” የፈሪ አካሄዶችን አወግዛለሁ” ሲሉ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሞጣውን ጥቃት አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ
ጥቃት የሃይማኖቶችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚፃረሩ ጽንፈኛ አካሄዶችን አወግዛለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በአማራ ክልል፣ በሞጣ ከተማ ቤተክርስቲያንና መስጊዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ በፌስቡክ ገጻቸው ድርጊቱን ያወገዙበትን መግለጫ ለሕዝብ አድርሰዋል።
ከተለያየ አቅጣጫ መንግሥታቸው ላይ ሰላም አደፍራሽ እንቅስቃሴ የተቃጣባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በዛሬው መልዕክታቸው፣ “በብልጽግና ጎዳና ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ የሀገራችንን የቆየ የሃይማኖቶችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚፃረሩ ጽንፈኛ አካሄዶች ቦታ የላቸውም፤ እንዲህ ያሉ የፈሪ አካሄዶችን አጥብቄ አወግዛለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
መላው ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያንም የመከባበርና አብሮ የመኖር ጥልቅ እውቀታቸውን እንዲያጋሩም እና ሕዝባችን በሚታወቅበት ተከባብሮ የመኖር መንገድ እንዲጓዝ መክረዋል።
“ከፋፋይ አጀንዳዎችን መረዳትና መጠየፍ የጋራ ዕድገታችንን ለማረጋገጥ ያስችላል” ሲሉም ኢትዮጵያውያን ከመሰል ኹከትና ችግር ፈጣሪ ቅስቀሳዎች ራሱን እንዲያርቅ አሳስበዋል።
ከሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በዜጎች ላይ የደረሰን ዘግናኝ ግድያን ጨምሮ የእምነት ቦታዎች ላይ ቃጠሎ የደረሰ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጫ ከመስጠት የዘለለ እርምጃ እስከአሁን ድረስ የወሰዱት ይፋዊ እርምጃ አለመኖሩ ይታወቃል። በዚህም በመከሰቱ ጥፋቶች ዙሪያ መንግስታቸው በየትኛውም አካባቢ ለሚከሰቱ ተመሳሳይ ጥቃቶች ያለአድልዎ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው በርካቶች ሲወተውቱ እንደነበር ይታወቃል።
ሲኖዶሱና መጅሊሱ በእምነት ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሱ ጥቃቶችን በጋራ አውግዘዋል።
ትናንት ምሽት በአማራ ክልል በሞጣ ከተማ ቤተክርስቲያንና መስጊዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጡት መግለጫ ነው ድርጊቱን የኮነኑት::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ፤ በደረሰው ወቅታዊ እና ያልታሰበ ጉዳት በሀዘን ላይ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና ምዕመናት፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት እና የመጅሊስ አባላት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ የተሰማትን ሀዘን ይፋ አድርጋለች።
ድርጊቱ ለሀገሪቱ ሰላም እና እድገት የማይጠቅም ፣ እንዲሁም ለዘመናት የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚንድ በመሆኑ፤ መላው ሕዝብ ይህን ተረድቶ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጉዳዩ እስከሚጣራ በትዕግስት እንዲጠባበቅም ቤተክርስቲያን መልዕክት አስተላልፋለች::
ጉዳዮ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለደረሰው ጥቃቴ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊው ክትትል እንዲያደርጉም አሳስባለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሚመለከተው የመንግሥት፣ የሕግ እና የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩን በማጣራት ይፋ እንደሚደረግም ነው የገለፀችው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ፣ ሞጣ ከተማ ያልተረጋገጠ ወሬ በመሰራጨቱ ምክንያት መስጊዶች ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም የደረሰውን ጉዳት የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያወግዙት ምክር ቤቱ በመግለጫው ጥሪ ማቅረቡን ተመልክተናል። ለደረሰው ጥቃትና ውድመትም አጥፊዎች በህግ ጥላ ስር ውለው ድርጊቱ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል መንግሥት፤ ከሃይማኖት ገለልተኛ በሆነ አግባብ በህግ መንግሥቱ መሠረት እንዲሠራም ጠይቋል።
ምክር ቤቱ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ጠብቆና ተረጋግቶ የሃይማኖቱ መሪ ድርጅት ከሆነው ከመጅሊስ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት በጋራ እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፏል። ህዝበ ሙስሊሙ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በማውገዝ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም መስጊዶች በየዕለቱ ቁነትና ዱአ እንዲሁም በጾም የመጣውን መከራ ፈጣሪ እንዲመልሰው ዱአ እንዲያደርጉም ምክር ቤቱ ተማፅኗል።
በመጨረሻም መጅሊሱ ጉዳዩን የሚያጣራ የልኡካን ቡድን ወደ ቦታው እንደሚልክና ውጤቱንም በዝርዝር ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።
ደለሉ እንዳይሞላ ለተሰጋው የሕዳሴው ግድብ ችግር ላይ በመቀሌ ውይይት ተጀመረ
ታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ አስቀድሞ ለመከላከል የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡ በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመቐለ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ሕይወት ዘላቂነትና የአገሪቱ ህዳሴ ጉዞ መረጋገጥ በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ የውሃ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ መከላከል ይገባል ሲሉ ፣ የታለቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ አስጠንቅቀዋል።። ባለፉት ዓመታት በሁሉም አካባቢ ለተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተሰጠው ትኩረት 81 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነትና መተባበርን በተግባር ያረጋገጠው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ 69 ነጥብ 7 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱም ተገልጿል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ በውሃ ግድቦችና በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮሩ አምስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል መባሉም ታውቋል፡፡
በአራት ወራት ከግብርና ከማዕድን ምርቶች 916 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱ ተገለጸ
በ2012 በጀት ዓመት አራት ወራት ከግብርና፣ ከማምረቻ እና ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ 916 ነጥብ 21 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኘ መባሉን ዛሬ ተሰምቷል።
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት 1 ነጥብ 07 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነው ፤ 916 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘው፡፡ አፈፃፀሙ ከ2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 814 ነጥብ 73 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር ፣ በ 101 ነጥብ 48 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ እንዳለው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አረጋግጧል፡፡
በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት አራት ወራት ውስጥ ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት የወጪ ምርቶች አበባ፣ የብዕርና አገዳ እህሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን፣ ጫት፣ እና የኤሌክትሪክ ምርቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የዕቅዳቸውን ከ75 በመቶ እስከ 99 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች ደግሞ ባህር ዛፍ፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ሰም፣ ቡና፣ ታንታለም እና የቅባት እህሎች እንደሆኑም የደረሰን መረጃ ያሳያል፡፡
ከዕቅዳቸው ከ50 ከመቶ እስከ 74 ከመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የቁም እንሰሳት፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ እና ሻይ ቅጠል ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲስቲካልስ፣ ማር፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ቅመማ ቅመም፣ ሌሎች ማዕድናት፣ ዓሳ፣ ሥጋ ተረፈ ምርት፣ ወርቅ እና ብረታ ብረት መሆናቸው ተረጋግጧል::