው ኢትዬጵያዊ እለታዊ ምግቡ መሆኑ እና ዋጋውን እንደዚሁ ሰማይ መጥቀሱ ቢታወቅም እናንተ የውሃ ዋጋ ጨመረ ብላችሁ የእንጀራ ዋጋን የምታነሩት፣ አፋር መንገድ ላይ አንዲት ግመል ሞታለች ብላችሁ የጨው ዋጋን በሁለት እጥፍ የምትጨምሩ፣ አሜሪካ በኩባ ላይ ማእቀብ ልትጥል ነው ሲባል የስጋን ዋጋ ከሜርኩሪ ዋጋ ጋር የምታመሳስሉት ጥቂት የአገሬ ስግብግብ ነጋዴዎች ይህቺን ስለ በርበሬ መልካም ዜናን ዋቢ በማድረግ ለወትሮውም በዘመኑ የአገራችን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጉዳይ ወገቡ የጎበጠው፣ ጨጓራው የተላላጠውየአገሬ ሸማችን ስሙ እና ቀለሙ እንጂ በውስጡ የበርበሬ ጣእም በሌለው ቁስ አታውኩት፣ የበርበሬንም ነገር “በርበሬ እኮ ድሮ ቀረ” አታድርጉት።አደረ!!!።