መንግሥት እርምጃ ባለመውሰዱ ጥቃቶች እንደተስፋፉ የአማራ ክልል የሃይማኖት አባቶች ገለፁ
አርብ ዕለት ማምሻውን በአማራ ክልል፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ ጀሚዑል ኸይራት ታላቁ መስጊድ እና አየር ማረፊያ መስጊድ ላይ ቃጠሎ መድረሱ አሳዛኝ መሆኑን የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ።
ጉባኤው በድርጊቱ ማዘኑን ጠቁሞ ለወደፊትም እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳይፈጸም ጥሪውን አቅርቧል። የኢትዮጵያ ሐይማኖት ጉባኤ አባላትና የአማራ ክልል ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ወደ ሞጣ በማቅናት ከነዋሪዎች ጋር እንደሚወያዩና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት::
“የሠው ልጅ ሊደረግበት የማይገባውን ነገር ሌሎች ላይ ማድረጉ ተገቢ አይደለም” ያሉት የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፤ “ሰው የሚያደርሰው ይህን መሰሉ ጥፋት በሰማይም በምድርም የሚያስጠይቀው ነው፤ የሃይማኖት ተቋማት እንክብካቤ ሊደረግላቸው ሲገባ መቃጠላቸው ግራ የሚያጋባ ነው ብለዋል።
“የአካባቢው ህብረተሰብ አብሮ የሚበላ እና የሚጠጣ እንጂ ለዘረፋ እና ለእሳት የሚዳረግ አይደለም፤ ክቡር የሆነውን ቤተ ዕምነት ማቃጠልም ተገቢ አይደለም” ሲሉም የነዋሪውን ፍቅር አመላክተዋል::
መንግሥትም ቢሆን በየጊዜው በተለይ በአማራ ክልል የሚፈጠሩ ችግሮችን ቀድሞ ፈጥኖ የመከላከል ሥራ መሥራት እንዳለበት አስታውሰው እንዲህ አይነት ጥፋት ከተፈጸመ በኋላ ሰዎችን ለህግ አቅርቦ ፍጻሜ ላይ ማድረስ እንደሚገባ፤ ነገር ግን ህግ የጣሱ እርምት ማግኘት ሲገባቸው የተቀጡ ሰዎች ባለመኖራቸው ችግሩ ሊስፋፋ መቻሉን የሃይማኖት አባቶቹ ተናግረዋል። “እንዲህ ከሆነ ነው ሰው ነፍሱንም እጁንም የሚሰበሰብው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ሁሉም የነበረውን አብሮነት እና መቻቻል ማጠናከር፤ የተሳተፉትንም ለህግ እንዲቀርቡ በመተባበር እና የተዘረፈውንም ሃብትም መተካት አለብን” ያሉት ደግሞ የቦርዱ ሰብሳቢ መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ናቸው።
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ካዛንቺስን ሲያፀዱ አረፈዱ
ያልተጠበቁ ቦታዎች ላይ በመገኘት የሚታወቁት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በካዛንቺስ የፅዳት ዘመቻ አካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትርሩ ዛሬ የፅዳት ዘመቻውን ያከናወኑት ከከተማዋ ባለታክሲ ባለንብረቶች ጋር በሕብረት መሆኑን ታዝበናል። በፅዳት ዘመቻው 13 የሚነባስ ታክሲ እና 3 የሀይገር ሚኒባስ ማኅበራት ተሳታፊ መሆናቸውንም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የፅዳት ዘመቻው ዓላማ “ተርሚናሎቻችን ከፀዱ ከመተላለፊያነት ወደ ማረፊያነት ይቀየራሉ” የሚል መሆኑንም ከተሰቀሉት ባነሮችና ቅስቀሳዎች ተረድተናል።
የታክሲ ማኅበራቱ ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት ስብሰባ በመዲናዋ ለአዛውንቶች፣ ለአቅመ ደካማዎች እና ለህሙማን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከንቲባ ታከለ ኡማን ሸለመች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የምስጋና ሽልማት አበረከተች።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በቅርበትና በትብብር በመሥራታቸው ነው ተብሏል።
የምስጋና ሽልማቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተበረከተላቸው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ፤ በምስጋና ሽልማት ስነስርዓቱ የተገኙ ሲሆን፤ አስተደዳሪዎቹ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለቤተ ክርስቲያኗ እያሳዩ ላሉት ቀና ትብብርና ድጋፍ ምስጋቸውን አቅርበዋል።
ቤተክርቲያኗ ለረጅም ዓመታት በቅሬታነት ስታነሳቸው የነበሩ ይዞታና ማረጋገጫ ካርታዎችና የተለያዩ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲገኙ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ኢትዮጵያ ነገ ከወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
ቤተ ክርስቲያኗ በምታዘጋጃቸው መርሀ ግብሮችም ይሁን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በሚከበሩ በዓሎች የከተማ አስተዳደሩ የሚያሳየው ድጋፍና ትብብር በቤተ ክርስቲያኗ ምስጋና ተችሮታል።
በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ የጥምቀት በዓል በዪኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ በመስፈሩ የተሰማውን ደስታ ገልጾ፤ የመጪው የጥምቀት በዓል በደመቀና የቱሪስቶችን ቀልብ በሚስብ መልኩ እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ሞፈሪያት ካሚል ከሲልጤ-ወራቤ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ተወያዮ
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን እና የተለያዩ የፌደራል መንግሥቱና የስልጤ ዞን ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎችን ያካተተው ቡድን ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በወራቤ ከተማ ዛሬ ጥልቅ ውይይት አካሂዷል።
በዞኑ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር እና የመሠረተልማት ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያም ምክክር መደረጉ ተሰምቷል።
የስልጤ- ወራቤ ዞን ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ ከመሠረተ ልማት ዝርጋት ጋር በተያያዘ በውሃ፣ መንገድ እና መብራት አገልግሎት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለባለሥልጣናቱ አስረድተዋል።
ለቀረቡት የነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የዞኑ አስተዳደሪ አቶ ዓሊ ከድር፤ በተሳታፊዎች የተነሱ የመልካም አስተዳዳር እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አመላክተው፤ ለችግሮች መፈጠር ምክንያት የሆኑ አመራሮችን በማንሳት በምትኩ እንደ አዲስ አመራሮችን የማዋቀር ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚስተዋሉ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ ሥራ መጀመሩን ለወራቤ ነዋሪዎች አረጋግጠዋል። የፊታችን ሀሙስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ወደ ዞኑ በማቅናት ምልከታ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት አሁን ላይ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ይልቅ የተጀመሩትን ለመጨረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ መንግሥት ከሚሰጠው ምላሽ በተጨማሪም የዞኑ ነዋሪዎች እና የብሄሩ ተወላጆች እንደ ከዚህ በፊቱ በልማት ሥራዎች ላይ የሚያድርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ፣ ነዋሪዎች በዞኑ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር እና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በሰለጠነ መንገድ ለውይይት ማቅረባቸው የሚደነቅ ተግባር ነው ሲሉ አመስግነዋል።