የኦሮሞ እና የአማራ ባለሃብቶች ያዘጋጁት የሰላም ኮንፈረንስ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ”ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ኮንፍረንሱ እንደሚካሄም እየተነገረ ነው።
ኮንፈረንሱን ያዘጋጀው የኦሮሞ እና የአማራ የባለሃብቶች ኮሜቴ እንደሆነም ታውቋል:: ኮሜቴው ኮንፈረንሱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ኮንፈረንሱ በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ለማመላከት የተዘጋጀ ነው ብሏል።
“ይህ ኮንፈረንስ በመንግሥት እየተሠራ ያለውን ሀገራዊ መግባባትን የመፍጠር እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም የማምጣት ጥረትን ለማገዝ የተዘጋጀ ነው” ሲሉም የኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው አስረድተዋል። በኮንፈረንሱ 6 ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበት እና በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል።
በኮንፈረንሱ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የሚሳተፉበት እንደሚሆን ተሰምቷል።
ኤፈርት ያመርተው የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ለቻይና ተሰጠ፤
አዲሱ የመከላከያ ልብስ በቅርቡ ሃገር ቤት ሊገባ ነው
የአገር መከላከያ ሠራዊት አዲስ የደንብ ልብስ ተዘጋጅቶለታል:: የሠራዊቱ የደንብ ልብስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው ጭነት የሚገባ ሲሆን ከሦስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መከላከያ ሚኒስቴር አንደሚረከብ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል::
አምስት ወር በፈጀ ሂደት ዓለም ዐቀፍ ጨረታ በማውጣት እና ከ15 የማያንሱ ድርጅቶችን በማወዳደር የተዘጋጀው የደንብ ልብስ ፣ የምድር እና የአየር ኃይልን የውጊያ እና የክብረ በዓላት ልብሶችን ከነመጫሚያው ያሟላ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል::
ግዢው የባህር ኃይልን የማያካትት ሲሆን በመዋቀር ላይ የሚገኘው የባህር ኃይል በቀጣይ እንደሚዘጋጅለት ነው የተነገረው። ጨረታውን ያሸነፈው የቻይና ድርጅትም ከመከላከያ ጋር ውል በማሰር ልብሶቹን ማዘጋጀት የጀመረ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊትም የምርት ሒደቱን በቅርብ እየተከታተለ ይገኛል። የደንብ ልብሶቹን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ የዋለው ጨርቅ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥራት ከፍ ያለ መሆኑንም የሠራዊቱ የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ ተናግረዋል::
ሠሞኑን ኢታማዦር ሹሙና ምክትል ኢታማዦር ሹሙ በተደጋጋሚ ለብሰውት የታየው የውጊያ ልብስ አዲሱ ዲዛይን መሆኑን ተረጋግጧል። አለባበሱ የጨርቁን ጥራት ሞክሮ ለማረጋገጥ የተደረገ መሆኑ ተገምቷል:: የምርት ሒደቱን ከኹለት ጊዜ በላይ ባለሞያዎች እየተላኩ ናሙና በመውሰድ እና በዓለም ዐቀፍ ላቦራቶሪ በማስገምገም ጥራቱን መከታተላቸውንም ለማወቅ ተችሏል::
ባለፉት በርካታ ዓመታት በትግራይ መልሶ ማቋቋም (ኤፈርት) ባለቤትነት የሚተዳደረው እና ከአድዋ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሠራዊቱን የደንብ ልብስ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል::
የአማራ ሜዲካል አክሲዮን ማኅበር በ100 ሚሊዮን ብር ሊመሠረት ነው ተባለ
የአማራ አክሲዮን ማኅበር የተሰኘ የሕክምና አልግሎት ሰጪ እና ቁሳቁስ አቅራቢ አክሲዮን ማኅበር ለመመስረት የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩ ተሰማ::
አክሲዮኑ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ በሚል የተቋቋመ ሲሆን ፤ የሕክምና አገልግሎት የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎችን ምርት ሽያጭ እና ማከፋፈል የአጭርና የረዥም የሕክምና የትምህርት እና ሥልጠና ማዕከላት መክፈትና አገልግሎት መስጠትን ዋነኛ ዓላማው ያደረገ ነው::
በውጭ አገራት ካሉ የጤና ተቋማት ጋር በወኪልና በኮሚሽን ኤጀንሲነት መሥራት ፣ የሕክምና ቱሪዝም አገልግሎት ፣ የሕክምና ፅዳት ኬሚካሎችና የሕክምና አልባሳት አቅራቢነት ፣ የጤና እና ጤና ነክ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ፣ እንዲሁም የማማከር አገልግሎት መስጠት እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን መስጠት ዓላማው ማድረጉንም ገልጿል::
በጤናው ዘርፍ ሰፊ ልምድ ባካበቱ ባለሞያዎች ተደራጅቷል የተባለው ማኅበሩ አክሲዮኑ መሸጥ መጀመሩን እና እስከተገባደደው ሳምንት ድረስም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡ እየተነገረ ነው::
በአድማው ምክነያት የአዲስ አበባ ሥጋ አቅርቦት 50 በመቶ ቀነሰ
በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ከኅዳር 24 / 2012 ጀምሮ ሥጋ ቤቶች እያካሄዱት ባለው የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት የሥጋ እርድ መጠን 50 በመቶ መቀነሱን ለማወቅ ችለናል:: ቀደም ባሉት ቀናት በቀን ሰባት መቶ በሬ የሚያርደው ቄራ ባለፉት ዐስር ቀናት ከ350 በሬ በላይ ለማረድ አልቻለም:: ይህ አኃዝ የሥጋ አቅርቦቱ በግማሽ ያህል (50) በመቶ መቀነሱን ያሳያል::
ሥጋ ቤቶቹ የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ሳያሳውቀን አዲስ የግብር አወሳሰን መመሪያን ተግባራዊ አድርጎብናል በሚል በከፊል አድማ በማድረጋቸው ነው ችግሩ የተከሰተው:: ግብር ሰብሳቢ ባለ ሥልጣኑ በ2010 ዓ.ም ያወጣውን የቁርጥ ግብር መመሪያ ለግብር ከፋዮ ዓመቱን ሙሉ እንዲገለገልበት ሳያሳውቅ በዓመቱ መጨረሻ በተግባር ላይ አውሎታል::
የአዲስ አበባ ሥጋ ቤቶች ማኅበር አባላቶቹ በራቸውን በመዝጋት እያካሄዱት ስላለው የሥራ ማቆም አድማ በትክክል የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል:: አባላቶቹ በከፊል ሥራቸውን ያቆሙበት ምክንያት በአዲስ አበባ ገቢውች ባለሥልጣን ጋር በተፈጠረው አለመግባባት እንደሆነ ገልጾ ቀሪዎቹ ግን ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት በመጪው ሳምንት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቼ አወያያለሁ ብሏል::