የዘውግ ፖለቲካ በጦዘበት ሃገር ተከታዩ የሃይማኖት ጎራ ለይቶ መባላት ነው። እንደውም በጥንት ግሪክ ዘመን የዘውግ ክፍፍል መነሻው የሃይማኖት ልዩነት ነው። በናይጀሪያ የሃይማኖት ጦርነት የሚባለው ፍጅት ከብሄር ጋር የተረዳበለ፣ ከአካባቢያዊነት ጋር የተሰናሰለ ነበር።
በሃገራችንም የሃይማኖት ክፍፍል አምጥተው በእሳት ሊጫወቱ የሚያምራቸው ሰዎች የዘውግ ፖለቲካው እሳት የሚፈልጉትን ያህል አልነድ ያላቸው፣በዘውግ ፖለቲካው የጥላቻ ዘር መርዝ ሲነሰንሱ የምናውቃቸው ራሳቸው ሰዎች ናቸው።
ከጥላቻ ፖለቲካ ምርት የሚሰበስብ ጥላቻ የሚዘራለትን ወቅታዊ አጀንዳ መምዘዙ የሚጠበቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ዘውግን እና ሃይማኖትን የሚያክል ጥሩመንገድ የለም። ሁለቱንም ካባ የሚለብሱት አንድ አይነት ሰዎች መሆናቸው ነገሩ የፖለቲከኝነት እንጅ የመንፈሳዊነት እንዳልሆነ ምስክር ነው።
መንፈሳዊ ከቅላፄው ያስታውቃል። የመንፈሳዊነት ዋናው በር በራሱ ላይ እንዲደረግ የማይፈልገውን በሰው ላይ አለማድረግ ነው። በክርስትና ደግሞ ግራውን ሲመቱ ቀኝን የመስጠት ትዕዛዝም አለ። በእስልምናም የዚህ ተመሳሳይ መንፈሳዊ ትህትናን የሚያዝ ህግ አይጠፋም።
ስለዚህ መንፈሳዊ ሰው መጀመሪያ የራሱን እምነት እንዲከበርለት ሲፈልግ ቀድሞ የወንድሙን እምነትም ያከብራል። የማያከብር ሲገጥመውም ቡጢ ጨብጦ ወደ ሃይል እና በቀል አይሮጥም። ይልቅስ ወንድሙ ያጠፋው ባያውቅ ነው ብሎ በማሰብ በፍቅር ሊያስተምረው ይሞክራል። “ሃይማኖቴን ስትነካ አስር እጥፍ እመልሳለሁ” ብሎ መነሳት የኮማንዶ ፀባይ እንጅ የመንፈሳዊ ሰው መለያ አይደለም!
መስጊድም ሆነ ቤክርስቲያን ለማቃጠል የሚሄዱ ሰዎች ፖለቲከኝነቱ በዝቶ ወደ ሚሊሻነት የወሰዳቸው ኮማንዶዎች እንጅ መንፈሳዊያን አይደሉም። የሌላው የእምነት ቤት በብዙ ቁጥር፣ በተለያየ ቦታ፣ ለብዙ ወራት በተከታታይ ሲቃጠል ለካምፋየር የተደረገ ሲመስለው የኖረ ሰው የእሱ የእምነት ቦታ የተነካ ሲመስለው አንዱ አንድሚሊዮን መስሎ የሚታየው ሰው አለ። ይህን የሚያሳየውም መነፅር መንፈሳዊነት ነው ኮማንዶነት?የእምነት ቦታዬ ተቃጠለ ብሎ አመት ሙሉ ሲያዝን የነበረ ሰው ዛሬ የሌላውን የእምነት ቦታ ለማቃጠል ያበቃው መንፈሳዊነት ነው ኮማንዶነት?!