“ሽምግልና ፓለቲካ አይደለም። መርህ ላይ ማተኮር ግን ነጻ ያወጣል።”
በፖለቲከኞቻችን ዘንድ ለፍትሕ ስርዓትና ለመርህ ሲባል ገለልተኛ መሆን ትርጉም አልባ ከሆነ ውሎ አደሯል፡፡ የኢዜማና የኢዴፓ ሙግትም የዚሁ የፓለቲካችን ክሽፈት መገለጫ ነው፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ አክብሮቴ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢዜማ በኩል በሕግ የተያዘው የኢዴፓ ጉዳይ እስኪጠናቀቀ ድረስ ለመታገስ ፍላጎት መታጣቱ የስህተቶች ሁሉ ስህተት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከመርህና ከሞራል ልዕልና ይልቅ የማንበርከክና ሁሉን የመሰልቀጥ የፖለቲካ አባዜም አደገኛነቱ ይህ ነው፡፡ ኢዜማ የያዘውን ይዞ ዳኝነት እስኪሰጥ ድረስ ኢዴፓን ሳይጠቀልል መታገል ይችል ነበር፡፡ ወቅታዊ ሁኔታው “ከኔ ጋር ነው” ብሎ ከማመንም ይቅል መርህ ላይ ብቻ ተመስርቶ ጉዳዩን በቅጡ ቢመረምር ኖሮ ዛሬ ላይ የኢዴፓ እውቅና ማግኘት አዲስ ነገር ባልሆነ ነበር። በጥቅሉ የተቃውሞ ጎራው መሻገር ያቃተው አደገኛ ፈተናም ይህው መርህ አልባነት ነው፡፡
ኢዴፓውያን ሕግንና መርህን ብቻ ተከትለው ከመንግስታዊ ተቋማት፣ ከቡድኖችና ከግለሰቦች ጋር ታግለው መብታቸውን ማስከበራቸው መርህ ሁሌም እንደሚያሸንፍ ትምህርት የሚሰጥ ተግባር ነው፡፡ አንተም ደጋግመህ እንዳነሳህው የስርዓቱና የጊዜው መሻሻል ለኢዴፓውያን አሸናፊነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ስላደረገ፤ ስርዓቱም ቢሆን ተገቢው ቦታ ሊሰጠው ይገባዋል፡፡
ወደ ዋናው ነጥብ ስንመጣ ለሽምግልና ጥያቄህና ለአክብሮትህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ነገር ግን፣ የፓለቲካ ሽምግልና እምብዛም ባላምንበትም የኢዴፓና ኢዜማ ጉዳዮ ለአንድ ወገን ብቻ የሚቀርብና የሚተው አይደለም፡፡ ጥያቄው በሁለቱም ጎራ ለሚገኙት ሃይሎች መቅረብ ነበረበት፡፡ ተበዳይ ካለ በዳይ አለ፡፡ ከኢዜማ በፊት እስከ ቅንጅት ዘመን ድረስ የሚመዘዝ፣ ጊዜው ያለፈበት የበቀልና የሴራ ፖለቲካ ዛሬም ጨርሶ እንዳልመከነም ግልጽ ነው፡፡
ኢዴፓን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በሚቆሰቆሰው እሳት የሚጎዳው ኢዴፓ ብቻ ሳይሆን ኢዜማን ጨምሮ በጥቅሉ የተቃውሞ ጎራውና ፖለቲካችን ሊሆን እንደሚችል በግንባር በተገናኘንበት ወቅት ተወያይተናል፡፡ ለሽምግልና የሚጋብዝ ሁኔታ ፓርቲያችሁ ውስጥ እንዲፈጠርም ውስጠ ፓርቲ ትግል ማድረጉ እንደሚጠቅም ጠቁሜ ነበር፡፡ ይህ አልሆነም። ኢዴፓም ሆነ ኢዜማ ውዝግቡን በዚሁ ከቀጠሉ የሚፈጠረው የጊዜና የሃብት ብክንት ብቻ ሳይሆን በተግባራቸው ልክ በሕዝብ ፊት መቅለል ሊሆን እንደሚችል መገመት ይገባቸዋል፡፡
ኢዴፓውያን ለሶስት ዓመት ውጣ ውረድ የበዛበት መራራ ትግል አደርገው ያገኙትን ድል ማክበራቸውና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መዘመራቸው አንዳችም ግድፈት የለበትም፡፡ የጥረታቸውና የድካማቸው ውጤት ስለሆነ ደስታቸውን መግለጻቸው እሰየው የሚስብልና የሚበረታታ ነው፡፡ ደስታን በቅጡ መያዝ ግን ያስፈልጋል፡፡ ደስታን በመግለጥ ሂደት ውስጥ ከመስመር ያለፈ ነገር ከተከሰተ፣ ኢዴፓውያን ከዚህ የላቀ የመርህ መሰረት ያለው ድርጅት ስለሆነ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር እራሱን እንደሚያርም እጠብቃለሁ፡፡
ንብረታቸውን ማስመለሳቸው ፍትሕ የማስከበሩ ሂደት ሌላው መገለጫ ስለሆነ በሕጋዊ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ካላደረጉ ድላቸው ጎዶሎ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ኢዜማም የራሱ ያልሆነውን ንብረት ከውዝግብና ከእንካ ሰላምታ በፊት መልሶ ጉዳዩን በሕግ አግባብ መከታተል ይችላል፡፡ ሕግ ለሁሉም የበላይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ኢዴፓ የጻፈው ደብዳቤ መጻፍ የነበረበት ለኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ነው የሚለው መነሻ ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ኢዜማ የኢዴፓን ቢሮዎች ሲወስድ በህጋዊ መንገድ ርክክብ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ ኪራይ ቤቶችም አስረካቢ ሆኖ በቦታ አልተሰየመም፡፡ ኢዜማ ቢሮውን ከኢዴፓ ላይ የወሰደው ውዝግብ ላይ ከነበሩት ሃይሎች ውስጥ ቁልፉ በአንዱ እጅ ስለተገኘ ብቻ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢዜማ በወቅቱ ባላለቀ ጉዳይ ቢሮ ከመቆጣጠር በላይ ማስተዋልና ማመዛዘን የሚገባውና የሚችል ድርጅት ነው፡፡ ይህንን ባለማድረጉ ሁለተኛው የኢዜማ ስህተት የሚጀምረው እዚህ ቦታ ላይ ይሆናል፡፡
ኢዜማ ለዜጎች ፍትሕ የቆም ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ቢያንስ ቢያንስ በሕግ እጅ ላይ ያለን ጉዳይ እልባት እስኪገኝ ድረስ መታገስ ነበረበት፡፡ ሌላውኛውና ዋነኛው ስህተት ደግሞ ይሄ ነው፡፡ በእርግጠኛነት መናገር የሚቻለው፣ ኢዜማ አንዳችም አስቸኳይና አጣዳፊ ጉዳይ ሳይኖርበት የኢዴፓን ቢሮና ንብረት መንጠቁ፣ ቁጣና ቂም በቀል ሊቀሰቅስ እንደሚችል መገመት ነበረበት፡፡ ኢዜማ ከጊዘያዊ አሸናፊነት ይልቅ፣ ዘለቄታ ያለው ሰላም እንደሚያዋጣ ተረድቶ እራሱን ከእንደዚህ ዓይነት ውሳኔም ማቀብ ነበረበት፡፡ ወደፊት ይህ ጉዳይ እንዳይደገምም እንደ ፓርቲ እራሳችሁን መገመግም ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በውዝግብ የባከነውና የሚባክንው ጊዜ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ ሊተረፍበት ይችል ነበር፡፡ ከግጭት ይልቅ ለሰላም፣ ለመከባበርና ለመቻቻል ቅድሚያ መስጠት ደግሞ ከዚህ ይጀምራል ባይ ነኝ፡፡
በግሌ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከእንካ ሰላንታ፣ ከስም ማጥፋት፣ ከማሳነስና “ከአቅላይነት” ከጥገኛነትና ከኔ በላይ ላሳር ከሚል ልክፍት ተላቆ ማየት እመኛለሁ፡፡ የሁላችንም የፓለቲካ አካሄድ በመርህ ላይ ቢመሰረት የሕዝባችንን የመከራ ዘመን ያሳጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለሕዝብ ሲባል በመከባባርና እውቅና በመስጠት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ብናራምድ ለሕዝባችን ፍትሕ፣ ርትዕና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ባንችል እንኳን ከተሸከመው በላይ ተጨማሪ የጥላቻና የቅራኔ ማህበራዊ ቀውስ በማቀጣጠል ሸክም ልንሆንበት አይገባም፡፡ ከሂደት እንደተማርነው አዋቂ፣ ዘውጌ፣ ተንታኝ፣ አክቲቪስት ነን በሚለው ሃይል ጠብ አጫሪነት ምክንያት ሕዝብ ለጥላቻ እንደሚዳረግ፣ በኛ ግጭት ወዳድነት ግጭት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል፣ በኛ ቂመኝነት ተበቃይ እንደሚሆን በቂ ተመክሮ አለን፡፡ ችግሩ የጋራ ስለሆነ የጋራ መፍትሔ ፍጠሩ።
በመጨረሻም አጥፊው ማንም ይሁን ማን፣ ኢዴፓዎች ባገኛችሁት ድል ሁላችንም ደስተኞች ነን፣ ኮርተናልም፡፡ የጽናት ምልክት መሆናችሁን በድጋሚ አረጋግጠችኃል፡፡ ድላችሁንም ማወደስና ድምጽችሁን ከፍ አድርጋችሁ መናገሩ ተገቢ ነው፡፡ የዛኑ ያህል ደግሞ እስጣ አገባን አስወግዱ፡፡ ቂም በቀልን ተሸገሩ፣ ወደ ውስጣችሁም ተመልከቱ፡፡ ለሃገርና ለሕዝባችን ክብርና ልዕልና ትኩረት ስጡ፡፡ ውጤት ሩቅ አይደለም።
ወንድም ሄኖክ በርካታ ለሃገር የሚቆረቆሩና አቅም ያላቸው አባላቶች ኢዜማ ውስጥ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ውጤታማ ፓርቲ ለመሆን ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ካረጀና ካፈጀ የቂም በቀል፣ የሴራ ፖለቲካ አንዲሁም ፖለቲከኞች እራሳችሁን በመጠበቅ ከትውልዱ ጋር ወደፊት በመራመድ ለውጤት እንድትበቁ እመኛለሁ፡፡